ቢሮው በዘርፉ ኢንስትራክተሮች ለተከታታይ 10 ቀናት ያህል በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሲሰጥ የቆየው የሰርከስ ስፖርት መሰረታዊ የአሰልጣኞች የተግባር ስልጠና ተጠናቋል።
አብሮነትና ፍቅር ጎልቶ የሚንፀባረቅበት የሰርከስ ስፖርት የወቅቱን ሳይንሳዊ የአሰለጣጠን ሂደት በተከተለ መልኩ በክህሎትና በተግባር ልምምድ የበቃ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለመው የአሰልጣኞች ስልጠና ዘርፉን ከዘልማዳዊነት የሚያላቅቅ ነው ያሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ ናቸው።
ስልጠናው በሰርከስ ስፖርት መሰረታዊ ጥበብና የአሰለጣጠን ሂደት ላይ ያተኮረ እንደ ሀገር በዘርፉ የካበተ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ኢንስትራክተሮች አማካኝነት የተሰጠ ወቅታዊ ስልጠና መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰይፈ፤ ሰልጣኞች ባገኙት ስልጠና መሰረት በየአካባቢያቸው ሰርከስ ስፖርት ሳይንሳዊ የአሰለጣጠን ጥበቡን በተከተለ መልኩ ፍላጎትና ተሰጥኦ ላላቸው አካላት መሰጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለስልጠናው ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ያደረጉትን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲና የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያን አመስግነዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ዶክተር ደገለ ሾሞሮ፤ የሰርከስ ስፖርት የታዳጊዎችን ስብዕና የሚያንፅ ተወዳጅና ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣ ስፖርት መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለስፖርት ልማት መጎልበት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰርከስ ስፖርት ጥምረት ማህበር ተወካይና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ቤዛ ማንያዘዋል በበኩላቸው፤ ስልጠናው በሰርከስ ስፖርት መሰረታዊ የአሰለጣጠን ጥበብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው በዘርፉ ብቁ ሰልጣኞች እንዲፈሩ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያመላከቱት ኢንስትራክተር ቤዛ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘርፉን ለማጎልበት የሰጠውን ልዩ ትኩረት አድንቀዋል።
ላለፉት 10 ያህል ተከታታይ ቀናት የሰርከስ ስፖርት የአሰልጣኞች ስልጠናን ከተከታተሉ አካላት መካከል ሲስተር ዮሃንስ ሀንዲሶ፤ በስልጠናው በአጭር ጊዜ ውስጥ የነበራቸውን ዕውቀትና ልምድ ይበልጥ የሚያዳብር በተግባር ልምምድ የተደገፈ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልፃለች።
በስልጠናው ማጠቃለያ ሰልጣኞች ውብና ማራኪ የሰርከስ ስፖርት በማቅረብ ታዳሚውን አዝናንተዋል።
ስልጠናቸውን በብቃት ለተከታተሉ ሰልጣኞች እንዲሁም ድጋፍና አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋናና እውቅና ሰርተፊኬት በመስጠት ስልጠናው ተጠናቋል።
ዘጋቢ: አብዱልሃሚድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአረጋዉያን ያስገነባዉን የመኖሪያ እና እንክብካቤ ማዕከል ስራ አስጀመረ
የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ