ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተጠናከረ ክትትል እያደረገ መሆኑን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ወ/ሮ ዝናሽ ምትኩ እና አቶ ብርሃኑ ባዩ በከተማው በልብስ ስፌትና ሽያጭ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሲሆኑ የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚረጋገጠው መተሳሰብን ላይ የተመሠረተ መርህ ተከትሎ በመተግበር መሆኑን ገልፀው ሥራቸውን የማህበረሰቡን ኪስ በማይጎዳ መልኩ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በደመወዝ ማሻሻያ ሰበብ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ወገንን መጉዳትና ተገቢ አለመሆኑን የጠቆሙት ነጋዴዎቹ፣ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ አካላት በተቀመጠው የመሸጫ ተመን መሰረት ለሸማቾች በመሸጥ ሀገር ወዳድነታቸውን በኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መንግስት በቅርቡ ያደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ሰበብ በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረግና መሰል ህገ ወጥ ተግባራት በሚፈጽሙ አካላት ላይ መንግስት ክትትል በማድረግ እርምጃ እንዲወሰድ ነጋዴዎቹ ጠይቀዋል።
በይርጋጨፌ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉለሽን ቡድን መሪ አቶ መንግሥቱ መሰለ፤ በተለይም ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለነጋዴው ማህበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የዋጋ ጥናት ተደርጎ በግልጽ እንዲለጠፍ በማድረግ ሸማቹም ይህን ተመልክቶ ግብይት እንዲፈጽም መደረጉን ቡድን መሪው ገልጸዋል።
የይርጋጨፌ ከተማ ምክትል ከንቲባና ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ታምራት ሚጁ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ይርጋጨፌ ጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በከተማው ኅብረተሰቡን በታማኝነት ከማገልገል ይልቅ ያለአግባብ በአቋረጭ በደመወዝ ማስተካከያ ሰበብ የሚበዘብዙ ነጋዴች እንዳሉ ጠቁመው፤ የሸማቹና የንግዱን ማህበረሰብ መብት የጠበቀ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ለመንግስት ሰራተኛው የተደረገውን የደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ሀይል በማቋቋም ከሌሎች ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
ምክትል ከንቲባዋ አክለውም በከተማው ያለንግድ ፈቃድ የሚሠሩ 65 ፈቃድ ያላሳደሱ 15 የተፈቀደውን የዋጋ ተመን የማይለጥፉ 15 እንዲሁም የዋጋ ጭማሪ ያደርጉ 1 በጠቃላይ 97 ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
ሸማቹ ህብረተሰብ የዋጋ ተመን ያልለጠፉና የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ሲመለከት በጽ/ቤቱ ስልክ ቁጥሮች በመደወል አሊያም ለህግ አካላት ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆን ወ/ሮ ታምራት አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በስብዕና ግንባታ ስራ ላይ በማተኮር በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ጽህፈት ቤት ገለፀ
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአረጋዉያን ያስገነባዉን የመኖሪያ እና እንክብካቤ ማዕከል ስራ አስጀመረ
የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ