የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተገለፀ
በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት መሪነት በወረዳዉ ማዕከል ካንጋቲን ከተማ ”ምርታማነት ለቤተሰብ ብልፅግና በአዲስ እመርታ ገፅታ” በሚል መሪ ቃል በወቅታዊ የግብርና ስራዎች ዙርያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የወረዳዉ ምክትል አስተዳዳሪና ቆላማና መስኖ አካባቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ እንጂነር ሎካሎቦንግ ሎሴኮና ባደረጉት ንግግር፤ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለዋል።
አያይዘዉም ምርታማነትን ማሳደግ ማለት በተግባር ተተግብሮ ዉጤት የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ከመናገራቸዉ ባለፈ እንደወረዳ በዘርፉ በየቀበሌዉ ወጣ ገባ አፈፃፀምና ትግበራ የሚስተዋል በመሆኑ ሁሉም ቀበሌያት ላይ የትግበራው ወጥነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል አርብቶ አደር አርቦ ናሞያ፣ ሎሮት ቃሌም እና ሌሎችን ጨምሮ ከድህነት ለመላቀቅ መንግስት የሚያወርዳቸዉን ተልዕኮዎች ተቀብለዉ በአግባቡ ቢተገብሩ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸዉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።
በመድረኩ የመወያያ ሰነድ በወረዳዉ ግብርና ጽ/ቤት ሐላፊ በአቶ ታደለ በቀለ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን በሰነዱ ከቀረቡ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ ለግብርናዉ ዘርፍ የባለድርሻ አካላት ትኩረት ማነስ፣ የመካናይዜሽን ማሽኖች ሲበላሹ ወቅታዊ ጥገና አድርጎ ወደስራ አለማስገባት፣ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች የመንግስት ስራ ሰዓትን አክብሮ አለመስራት፣ የደን ጭፍጨፋ መበራከት፣ የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ አለመጠቀም የሚሉት ሐሳቦች ይገኙበታል።
በመድረኩ የሚመለከታቸዉ የወረዳ ስራ አስፈፃሚዎች፣ የጽ/ቤቱ ባለሙያዎች፣ ከየቀበሌያቱ የተዉጣጡ የግብርና ባለሙያዎች እና የቀበሌ ሊቃነ መናብርት ተሳትፊዎች ናቸዉ።
ተመሳሳይ መድረኮች በተዋረድ በቀበሌ ደረጃ እንደሚተገበሩም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ በቀለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የተመሰከረለት ምርጫ
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ