በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ በረከት ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ሀዋሳ ከተማ 32 ቀበሌያት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት ጨፌ፣ ዳቶ፣ ጥልቴ፣ ገመጦ፣ ቱሎ፣ ፋራና ሂጠታ ቀበሌያትን ለወባ ወረርሽኝ ተጋላጭ ናቸው፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት በሀይቁ አቅራቢያ መሆናቸውና አንዳንዶቹ ቀበሌያት ደግሞ ያሉበት አካባቢ ረግራጋማ የሆኑ ቦታዎች በመሆናቸው ምክንያት ለወባ ተጋላጭ እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝን መከላከል መሠረት ያደረገ ከመምሪያው እስከታች ባሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመው፤ የጤና ተቋማት በከተማ ደረጃ 14 እንዲሁም ጤና ኬላዎች ደግሞ 16 ያሉ ሲሆን በጤና ኬላዎች የወባ ግብዓት ኖሯቸው ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ ወረርሽኝ በሚታዩባቸው አካባቢዎች በስፋት እየተሰራን እንደሚገኝ ገለጸዋል፡፡
ወባን ለመከላከል የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በመለየት ማፋሰስና ማዳፈን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰራ ከኬሚካል ነፃ የሆነ የመጀመሪያ አማራጭ የመከላከል ዘዴ እንደሆነ ጠቁመው፤ ማፋሰስ በማይቻሉ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎች ላይ ደግሞ የጸረ-ዕጭ ኬሚካል ርጭት መርጨት ከሌሎቹ ዘዴዎች ይልቅ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የተጠበቀውን ያህል ጥቅም ላይ እንዲዉል ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ ተሰርቷል በማለት ተናግረዋል፡፡
የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች አንዱ በጤና ተቋማት የምርመራና ህክምና አገልግሎት ሲሆን በአጠቃላይ በከተማችን በሚገኙ ጤና ተቋማት 349,492 ሰዎች በተመላላሽ ህክምና ክፍል ከታዩት ውስጥ 74,288 (21.3 በመቶ) ሰዎች በአርዲት እና በማይክሮስኮት የደም ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 21,487 (28.9 በመቶ) ሰዎች የወባ በሽታ የተገኘባቸውና የጸረ ወባ መድሃኒት ህክምና በ2017 በመጀመሪያ ሩብ ዓመቱ ያገኙ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡
ኃላፊው ባስታላለፉት መልዕክት፤ ሀዋሳ ከተማ በአሁኑ ሰዓት በወባ ወረርሽኝ እየተጠቃች ከመሆኑ አንፃር ሕብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀምና ወባን ከመከላከል አንፃር የትኛውም ያቆሩ ውሀዎች ከጊቢና ከግቢ ውጪ ማፋሰስ ያስፈልጋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የጥልቴ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ታምሩ ሆባሶ በበኩላቸው፤ የወባ በሽታ እንደ ሀገር ስርጭቱ የጨመረና ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ እንደተከሰተ ጠቁመው መምሪያው ከክልል ጤና ጣቢያ ጀምሮ ስርጭቱን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በዋናነት የጤና ተቋሙ አገልግሎት የሚሰጠው ጥልቴ ቀበሌ እና ሆጋኔዋጮ ቀበሌ በዋናነት ወባማ ተብለው ከሚፈረጁ ቀበሌያት ዋነኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አካባቢው የሀይቅ ዳርቻና ከሀይቁ ተቆራርጠው የወጡ ሀይቆች መኖራቸው ለቢንቢ መራባት እድሉ ሰፊ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡
እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቁመው ውሀ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ስራዎች በዋናነት ተሰርተዋል፡፡
ቋሚና ጊዜያዊ ውሀ የሚያቁሩ ቦታዎችን በመለየት ከጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰማራት ቤት ለቤት በመሄድ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው የገለፁት፡፡
በተለይም ነፍሰጡር እናቶችና ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ቶሎ የመጠቃትና የመጎዳት እድላቸው ከፍ ስለሚል ለእነሱ ቅድሚያ በመስጠት አጎበር እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ከዚያም ባሻገር ማንኛውም ዓይነት የህመም ስሜት ያለው ግለሰብ ካለ ወደህክምና ጣቢያ ተቋማት በመምጣት ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ አንዱ የመከላከያው መንገድ ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ በጤና ተቋሙ ከመጡ ታማሚዎች ባሻገር የሕክምና መሣሪያን በመጠቀም ቤት ለቤት በመመርመር ሕክምና የሚሰጥበትም ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ሀና በቀለ
More Stories
የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተጠቆመ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ