የተመሰከረለት ምርጫ
በደረጀ ጥላሁን
በሶማሊላንድ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አብዱራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ አሸንፈዋል፡፡ የተቃዋሚው የ“ዋዳኒ/Waddani” ፓርቲ ከ60 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡ ለማሸነፋቸው ሶማሊላንድ አለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ ጥረት ለማድረግ ቃል መግባታቸው ምክንያት እንደሆነ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በገንዘብ እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች ለሁለት ዓመታት ዘግይቶ የነበረው ምርጫ በሰላም መጠናቀቁም ተመላክቷል። እጩዎቹ የታመመው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ እና ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል በመግባት የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል።
እ.ኤ.አ በ1991 ነፃነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ሶማሊያ ወደ ግጭት ስትገባ፣ ከሶማሊያ የፀጥታ ትግል በተቃራኒ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንደገነባች መረጃዎች ያሳያሉ።
የሶማሊላንድ ምርጫ ኮሚሽን አብዲራህማን ሞሃመድ አብዱላሂ “ኢሮ” በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን በመግለጽ ከጠቅላላው ድምጽ 63.92 በመቶውን ማግኘታቸውን አሳውቋል። ዋና ተቀናቃኛቸው የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ 34.81% በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ኦል አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስፍሯል።
ምርጫው በ2022 እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በፖለቲካ ልዩነት እና በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን የዘገበው ደግሞ ቪኦኤ ነው፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ለሶማሊላንድ ሕዝብ የበለጠ ብሩህ ተስፋ እንደሚፈጥሩ፣ እንዲሁም ለሴቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ቃል መግባታቸውን መረጃው ጠቅሷል፡፡
የሰብአዊ መብት ጠበቃ እና ተንታኝ ጉሌይድ አህመድ ጃማ እንዳሉት ምርጫው የሶማሊላንድን የዴሞክራሲ ጥንካሬን ያሳያል። አክለውም “ከሁለት አመታት የፖለቲካ ውዝግብ እና የፖለቲካ ብጥብጥ ያስከተለ የምርጫ መዘግየት በኋላ የምርጫው ሂደት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ መልካም ዜና ነው” ብለዋል።
“ነገር ግን ሶማሊላንድ እያጋጠሟት ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል። የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ሶማሊላንድን መታደግ እና የተከፋፈለውን ሕዝብ አንድ ሊያደርግ ይችላል ብዬ አምናለሁ።
“ተመራጩ ፕሬዝደንት ይህንን እንደ አሸናፊ-ተሸናፊ ሁኔታ ሊመለከቱት አይገባም። ህዝቡን አንድ ለማድረግ እቅድ ማውጣት አለባቸው። የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በሶማሊላንድ የተለያዩ ከተሞች 30 የምርጫ ጣቢያዎችን ጎብኝተው ለዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ድጋፋቸውን አረጋግጠዋል” ብለዋል።
ምርጫውን ለማየት በሶማሊላንድ የተገኙት ከዘጠኝ የአውሮፓ ሀገራት እና ከአሜሪካ የተውጣጡ የውጭ ዲፕሎማቶች፤ የሶማሊላንድ ብሄራዊ ምርጫ ኮሚሽን “ግልጽ የሆነ የመራጮች ምዝገባ እና የእጩዎች ጥቆማ ሂደት” ማካሄዱን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።
በሶማሊያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ማይክ ኒታቭሪያናኪስ ዲፕሎማቶቹ ከሶማሊላንድ ጋር ወደፊት ዴሞክራሲን እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሶማሊላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው ሰላማዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች “በግጭት” ምክንያት አልተከፈቱም ብለዋል።
ታዛቢዎቹ 146 የምርጫ ጣቢያዎችን ጎብኝተው “አንዳንድ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን” አይተዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች “አሠራሮችን አልተከተሉም” ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ በአጠቃላይ ሰዎች በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ፣ ድምጽ ለመስጠት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው እና ምርጫው ሰላማዊ እንደነበር አመላክተዋል።
መቀመጫውን በጆሃንስበርግ ያደረገው ብሬንትረስት ፋውንዴሽን፣ ታዛቢዎችን ወደ ሶማሊላንድ የላከ ሲሆን በምርጫው ቀን የምርጫውን ታማኝነት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት ከባድ ነገር አልተከሰተም ብሏል። “በእኛ እምነት ይህ ምርጫ የሶማሊላንድ የፋይናንስ እና የተቋማት ችግር ቢኖርም ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ተአማኒ ነበር” ሲል ጽፏል፡፡
በምርጫው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሲሆን ከ2003 ጀምሮ በሶማሊላንድ አራተኛው ምርጫ ነው። ክልሉ በ1991 ከተቀረው የሶማሊያ ክልል ቢለይም ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘም። ሶማሊያ አሁንም ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ ትወስዳለች።
ጉሌይድ አህመድ ጃማ ታዋቂ የሶማሊላንድ የሰብአዊ መብት ጠበቃ እና ተንታኝ ነው። እጩዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የቆዩባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ኢኮኖሚ፣ አለም አቀፍ እውቅና፣ የውጭ ጉዳይ፣ ሰላም እና ደህንነት መሆናቸውን ተናግሯል።
“የሶማሊላንድ ኢኮኖሚ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ በመሆኑ በዓለም ላይ ካሉት ድሃ ሀገሮች አንዷ ነች። በሶማሊላንድ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው እቃዎች ከውጪ የሚመጡ ናቸው” ሲል ተናግሯል።
አያይዞም የሶማሊላንድ ኤክስፖርት የእንስሳት እርባታ ብቻ ከመሆኑም በላይ ከሬሚታንስ እና ከዲያስፖራ ማህበረሰብ የተወሰነ ገንዘብ ይገኛል ማለቱን የቪኦኤ ዘገባ አመላክቷል፡፡
More Stories
የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተገለፀ
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ