ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት መሆኑን የኮሬ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡
“የምርታማነት እምርታ ለቤተሰብ ብልጽግና በአዲስ እይታ” በሚል መሪ ቃል የወቅታዊ ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ እንዳሉት፤ ህዝባችንን ከተረጅነት ለማላቀቅ ምሰሷችን የሆነውን ግብርናን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መምራት ከተረጅነት ወደ ምርታማነት የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን ለማስቀጠል እና ከድህነት ለመላቀቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በማዘመን፣ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ እና ሰራተኞችን በሚገባ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልገል ነው ያሉት አስተዳዳሪው።
የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንደባ በበኩላቸው፤ ግብርና እንደ ሀገር ባደጉት ሀገራት ተርታ ለመሰለፍና ያስቀመጥነውን ግብ ለማሳካት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያ ምርት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሪ የሚሆኑ ምርቶችን ከማምረት ረገድ ትርጉም ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በመኸር እርሻ በዋናነት ከተዘሩ አምስት የሰብል አይነቶች ምርት በመሰብሰብ ላይ እንገኛለን ያሉት ኃላፊው ለምርታማነትም ሆነ የቤተሰብ ብልጽግናን ለማሳደግ እስካሁን ከሠራነው ይልቅ በተሻለ ሁኔታ ጥረት ማድረግና መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሻገር በሚያግዙ በበጋ መስኖ፣ የመኸር እርሻ ዕቅድና ሥራን ጨምሮ የሚፈለገውን ያህል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ባለበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሰነድ በኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንደባ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በ2016 ዓመተ ምህረት የምርት ዘመን የስንዴ ምርት በምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ያውቁ ይሆን?
በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በቆይታቸው ተደስተው እንዲመለሱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ከ148ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ