ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ

ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ

የቶትንሃሙ የመሐል ስፍራ ተጫዋች የሆነው ሮድሪጎ ቤንታንኩር በቡድን አጋሩ ሰን ሁን እና ቤተሰቦቹ ላይ በሰጠው አስተያየት ምክንያት በ7 የእግር ኳስ ጨዋታዎች እገዳ በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ተጥሎበታል።

ተጫዋቹ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በሀገሩ ኡራጓይ ከአንድ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ደቡብ ኮሪያዊው ሰን ሁንግ ሚን እና ቤተሰቦቹ አይናቸውን ጨምሮ ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው የሚል አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ክስ ተከፍቶበት እንደነበረ አይዘነጋም።

የእግር ኳስ ማህበሩ ከጨዋታ ቅጣት በተጨማሪ የ100 ሺህ ፓውንድ የገንዘብ ቅጣት በ27 ዓመቱ ተጫዋች መጣሉን አሳውቋል።

በዚህም መሰረት ሮድሪጎ ቤንታንኩር በፕሪሚዬርሊጉ ክለቡ ከማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲ እንዲሁም በሊግ ካፕ ሩብ ፍፃሜ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የሚካሄደው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል።

በሙሉቀን ባሳ