አብሮነት፣ ፍቅርና አንድነት የሚነግስበት ታላቁ የረመዳን ወር የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት በጀንካ ከተማ ተካሄደ
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ተገኝተዋል።
በከተማው እስልምና ጉዳይ ም/ቤት በተሰናዳው የኢፍጣር ስነ ስርአት ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና የዞኑ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ከፍተኛ ስራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል።
የም/ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በኢፍጣር ስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ አብሮነትና ፍቅር የሚነግስበት የኢፍጣር ስነ ስርዓት ልዩ ኢስላማዊ እሴት ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ብዝሃነትን ያከበረ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህ የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
መሰል ሀይማኖታዊ እሴቶች ለአብሮነት ወሳኝ በመሆናቸው በጎዳና ላይ ጭምር በማከናወን የተሻለ ሰብዓዊ ተግባር የሚፈጸምበት አጋጣሚ ሊደረግ የሚገባው እንደሆነም አብራርተዋል።
ለዚህ ደግሞ ዲሞክራሲን ማጽናት ተገቢ ይሆናል ያሉት አፈ ጉባኤው፥ ህዝበ ሙስሊሙ በቀጣይ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ሁሉም ማንነቶች ተደምረው እንደ ሀገር ውበታችንን ያጎሉታል፤ የዚሁ መገለጫ የሆነው የረመዳን ቅዱስ ወር የኢፍጣር መርሃ ግብርም በመልካምነት ተገናኝተን በድምቀት በማሳለፋችን አስደሳች ስሜት ፈጥሮብናል ያሉት ደግሞ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።
በሥነ-ሥርዓቱ የተመለከትነው አብሮነት በሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳር ስራዎች ላይ የምንደግመው ሊሆን ይገባልም ብለዋል።
የከተማው የኡላማ ም/ቤት ጸሐፊ ሼህ አብዱልመሊክ ኢብራሂም ኢፍጣር የረመዳን ወር የመተሳሰብና አብሮነት በረከት መሆኑን አንስተዋል።
ወቅቱ የሙስሊሙ ጥያቄ ምላሽ አጊንቶ መንፈሳዊ ስርአቶች በነጻነት የሚከበሩበት መሆኑን አስታውሰው ሌሎች ጥያቄዎች እየተመለሱ ለተሻለ ሀገር ግንባታ ህዝበ ሙስሊሙ በጋራ የሚረባረብበት እንዲሆንም በመቀራረብ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ኡመርዲን ግርማ በበኩላቸው ታላቁ የረመዳን ወር የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓቱ የአብሮነት፣ የፍቅርና አንድነት መንፈስ የሚጎላበትን የረመዳን ወር ታሳቢ በማድረግ ይህ መርሃ ግብር መሰናዳቱን ገልጸዋል።
የእዝነትና የዱአ ወቅት በሆነው የረመዳን ወር ቅዱስ ቁርአንን ያወረደልን አላህ በኢፍጣሩ ያሳዬነውን ፍቅር መተሳሰብ በጽኑ አብሮነትና ሀገራዊ ሰላም የሚገለጥ እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ዘመናዊ የመሬት ሕግ ሥርዓት መዘርጋትና ተቋማዊ አቅምን መገንባት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፍቼ ጫምበላላ በዓል በታላቁ ሶሬሳ ጉዱማሌ መከበር ጀምሯል
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ከተማ በሲዳማ ባሕል አዳራሽ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል