መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
በደረሰ አስፋው
ገና በለጋ ዕድሜዋ በእጇ እስክርቢቶ ሳትጨብጥ፣ ቡና ከአቦል እስከ ቶናና በረካ በሚጠጣበት ጊዜ፣ የጎረቤት ሰዎች ይህቺ ስታድግ ዲግሪ ትጭናለች ይሉ ነበር፡፡ አንዳንዶች ዶክተር፤ ሌሎች ደግሞ ፕሮፌሰር ትሆናለች እያሉ ይተነብዩላት ነበር፡፡ የመንደሩ ሰው አባባል በሷ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ አድጋ ተምራ ኮሌጅ በጥሳ ዶክተር ለመባል የነበራትን ምኞት እውን ለማድረግ በትምህርቷ ትተጋ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምንም እንኳ ያሰበቸው ባይሆንም፡፡
ወላጅ አባቷ ከእርሻ ስራቸው ጎን ለጎን በአካባቢው ታዋቂ የእህል ነጋዴ ነበሩ፡፡ የታታሪው ገበሬና ነጋዴ መልካም ስራ ግን እንዳማረበት አልዘለቀም፡፡ በሽታ የሚሉት ጠላት ገባበት፡፡ ያጋጠማቸው የአይን ህመም ጠንቶባቸው ለአይነ ስውርነት ተጋለጡ። እርሻውም ሆነ ንግዱ ተገታ፡፡ ከእርሻ ወደ ጎተራ መክተቱና ነግዶ ማትረፉም አቆመ፡፡ በገጠር ለእርሻ በከተማ ለንግድ የሚንቀሳቀሱት ታታሪው ነጋዴ እግራቸው ተይዞ በቤት ውስጥ ተቀመጡ፡፡
ችግሩ ለቤተሰብም ተረፈ፡፡ ብርቱካንንም ከሞቀው ቤቷ አውጥቶ አዲስ አበባ የሰው ቤት ተቀጣሪ አደረጋት፡፡ ሰርታ ሀብት ፈጥራ የአባቷን ኃላፊነት ለመሸከም፡፡ ይሁን እንጂ ተልካ በወጣችበት የአዲስ አበባ ጎዳና የደረሰባት የመኪና አደጋ ውጥኗን መና አስቀረ፡፡ የተሻለ ሰው ሆና ቤተሰቧን ከችግር ለመታደግ የነበራት ምኞት ተገታ፡፡ ለወራትም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስትታከም ቆየች፡፡ በመጨረሻም በህክምና ባለሞያዎች ሁለቱም እግሮቿ እንዲቆረጡ ተወሰነና ለዛሬው አካል ጉዳት መዳረጓን በሐሳብ የኋሊት ተጉዛ አወጋችኝ፡፡
ዛሬ ብርቱካን የአካል ጉዳተኛ ብትሆንም ከታታሪው አባቷ የቀሰመችው ንግድ የሷና የቤተሰቧን ችግር የምትታደግበት ሥራዋ ሆኗል፡፡ በችግር መሸነፍን አትወድም፡፡ አካል ጉዳትን ለሌላ ዓላማ መጠቀሚያ ማድረግን አትሻም፡፡ ነገ የተሻለ ሰው የመሆን ምኞቷ በአካል ጉዳት አልተጨናገፈም፡፡ ክረምት በጋ አይዛትም፡፡ ገጠር ከተማ አይገድባትም። የጀመረችው ትምህርትም መቋጫውን አግኝቷል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትም እንዳሰበችው አልሆነም፡፡ በልጅነቷ የመንደሯ ሰዎች እንዳሉት ባይሆነም ንግዱ ግን “ነገን የማይበት ነው” ብላ ይዘዋለች፡፡ በንግዱ ዓለም አንዴ በሌባ መዘረፍ ሌላ ጊዜ የቤተሰብ ኃላፊነት ቢፈትናትም ከዓላማዋ ግን አላዘናጋትም፡፡
ብርቱካን ሀይሉ ሀዲያ ዞን፣ ፎንቆ ወረዳ፣ ምዕራብ ኦማ ቀበሌ ነው የተወለደችው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በትውልድ መንደሯ ምዕራብ ኦማ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በፎንቆ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ተምራለች፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤቷ ባይሳካም ቀድሞም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ንግድ ትሞካክር ስለነበር፣ ዛሬ ላይ ሙሉ ጊዜዋን በንግድ ሥራ ላይ አድርጋለች፡፡ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሎሚና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ነው የምትነግደው፡፡ ለሌላውም ንግድ የታገደች አለመሆኑን በመጠቆም፡፡
“መቀመጥ አልወድም ቀደም ሲልም ጊዜዬን ለጥናት፣ ለትምህርት፣ ለራሴና ለስራ በመስጠት የጊዜን አጠቃቀም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ አሁን የተሰማራሁበት ንግድም ሙሉ ጊዜዬን በመጠቀሜ ውጤታማ እንድሆን አግዞኛል” በማለት ነው የተናገረችው፡፡
በ2009 ዓ.ም በደረሰባት የመኪና አደጋ ለአካል ጉዳት መዳረጓን ነው የምትገልጸው። ለስራ ብላ ወደ አዲስ አበባ በሄደች ጊዜ ያጋጠማት የቀን ክፉ እንደሆነ ታነሳለች። ድንገት ወደ ሱቅ ተልካ እንደወጣች መንገድ ስታቋርጥ በሲኖ ትራክ ከባድ የጭነት መኪና ነው አደጋው የተከሰተባት፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ3 ወር ያህል በህክምና ስትረዳ ቆይታ ህይወቷ ቢተርፍም፣ እግሮቿ ግን ከመቆረጥ የሚታደጋቸው አልተገኘም፡፡
ለአመታት በክራንች ድጋፍ መንቀሳቀስ ግድ ሆነባት፡፡ ሰርታ ሀብት ፈጥራ የተሻለ ሰው ለመሆን የነበራትን ውጥን ቢያጨናግፈውም፣ ብርቱካን ዛሬም መንፈሰ ጠንካራ ነች። ትናንትን ማየት አትሻም፣ የነገዋን ማንነት እንጂ፡፡ አካል ጉዳት በአጋጣሚዎች የሚከሰት ቢሆንም አእምሯዋ ጤናማ በመሆኑ ሰርታ ለመለወጥ የሚገድባት እንደሌለ በመጠቆም። “በህይወት ስተርፍ ፈጣሪ ያሰበልኝ ሌላ ዕድል እንዳለ ተገነዘብኩ” ያለችው ብርቱካን ይህን እውን ለማድረግ ገጠር ከተማ እያለች የመነገዷም ምክንያት ይሄው ነው፡፡
ዛሬ ላይ ብርቱካንን ከክራንች ድጋፍ የሚታደጋትን ህክምና የአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል አድርጎላታል። የአካል ድጋፉም /ሰው-ሰራሽ እግር/ ያለ ክራንች መንቀሳቀስ እንዳስቻላት ነው የገለጸችው፡፡ ይህንንም እንደመልካም ዕድል ትመለከተዋለች። መቀመጥ ለማትወደው ለዛሬዋ ነጋዴ ብርቱካን ካለምንም ችግር መንቀሳቀስ በመቻሏ ደስተኛም አድርጓታል፡፡
ወላጅ አባቷና እናቷ የሷን እጅ የሚጠብቁ መሆናቸውን የገለጸችው ብርቱካን፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጠንካራ ሰራተኛ ሆኖ መገኘትን ትሻለች፡፡ ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክልን በመጠቀም እስከ ገጠር ድረስ እየሄደች ንግዷን እንደምታከናውን ነው የተናገረችው፡፡ በዚህ ጥረቷም ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ እንደቻለች ታነሳለች፡፡
“አካል ጉዳተኛ መባልን፣ እራስን ዝቅ አድርጎ መኖርን አልሻም፡፡ ሰርቼ መለወጥ እንጂ፡፡ አካል ጉዳት የመለመኛ መንገድ አይደለም፡፡ እግሬን ባጣም ፈጣሪ ንጹህ አእምሮ አልነሳኝም፡፡ ትልቁን ሀብቴን አላጣሁም፡፡ እኔ በህይወቴ ለሌሎች የበጎ ተምሳሌት ለመሆን እንጂ በማይረባ ነገር ስሜ እንዲጠቀስ አልሻም፡፡
በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤቷን እንዳወቀች ሙሉ ጊዜዋን በንግዱ ላይ ነው ያዋለችው፡፡ ውጤታማ እንደሆነችም ታነሳለች፡፡ በሥራ ዓለም ውስጥ ፈተና አይጠፋም፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በቦርሳ የያዘችው ገንዘብ የሌባ እጅ ገባ፡፡ ካለምንም መንቀሳቀሻ አስቀራት፡፡ በችግር ላይ ችግር ተደራረበባት፡፡ የፈተናዎች መደራረብ ሚስጥሩ ምንድነው አለች፡፡ ለዚህ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባትና ተስፋዋን ማለምለም እንዳለባት ለራሷ ቃል ገባች፤ አደረገችውም፡፡
“ሊጥሉኝ ለሚያስቡት እጅ አልሰጥም፡፡ አሸናፊ ሆኖ መገኘት እንጂ፡፡ ከመቀመጥ ይልቅ መስራት ደግሞ ችግርን የማሸነፊያው መንገድ ነው፡፡ ስራ እወዳለሁ፡፡ እንደዚህ ሆኛለሁ በማለት እጄንም ለልመና አልዘረጋሁም” ነው ያለችው፡፡
“በህይወት መኖር ከቻልኩ ትርጉም ያለው ህይወትን መኖር እመኛለሁ፡፡ ነገ ወልጄ ከብጄ መኖር ለምሻው ህልሜ ዛሬ ሰርቼ ማግኘትን ነው ምኞቴ፡፡ ትዳር መስርቼ፣ ልጆች ወልጄ ማስተማርም እሻለሁ፡፡ ልጆቼም እኔ በሄድኩበት ሳይሆን ከኔ የተሻለ ህይወት የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ መሰረቱ እኔው ነኝ፡፡ ይህን ለማሳካትም ጥሩ ነጋዴ የመሆን ውጥን አለኝ፡፡
“አካል ጉዳትን ለልመና የመጠቀም አዝማሚያ ዘመን ያለፈበት ነው፡፡ አካል ጉዳተኛ የሚባለው እጅና እግር የሌለው፣ ጆሮ የማይሰማና ሌላ የአካል ጉዳት ያለበት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ከሰውነቱ አካል አንዱ ወይም ሁለቱን አጥቷል ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው የአካል ጉዳት የሚባለውና ለልመና ደጅ የሚያስወጣው የአእምሮ ችግር ብቻ ነው፡፡
“የኛ ማህበረሰብ ማውገዝ ያለበትን አልተረዳም፡፡ አካል ጉዳተኛውን ያገላል፣ ለማኙን ደግሞ በመስጠት ያበረታታል። ይህ የሚጣረስ ተግባር ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች እድሉን ካገኙ መስራት ይችላሉ። ሰርተውም እራሳቸውን የለወጡ አሉ፡፡ ለሌሎች የተረፉትንም ቤት ይቁጠረው፡፡ ጠንካራ ማንነትን እንዲፈጥሩ ሊታገዙ ይገባቸዋል እንጂ እንዲለምኑ ማበረታታት ተገቢ አይደለም፡፡ እጅ የተሰበሰበ ጊዜ መውደቂያው ይከፋልና መስራት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው” በማለት ነው ብርቱካን ሀሳቧን የቋጨችው፡፡
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን