“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ

“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ

በአለምሸት ግርማ

በአንድ የኮንዶሚኒየም የጋራ መኖሪያ መግቢያ በር ጥግ ላይ ያለች ቦታ ናት። በውስጧ ለማረፊያ የሚሆኑ ከጣውላ የተዘጋጁ መቀመጫዎች አሉ። መፅሐፍትም በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ በየዓይነቱ ተደርድረዋል። በተለይ ደግሞ አበባዎቹ በዙሪያው ባሉ ዛፎች ላይ በተሰራላቸው መስቀያ ላይ ሆነው ለአካባቢው ልዩ ውበትን አላብሰውታል። በተለይ ደግሞ የበጋው ፀሃይ በሚገኝበት ጊዜ በዚያች ስፍራ ከሚተላለፉ መንገደኞች መካከል ጫማ ለማስጠረግ በሚል ምክንያት በውስጡ ለማረፍ የማይፈልግ የለም ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ በአረንጓዴ የተከበበው ይህ ቦታ የተመልካችን ዓይን ከመማረኩም በላይ በዚያ ለሚሰራው ወጣት የገቢ ምንጭ ወይም መተዳደሪያ ሆኗል።

ወጣት አያኖ ብርሃኑ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በሲዳማ ክልል፥ ሰሜናዊ ዞን ቦሪቻ ወረዳ ነው። ቤተሰቦቹ አርሶ አደሮች ሲሆኑ እሱም እንደአካባቢው ታዳጊዎች ትምህርቱን እየተማረ፤ አቅሙ በፈቀደው ቤተሰቦቹን እያገዘ ነው ያደገው።

ትምህርቱን “በይርባ ያናሴ ትምህርት ቤት” የተከታተለ ሲሆን በ2009 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ወደ ሚቀጥለው ክፍል የሚያስገባ ውጤት ሳይመጣለት ይቀራል። በዚህ ጊዜ ነበር የህይወቱን አዲስ ምዕራፍ ማሰብ የጀመረው። ከጥቂት ቆይታ በኋላ በሃሳቡ ፀንቶ ለቤተሰቦቹ ሃዋሳ ስራ እንዳገኘ ይነግራቸውና ወደ ሃዋሳ ይመጣል።

ይሁን እንጂ ወደ ሃዋሳ ሲመጣ ምንም ዓይነት ስራ አግኝቶ ባይሆንም ያገኘውን ለመስራት ግን ራሱን አሳምኖ ነበር። በዚህ ውሳኔው መሰረት ሃዋሳ ከተማ መጥቶ ባረፈበት አካባቢ የነበሩ ሰዎችን በጉልበቱ እያገለገለና ያገኘውን ስራ እየሰራ በሚያገኘው ገቢ የዕለት ጉርሱን ይሸፍን እንደነበር አጫውቶናል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ስራ ሳይመርጥ እየሰራ ከሰዎችም ጋር እየተግባባ ኑሮውን ቀጠለ።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ታታሪነቱን ያዩ አንድ ግለሰብ አንድ መቶ ብር ይሰጡታል። እሱም ገንዘቡን የሰጡት መልካም ሰው ሃሳባቸው ስራ እንዲሰራበት መሆኑ ገብቶት የሊስትሮ ዕቃ ይገዛል። ገንዘቡ የቻለለትን ያህል ቀለምም ከየዓይነቱ ሩብ፣ ሩብ በመግዛት ወደ ስራ ለመግባት ይዘጋጃል። በወቅቱ የስራ ፍላጎት እንጂ ችሎታውም ሆነ ልምዱ አልነበረውም። ሁኔታውን ሲያስታውስም ፥“ወደስራ የገባሁት ከችግር ለመውጣት ነው” ይላል ወጣት አያኖ።

ሆኖም ራሱን ለመለወጥ ከነበረው ፍላጎት የተነሳ ስራውን እየሰራ ልምዱን እንዳገኘ አጫውቶናል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ጫማዎችን በማምጣትና እንዲሰራ በማድረግ ያበረታቱት እንደነበር ያስታውሳል። ጥረቱን የተመለከቱት የሰፈሩ ሰዎችም ስራውን የሚሰራበትን ምቹ ቦታም ፈቀዱለት።

በዚያም ከጫማው ስራ በተጓዳኝ ባለው ትርፍ ሰዓት ማንኛውንም የጉልበት ስራ እየሰራ ተጨማሪ ገቢም ፈጥሯል። በዚህ ብቻም አልተገደበም። ያገለገሉ ዕቃዎችን በመጠቀም የተለያዩ የአበባ ችግኞችን አዘጋጅቶ በስራ ቦታው ላይ ለአይን በሚማርክ መልኩ አስጊጦበታል። ማስጌጥ ብቻም አይደለም፥ ለሚፈልጉ ሰዎች ችግኙን ለሽያጭ ያቀርብም ነበር።

እሱ ግን ከችግኝ ሽያጩም በላይ የስራ ቦታውን ሰዎች ሲያዩት የሚያስደስት እንዲሆን እንደሚፈልግ አጫውቶናል።

በልጅነቱ ሀኪም የመሆን ህልም እንደነበረው የሚናገረው ወጣቱ፥ ያንን ፍላጎቱን ማሳካት ባይችልም በሚችለው አቅም ለሰዎች በጎ ነገር ማድረግን እንደሚፈልግ ነው የሚናገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ መፅሐፍ የማንበብ ፍቅር የነበረው ሲሆን ዛሬም ይህንን ልምዱን አላቋረጠም።

ከሚያገኘው ገቢ እና ከሚመገበው ላይ በመቀነስ መፅሐፍትን የመግዛት ልምድ አለው። ስራውን ሲያጠናቅቅ እረፍት የሚያደርገው እያነበበ መሆኑንና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ያነሳል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ለራሱ ብቻ አንብቦ መፅሐፍቱን ቤቱ ማስቀመጥን አልወደደም። ይልቁንም ሌሎችም እንዲያነቡ ለማድረግ አሰበ። በሃሳቡ መሰረት በሚሰራበት ቦታ የመፅሐፍት መደርደሪያ በማዘጋጀት ለአንባቢዎች ክፍት አደረገ።

በአሁኑ ወቅት ከሶስተኛ ክፍል እስከ 12ተኛ ክፍል ድረስ ያሉ መማሪያ መፅሐፍት፣ መንፈሳዊ መፅሐፍት እና ሌሎችንም መፅሐፍት አቅሙ በፈቀደው መጠን ለአንባቢዎች ዝግጁ አድርጓል። በዚህም መሰረት በሚሰራበት አካባቢ ያሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች መፅሐፍ በመዋስ አንብበው ይመልሳሉ። ይህንን ተግባሩን ልዩ የሚደርገው በሌሎች አካባቢዎች ሰዎች መፅሐፍትን የሚያውሱት በኪራይ ነው፤ እሱ ግን ትርፌ የሰዎች ደስታ ነው ይላል። በዚህም ምክንያት መፅሐፍቱን ለሰዎች የሚያውሰውም በነፃ ነው። በማንበባቸው ስለሚጠቀሙ እንዲያነቡ ነው የማበረታታው ይላል።

ስለንባብ ሲናገርም፦ “ሰዎች ሲያነቡ የተለያየ እውቀት ያገኛሉ። ተማሪዎችም በትምህርታቸው የተሻለ እውቀት ይኖራቸዋል። የሚያነብ ሰው ከክፋት ይልቅ በጎነት ላይ ነው ትኩረቱን የሚያደርገው። አዕምሮ የሚሰራው በማንበብ ስለሆነ ሰዎች እንዲያነቡ አበረታታለሁ”

ትምህርቱን ለማሻሻል ካለው ጉጉት የተነሳ ከሚያገኘው ገቢ በመቆጠብም በዩኒክ ስታር ኮሌጅ በአካውንቲንግ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቋል። በአሁኑ ሰዓትም የስነ-መለኮት ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በግል ስራ ለመሰማራት በመሞከር ላይ እንደሆነ አስረድቶናል።

በቀጣይ ምን አቅደሃል? የሚል ጥያቄ አቅርበንለት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል፦

“ተጨማሪ መፅሐፍት በማሟላት ወደ ቤተ-መፅሐፍ ለማሳደግ አቅጃለሁ። ከዚህ ሌላ ህፃናት በመልካም ስነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ለማድረግም በምችለው አቅም ለማስተማር ዝግጁ ነኝ። ትውልዱ መልካም ስነ-ምግባር ያለው እንዲሆን ህፃናት በስነ-ምግባር ታንፀው ማደግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን። የነገ ሀገር ተረካቢ ስለሆኑ ሁላችንም ልናንፃቸው ይገባል። በተለይ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ልጆች በጥንቃቄ ካልተጠቀሙ ተጎጂ ስለሚሆኑ፥ ወላጆች ሊያግዟቸውና ሊከታተሏቸው ይገባል። ቴክኖሎጂ በዕውቀት ተደግፈን ካልተጠቀምነው ጉዳቱ ያመዝናልና ልጆች መጀመሪያ መፅሐፍት ማንበብ አለባቸው። ፈጣሪን እንዲፈሩ፣ ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙና እንዲያከብሩ በዕውቀት መገንባት አለባቸው። እውቀት እንዲኖራቸው ደግሞ መፅሐፍትን ማንበብ ስለሚያስፈልጋቸው ለዚያ ነው ቢያንስ በቻልኩት መጠን ቤተ-መፅሐፍት ከፍቼ አገልግሎት መስጠት የምፈልገው። በዚህም ብዙዎች ይታነፃሉ የሚል እምነት አለኝ። በተጨማሪም ችግኝ በስፋት በማፍላት ለገበያ ማቅረብ እፈልጋለሁ።

በስራ ህይወት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ያጋጥማልና የማይረሳውን ገጠመኝ እንዲያጫውተን ጠይቀነው ነበር፦

ይህን ጥያቄ ስናቀርብለት ዓይኖቹ እንባ አቅርረው ነበር። ከጥቂት ዝምታ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ፦ “ገጠመኞቼ ብዙ ናቸው። ብዙ ጊዜ ተርቤያለሁ። በአንድ ወቅት ለአራት ቀናት ምግብና ውሃ ሳልቀምስ አሳልፌያለሁ። ማደሪያ በማጣት ለሁለት ዓመታት ኮንዶሚኒየም ጊቢ ውስጥ ባጃጅ ውስጥ አድሬያለሁ። የትም ብደርስ የማልረሳው ገጠመኜ ችግሬ ነው”

ከዚሁ ጋር አያይዞ በሚሰራበት አካባቢ እንደእናትና እንደአባት ሆነው በችግሩ ጊዜ የደረሱለት ወገኖች መኖራቸውን ይናገራል። ሲርበው ፊቱን አይተው የሚረዱ፤ በጉድለቱ የሚደርሱለት ሰዎች እንዳሉ የነገረን እነሱን ከማመስገን ጋር ነው።

አልፎ አልፎ ቤተሰቦቹን እየሔደ እንደሚጠይቃቸውና በጉልበቱም ሆነ በሚችለው ነገር ሁሉ እንደሚያግዛቸውም አጫውቶናል። ታናናሾቹን መከታተልም የሁል ጊዜ ተግባሩ ነው።

ወደፊት ለመስራት ላቀዳቸው እቅዶች እንደእንቅፋት ነው ብሎ የሚያስበው የቦታ ችግር መሆኑንም በማንሳት በተለይም አበባ እና ሌሎች ችግኞችን ለማፍላት ሰፋ ያለ ቦታ ያስፈልጋልና የሚመለከተው አካል ሃሳቤንና ጥረቴን አይቶ ቢያግዘኝ የሚል ሃሳብም አቅርቧል።