“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ

በገነት ደጉ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶክተር እውነቱ ዘለቀ ይባላሉ፡፡ በህክምና ሙያ ለ13 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነት እንዲሁም በያኔት ድንገተኛ ቀዶ ህክምና ማዕከል ሀኪም ናቸው፡፡ ካንሰር ምንድ ነው? መንስኤዎቹ እና አጋላጭ ምክንያቶቹስ ምን ይመስላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች አንስተንላቸዋል፡፡ በሌሎች በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያም ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!

ዶክተር እውነቱ፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!

ንጋት፡- ከልጅነት ጀምሮ ያለው የትምህርት ዓለም ጉዞዎን በማንሳት እንጀምር?

ዶክተር እውነቱ ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በአማራ ክልል ጎጃም አካባቢ ነው፡፡ ከ1ኛ- 8ኛ ክፍል ወይን ውሃ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማርኩ ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ሞጣ መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡

በ1999 ዓ.ም ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመግባት፣ በ2004 ዓ.ም ነው ትምህርቴን የጨረስኩት፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በመምህርነት እና በህክምና ሙያ ላይ ነኝ፡፡

የመጀመሪያ ድግሪዬን በሀዋሰ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነው የተታተልኩት። ከተመረኩ በኋላ እዛው በመምህርነት ተቀጥሬ ስሰራ ከቆዩ በኋላ ለአራት ዓመታት የቀዶ ህክምና ስፔሻሊት ትምህርት እዛው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጥንቻለሁ፡፡

በያኔት ሆስፒታል ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ማዕከል በቀዶ ጥገና ሀኪምነት እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነት ለአራት ተከታታይ ዓመታት አገልግዬ ለ“ሰብ” ስፔሻሊቲ ስልጠና ወደ ህንድ ሀገር ሄድኩኝ፡፡

በዚያም አንድ ዓመት የካንሰር ቀዶ ህክምና አጥንቼ በቅርብ ወደ ሀገሬ በመመለስ በጠቅላላ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት እና የካንሰር ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት በመሆን በቀድሞ መስሪያ ቤቶቼ እያገለገልኩ ነው፡፡

ንጋት፡- ካንሰር ምንድነው?

ዶክተር እውነቱ፡- ካንሰር እንደ ቃሉ አንድ በሽታ አይደለም፡፡ ካንሰር የወል ወይም ጥቀል ስም ነው ብንል ይቀለናል፡፡ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ምናልባት ቢቆጠሩ ከ200 በላይ በሽታዎችን በጥቅል የምንጠራበት ስያሜ ነው፡፡

ካንሰር የሰው ልጅ ታሪክ መፃፍ ከጀመረበት ከክርስቶስ ልደት ከ3ሺህ ዓመተ ዓለም ጀምሮ በሰዎች ታሪክ ላይ ተጽፎ የሚገኝ አብሮ የኖረ በሽታ ነው፡፡

በሰዎች ታሪክ ውስጥ የቆየውን ያክል የካንሰር ህክምና በጠልቀት የታወቀው ምናልባት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ህክምና እና በሽታው በአብዛኛው መላምቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሁለት አስርት ዓመታት ነው ካንሰር ምንድነው? እንዴት ያደርጋል? ህክምናውስ ምንድነው? የሚለው በጥልቀት የታወቀው ማለት ይቻላል፡፡

ንጋት፡- ካንሰር ዓይነቶች አሉት ይባላል? ምንድን ናቸው?

ዶክተር እውነቱ፡- ካንሰር ዓይነቶች አሉት፡፡ በተለያየ መስፈርት ምናልባትም በህክምናው ከሚነሱበት ህዋስ ወይም ቲሹ አንፃር ልንከፋፍላቸው እንችላለን፡፡

በህክምና ቋንቋ ኢፕቴሊየም ከሚባለው የሚነሱት ካንሲሎማ እንለዋለን፡፡ ሌሎችን ሳርኮማስ እንላቸዋልን፡፡ ከጠጣር የሚነሱትን የደም ካንሰር እንላለን፡፡ ሌሎቸም ብዙ ዓይነት የካንሰር ዓይነቶች አሉ፡፡

ከዚህ ይልቅ የእኛ ማህበረሰብ የሚያውቃቸው በሽታው ከሚታይባቸው የሰውነት አካል ነው። ለማህበረሰቡም የጡት፣ የማህፀን፣ የአንጀት፣ የደም፣ የጨጓራ እንዲሁም የቆዳ ካንሰር በማለት ብዙ ዓይነት የካንሰር ዓይነቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ እንዲህ ናቸው ተብሎ በቁጥር አይገለፁም፡፡ ግን በእነዚህ ሁለት መሰረታዊ መንገዶች ይገለፃሉ፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም ካንሰር በባህሪው አንድ ዓይነት ላይሆን ይችላል የምንለው፡፡

ንጋት፡- የካንሰር ዓይነቶች የተለያዩ በመሆናቸው ህክምናውን ውስብስብ አያደርገውም?

ዶክተር እውነቱ፡- የካንሰር ዓይነቶች በመለያየታቸው ምክንያት ህክምናውን ውስብስብ እና አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ካንሰርን ዓይነቶቹ ብቻ አይደሉም የሚለያየው፡፡ ደረጃው እና የበሽታው ባህሪ ከካንሰር ካንሰር ይለያያል፡፡ ሁለት የጡት ካንሰር ታካሚዎች ቢመጡ የሁለቱም ታካሚዎች የጡት ካንሰር ይሁን እንጂ ዓይነቱ ግን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም በምርመራ ቴክኖሎጂ ለመለየት እጅግ አዳጋች እና ውጤቱንም ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ያም ሂደት ነው የካንሰር በሽታን ውጤትን ከባድ የሚያደርገው፡፡ ሁሉም የመጡት ታካሚዎች አንድ ዓይነት መድሀኒትና ተመሳሳይ ህክምና ይሰጣል ማለት ግን አይደለም። ለዚህም ነው የካንሰር ህክምና ለየግል እንጂ ተመሳሳይ ህክምና የለውም የሚባለው፡፡

ንጋት፡- ካንሰር የሚያመጡ መንስኤዎች እና አጋላጭ ምክንያቶች ምንድናቸው?

ዶክተር እውነቱ፡- ካንሰርን ከሌሎች ከለመድናቸው እና ከምናውቃቸው በሽታዎች ለየት የሚያደርገው አንዱ እንደሌሎች በሽታዎች ከውጪ የሚመጣ ባዕድ ነገር ወደ ውስጣችን የሚገባ አይደለም፡፡ የራሳችን ሰውነት በሚፈጠረው ጉዳት የሚከሰት ነው፡፡

ሰውነታችን ባለማቋረጥ በተከታታይ ሁሌም እራሱን የሚያድስ ትልቅ ፋብሪካ ነው። የሚያድሰውም ሴሎችን በማባዛት ነው፡፡ ሴሎችም የአገልግሎት ዕድሜ እና ገደብ አላቸው፡፡ አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ የሚያስወግድበት እና በአዲስ የሚተካበት ተፈጥሮአዊ ሂደት አለ፡፡

እነዚህን የሚቆጣጠር ደግሞ በዘረመል ነው። ይህም የሴል መባዛት በጣም ውስብስብ ቢሆንም ስህተቶች ይኖሩታል፡፡ እነዚህም ስህተቶች የማይሆኑና ያልታሰቡ ሴሎችን ይፈጠራሉ። እነዚህ ሴሎች የእኛን ሴል ስለማይመስሉ የታሰበላቸውን ስራ አይሰሩም፡፡ ከእኛም የሰውነት ቁጥጥር ውጪ ናቸው፡፡ እነዚህ ሴሎች ናቸው ካንሰር የሚሆኑት፡፡

የመባዛታቸው ፍጥነት ሀይለኛ እና ለሰውነት የሚያስፈልገውን ተግባር የማይሰሩ ናቸው፡፡ በመጨረሻም የሰውነታችንን መደበኛ ሴሎችን ያጠፉና እነሱ ይባዛሉ፡፡ የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር እነርሱ ብቻ ስለሚመገቡ ካንሰር የተያዘ ሰው የሚከሳውና የሰውነት ክብደት የሚቀንሰው ለዚያ ነው፡፡ በዚህም ብቻ አያበቁም በደም ዝውውር ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ስለሚዘዋወሩ ብዙ የሰውነት ክፍሎችን የሚጎዱበትን ምቹ ሁኔታን ያገኛሉ፡፡ ይህም የተጎዳው ዘረመል (ጂን) በቤተሰብ ሊወረስ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ካንሰር በቤተሰብ ሊወረስ ይችላል የሚባለው፡፡

ከዚህም ውጪ አኗኗራችንና አመጋገባችን በቤተሰብ ባይኖርም እንኳን ለካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ በአብዛኛውም ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ለካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ይጨምራል። ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መውሰድ እንዲሁም ከልክ ያለፈ ውፍረት ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ እና በታዳጊ ሀገራት ኢንፌክሽኖችና ወ.ዘ.ተ ካንሰርን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

ንጋት፡- ካንሰር የትኞቹን የማህበረሰብ ክፍሎች ያጠቃል?

ዶክተር እውነቱ፡- ካንሰር በመሰረቱ የማያጠቃው የማህበረሰብ ክፍል የለም፡፡ ሁሉንም ፆታ እና ቀለም ሳይለይ ሁሉንም የሰው ዘር ያጠቃል፡፡ ይህ ማለት ግን ስርጭቱ ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለይም ደም ካንሰር ስርጭትን ብናይ በህፃናት ላይ ሊሰፋ ይችላል። በህፃናት ብቻ የሚፈጠሩ የካንሰር ዓይነቶች አሉ፣ በሴቶች ብቻ የሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች አሉ እንዲሁም ወንዶችን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነት አለ እንጂ በጥቅሉ የማያጠቃው የማህበረሰብ ክፍል የለም፡፡

ንጋት፡-ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ የካንሰር ስርጭት አሁናዊ ሁኔታው ምን ይመስላል?

ዶክተር እውነቱ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የስርጭቱም ሆነ የሞት ምጣኔው እየጨመረ በመምጣቱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ እያንዳንዱ ማህበረሰብም ይህን ማወቅና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡

የማህበረሰቡን አኗኗር እና አመጋገብን ተከትሎ ከተላላፊ በሽታዎች ይልቅ በጣም ጨምሯል፡፡ በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ሁሉ የካንሰር ስርጭት ጨምሯል፡፡ ባደጉት ሀገራት ዕድገታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2020 እና በ2022 ያወጣውን መረጃ ስናይ በዓለም ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 10 ሚሊየን ሰዎች በካንሰር ይሞታሉ፤ እስከ 20 ሚሊየን አዳዲስ ካንሰር ተጠቂዎች ይኖራሉ፡፡

ኮቪድ በአምስት ዓመት ውስጥ 7 ሚሊየን ሰዎችን የገደለ ሲሆን ካንሰር ግን በአንድ ዓመት ውስጥ የገደለው ከኮቪድ ጋር ሲነፃፀር ብዙ ነው ማለት ነው፡፡

በሀገራችን የካንሰር ምዝገባ ወደ ሆስፒታል መጥቶ የታከመውን ሰው ተመዝግቦ ይህን ያህል ነው ተብሎ ያለው ቁጥር ለመግለፅ እዚ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ እንኳን ለካንሰር ለሌሎችም በሽታዎች ምዝገባ ስርዓት የለንም፡፡

ምናልባት ማህበረሰብ ዓቀፍ የካንሰር ምዝገባ ያለው ከ2004 ጀምሮ በአዲስ አበባ ላይ ነው። ምንአልባት ከዚያ ተነስተን መገመት ይቻላል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በተመሳሳይ ወቅት ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ሺህ ሰው በአንድ ዓመት ውስጥ በካንሰር በሽታ እንደሚያዝ ያመላክታል፡፡ እስከ 50 ሺህ ሰዎች ደግሞ በካንሰር ይሞታሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨረ ነው፡፡

ስለዚህ የማህበረሰብ ጤና ትኩረት ይፈልጋል። በተለይም በዚህ ሰዓት ካንሰር ከፍተኛ የሆነ የማህበረሰብ ጤና ጠንቅ በሽታ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ግለስብ፣ ማህበረሰብ ብሎም እንደ መንግስት ሰፊ የትኩረት አቅጣጫ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡

ከዚህም በፊት የማህፀን ጫፍ ካንሰር የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ መንግስት እንደ መንግስት ባደረገው እርብርብ እና ክትባት በስፋት በመስጠቱ አሁን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው። እንደ ሀገር አንደኛ ደራጃ ላይ ያለው የጡት ካንሰር ሲሆን መንግስትም በ2016 ዓ.ም ለጡት ካንሰር ጋይድ ላይን አውጥቶ በመስራቱ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ማከም ሆነ ቅድመ መከላከል ትኩረት ከተደረገ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሶሰተኛ ደረጃ ላይ ያለው የትልቁ አንጀት ካንሰር ናቸው፡፡

ንጋት፡- ካንሰርን መከላከል ይቻል ይሆን? እንዴት?

ዶክተር እውነቱ፡- የካንሰር በሽታን መከላከል ይቻላል፡፡ ግን ሁሉንም የካንሰር ዓይነቶችን መከላከል አይቻል ይሆናል፡፡ መከላከል በመሰረቱ በሁለት ይከፈላል፡፡ ቀዳሚ መከላከል የምንለው እንዳይዘን መጠንቀቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከታመምን በኋላ ቶሎ መታከምን ሌላው መከላከያ መንገድ እንለዋለን፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች አዎ መከላከል ይቻላል የሚል ምላሽ አለኝ፡፡

ሌላው ካንሰርን መከላከል የምንችለው አጋላጭ ምክንያቶችን በመጠንቀቅ ነው። ለሁሉም ባይሆንም ግን በምናውቀው ልክ አጋላጭ ምክንያቶችን ማወቅና መጠንቀቅ ብሎም የታወቀውን አጋላጭ ምክንያት ካንሰር ከመሆኑ በፊት መታከም ነው፡፡ ለዚህም ነው ተጋላጭነትን በመከላከል ካንሰር እንዳይዘን መከላከል እንችላለን፡፡

በእኛ ሀገር በጣም ያልተለመደው የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ እና ዓመታዊ የካንሰር ምርመራ ማድረግ መለመድ ቢቻል መልካም ነው። ይህ ከሆነ በሽታውን በጊዜ ማወቅ እና ማከም ብሎም እስከማጥፋት ድረስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የቅድመ ካንሰር ምርመራ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ንጋት፡- ህብረተሰቡ በካንሰር በሽታ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አለው ብለው ያምናሉ? ካልሆነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶክተር እውነቱ፡- በአጭሩ የለውም፡፡ በጣም ትልቅ ክፍተት ስላለ ዋጋ እንዳያስከፍለን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ ቴክኖሎጂ በዘመነበት እና ሚዲያው ለሁሉም ሰው በእጁ በመሆኑ መጥፎውን ነገር እንደምንሰማው ሁሉ ስለበሽታው መስማትና ማወቅ ቢቻል መልካም ነው፡፡

ትናንትን ወደኋላ መለስ ብለን ስናይ ከቀድሞው ጊዜ የተሻለ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በጣም በሚገርም ሁኔታ ስሙን መፃፍ የማይችል ሰው እና ስለ ካንሰር ሰምቶ የማውቅ ሰው ወደ ህክምና ተቋም በወቅቱ እና በጊዜ ሲመጣ ይታያል። ግንዛቤ በትምህርት ደረጃ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ለጤናችን የምንሰጠው ትኩረት የመጀመሪያው ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ጤና ዘብ መቆም አለበት፡፡

ንጋት፡- ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?

ዶክተር እውነቱ፡- ካንሰርን ቀድሞ መከላከል እና ማዳን ይቻላል፡፡ ለማዳንና ለማከም ግን ወደ ህክምና ተቋም መምጣት አለብን፡፡ ቢያንስ ከሀኪም ጋር መነጋገር እና መወያየትን ይስፈልጋል። ሰፈር ወስጥ ባሉ ነገሮች ከምንቆይ ካንሰር የሁሉንም ደጃፍ ያንኳኳ በሽታ በመሆኑ ከባለሙያ ጋር መነጋርና ማማከር ወሳኝ ነው፡፡

ከካንሰር በሽታ የምንድንበት የእኛ ወደ ህክምና ተቋም መቼ መጣን የምንለው እና ቀድመንስ ትኩረት ሰጥተናል ወይ? ካንሰርን ቀድሞ መከላከል ስለሚቻል እና አጋላጭ ሁኔታዎችን በመለየት አለመያዝም ይቻላል፡፡ ቀድመንም ነገ እና ተነገወዲያ ካንሰርን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ማከም ይቻላል፡፡ ከዚያም አልፎ የመጀመሪያ ጊዜያትን ሙሉ ለሙሉ ማከም ይቻላል፡፡ የካንሰር በሽታ ህክምና እና መፍትሔ ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ የሚጠራጠረውን ነገር በሰውነቱ ካየ ወደ ህክምና በአፋጣኝ በመምጣት መታየት አለበት መልዕክቴ ነው፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም በድጋሜ አመሠግናለሁ፡፡

ዶክተር እውነቱ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡