‎የማህበረሰቡን የፍትህ ጥማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ውጤታማ የሆኑ ድጋፋዊ ክትትሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የማህበረሰቡን የፍትህ ጥማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ተቀናጅቶ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ አሳሰቡ።

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፍትህ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወር አፈጻጸም እና የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ለመገምገም የተዘጋጀ ጉባኤ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

‎የቢሮው የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በተለያዩ ባለሙያዎች በዝርዝር የቀረበ ሲሆን የአፈጻጸም ሪፖርቱን ተከትሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።

‎የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አሁንም በተቀናጀና በተደራጀ ሁኔታ መከወን የሚገቡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መኖራቸውን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ አሳስበዋል።

‎ክልሉ በርካታ ልምድና ዕውቀት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዋና አፈ ጉባኤው፥ የዜጎችን የፍትህ ጥማት ለማርካት ተመካክሮና ተደጋግፎ መስራት ይጠበቃል ብለዋል ።

‎የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እውን እንዲሆን በሶስትዮሽና በአራትዮሽ ቅንጅታዊና ድጋፋዊ ክትትል ሥራዎች ተለይተው በወጡ ጉዳዮች ላይ አንዱ ለሌላው መግፋትና መወቃቀስን ያስቀረና ለማህበረሰቡ ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት ዓላማ አድርጎ የመከረበት ጉባኤ መሆኑ ተመላክቷል።

‎ነጻ የሕግ አገልግሎት አሰጣጥ እና ባህላዊ የዳኝነት እንቅስቃሴዎች በስፋት መሠራት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

‎በባህላዊ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በካፋ እና በሸካ ዞኖች ውስጥ የታየው መልካም ተሞክሮ በሌሎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ዋና አፈ ጉባኤው አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶች በምክክር መስተካከል እንዳለባቸው አመላክተዋል።

‎በጥርጣሬ ተይዘው /በኤግዚብሽ/ በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ንብረቶች ከአገልግሎት ውጭ ከመሆናቸው አስቀድሞ ተጣርተው ለሚመለከተው አካል ቀርበው መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

‎ከሰው ኃይል እጥረት ጋር ተያይዘው የቀረቡት ጉዳዮች ያለውን የሰው ኃይል አመጣጥኖ ከመጠቀም ባሻገር ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች በክልሉ ፐብሊክ ሰርቨስ ቢሮ በማስጠናት ተገቢ የሆነ ምላሽ እንዲሰጥባቸው አቅጣጫ ሰጥተዋል ።

‎በየማረሚያ ተቋማት የሚታዩ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዋና አፈ ጉባኤው፥ የቀለብ ምጣኔዎችን በሚመለከት በጥናት የሚስተካከሉ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆኖ ማረሚያ ተቋማት በበኩሉ በተለያዩ ልማት ሥራዎች በመሳተፍ ተደማሪ አቅም በመገንባት የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

‎በጉባኤው ላይ የቀረበው የተቋሙ የ5 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተገቢነት ያለውና ሊያሰራ የሚችል መሆኑን አቶ ወንድሙ አስረድተዋል።

‎ክልሉ ከተደራጀበት እስካሁን ባለው ሂደት 49 አዋጆች መውጣታቸውን ጠቁመው በየተቋማቱ የሕግ የበላይነት ከማስፈን አንጻር ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው ዋና አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

‎ውጤታማ የሆኑ ድጋፋዊ ክትትሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የማህበረሰቡን ፍትህ ጥማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ተቀናጅቶ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል በማለት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ አሳስበዋል።

‎ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን