በፈረኦን ደበበ
የተፈጥሮ አየር መዛባት ሁሉ በሀገሪቱ ያነጣጠረ መስሏል፡፡ ከወራት በፊት ሲነገር የነበረውን ድርቅ ሁሉ በማስረሳት። በድርቅ ተጎድተዋል ሲባሉ የነበሩ እነዚያ ውብ ከተሞችና መንደሮች ሰሞኑን በጎርፍ ተውጠው መሰንበታቸው ሰው በተፈጥሮ ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግም ሆኗል፡፡
አዎን የስፖርትና የብዙ ባህላዊ ክዋኔዎች ማዕከል የሆነችው ስፔን ሰሞኑን ስታለቅስ ሰንብታለች፡፡ ዜጎቿ መግቢያና መውጫ አጡ። ቀይ መረሬ ዓይነት አፈሯ ተጠራርጎ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ገባ፡፡ መውጫ መንገድ አሳጥቶ ለብርድና ቸነፈር ዳረጋቸው፡፡
የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ ችግሩ በሌሎች የዓለም አካባቢዎች ከተከሰተው ይለያል፤ ምክንያቱም ዝግጅት ለማድረግ ዕድል ባለመስጠቱ፡፡ ከዚህ በፊት በአውሮፓ በተመሳሳይ ከተጎዱ ሀገራትም ይለያል፤ ምክንያቱም የጋራ ጥረት ማድረግ እንዳይችሉ በተናጠል እየመጣ ስለመታቸው፡፡
የዘንድሮውን ትዕይንት ብንመለከት መዘዙ የጀመረው በጀርመንና ጣሊያን ነበር። ወንዞች ሞሉ፡፡ ሜዳውን ሁሉ አጥለቀለቁ። እንደ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጥቁር ሳይሆን ቀይ አፈራቸውን እየጠራረገ ነዋሪዎችንም ለጉዳት ዳረገ የወጡ ፎቶዎችን እንደተመለከትነው ከሆነ፡፡
ያደረሰው ውድመት እንዲህ ባይነገርም በፖላንድ ያደረሰው አደጋም ሲያልፍ ብዙዎች አህጉሪቱ በሠላም ወደ አዲሱ የአውሮፓዊያን ዓመት 2025 ትሻገራለች ብለው ጠብቀው ነበር፡፡ ይህ ተስፋ ግን አሳዛኝ ገጽታ ተላብሶ መጣ፡፡ ውድመትና ስቃይን በስፔን አስከተለ።
እንደተመራማሪዎች ገለፃ ከሆነ ከአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ጋር እንደተያያዘ የሚነገረው ክስተት ከአካባቢው የዝናብ ወቅት ጋር ሁሉ የተያያዘ ሲሆን ዓመት ከዓመትም የመከሰት ዕድል አለው፡፡ ይህንን አዝማሚያ ክላይመት ሴንትራል የተባለው ጥናት ቡድን ከሞቃታማው አትላንቲክ ከሚነሳውና ዝናብ አምጪ ከሆነው ዝቅተኛ አየር ግፊት ጋር አገናኝቶታል፡፡
አነዚህ አብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት ሜዲትራኒያን የተባለው ሞቃትና ቀዝቃዛ የአየር ክልል የሚገኙ እንደመሆናቸው ከፍተኛ የዝናብ ጊዜያቸውም አሁን የምንገኝበት ጸደይና ቀጣይ በጋ ወቅት ነው፡፡
በእንዲህ ዓይነት ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2021፤ 185 ሰዎች በአስከፊው አደጋ ሲሞቱ በሮማኒያ በ1974 209 ሰዎች ሞተዋል። በፖርቹጋል በ1967 500 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት አልፏል ሲ.ኤን.ኤን እንዳስታወቀው። የሰሞንኛው አደጋ በተመለከተ 4 ሺህ 607 ሰዎች ህይወት በሀገሪቱ መከላከያ አማካይነት መትረፉንም አስታውቋል፡፡
የህይወት አድን ተግባሩ እየተከናወነ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ጠቅላላ የሟቾች ቁጥር ከ200 በላይ ሆኗል ብሎ የዘገበው ዘ ጋርዲያን ተብሎ የሚታወቀው የዜና ምንጭ ሲሆን በሀገሪቱ ዘመናዊ ታሪክ በጣም አሳዛኝ በማለትም ገልጾታል፡፡
ደቡብ ምሥራቅ ኤሲያ ሀገራት፣ አሜሪካና የእኛው አፍሪካ ጨምሮ እየጣለ ከነበረው ዝናብ መጠኑ በእጅጉ ልቋል የተባለለት ውርጅብኝ በታሪክ ከፍተኛ ሆኖም የተመዘገበ ነው እስከ 180 ሚሊ ሜትር ሁሉ በመምታት። ይህንን ብዙ ተንታኞች “አመታዊ ዝናብን በ8 ሰዓታት ብቻ”¡ በማለት በአግራሞት ገልጸውታል፡፡
እስከዚህኛው ሳምንት ድረስ በሀገራችን እየጣለ ከቆየው ዝናብ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሆኖ የታየው ዝናብ በሀገሪቱ ደቡብዊና ምሥራቃዊ ክፍሎች ላይ ጉልበቱን ያሳረፈ ሲሆን በዚህም በስፔን እግር ኳስ ስሟ ጎልቶ የምትታወቀው ቫሌንሲያ ከተማ ሰለባ መሆን ችላለች፡፡
ይህንን ሁኔታ ዘ ጋርዲያን ሲዘግብ የሟቾቹ ቁጥር 205 መድረሱን አስታውቆ ድልድዮችን፣ መኪኖችን እና የመንገድ መብራቶችን ሁሉ ጠራርጎ እንደወሰደ ነው ያስታወቀው። በሺዎች የሚቆጠሩትን ካለ ውኃ እና ምግብ ማስቀረቱን አስታውቆ መንገዶችም በቆሙ መኪኖች እና ቤት ፍርስራሾች እንዲዘጉ አድርጓል ብሏል፡፡
ሌሎች ካለምንም የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቅረታቸውና የሚመገቡበት ምግብም ሩቅ ያሉ ዘመዶቻቸው አምጥተው መብላታቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
በዚህ ሁሉ ውጣውረድ መንግሥት አፋጣኝ የድጋፍ ሥራ አልሠራም በሚል ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች የሚነሳው ወቀሳ ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ ያወረደው ሲሆን አንዳንድ የአካባቢ አስተዳደሮች በበኩላቸው የአደጋውን ቅጽበታዊነት መግለጻቸው በአሁኑ ጊዜ ከተሻሻለው የአየር ትንበያ ዕውቀት ጋርም መጣጣሙን ማመዛዘን ይቻላል፡፡
አልጀዚራም በ10 ዓመታት በአውሮፓ የተከሰተ አስከፊ የአየር ሁኔታ ጉዳት በማለት ሲገልጽ በሀገሪቱ እ.ኤ.አ ከ1970 ወዲህ ታይቶ ያለማወቁን ነው ያስታወቀው፡፡ መንገዶች፣ የባቡር ሀዲዶችና ድልድዮች መሰባበራቸውን ሲጠቁም ለዚሁም ውኃ ከወንዞች እየሞላ መውጣቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክቷል።
ዩሮ ኒውስ የተባለው ዜና ምንጭ በበኩሉ ዝናቡ መንገዶችን ወደ ወንዝነት እንደቀየረ ሲያመለክት ከአደጋው ለመከላከል 1ሺህ 700 ወታደሮች ወደ ቦታው መመደባቸውንም ነው ያስታወቀው፤ ክስተቱን ከትልቅ ሀሪካን ወይም ሱናሚ ጋር በማመሳሰል፡፡ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባም 500 የሚሆኑ ጦር ሠራዊት አባላት ለድጋፍ መሠማራታቸውን አብራርቷል የነፍስ አድን ተግባሩ እጅግ አድካሚ በሆነበት አግባብ፡፡
ከሁለት ሳምንታት ለማያንስ ጊዜ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጉዳት እንዲሁ ሀገሪቱን በብዙ መልክ የጎዳትና መልሶ ግንባታውንም አስቸጋሪ የሚያደርግባት ሲሆን እንዲህ ዓይነት ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች በሚከሰቱ ጊዜም ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት አብሮ መሥራት የሚችሉበትን አስፈላጊነት ጠቁሞ አልፏል፡፡
በርካታ የአየር ንብረት ክስተቶች ከአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች እንደሚነሱ ባለሙያዎች እየገለጹ ያሉበት ሂደት በአንድ በኩል ትክክለኛ መፍትሄ ጠፍቶ የጉዳቶች መጠን እየጨመረ መምጣት የወደፊት ኑሮን ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በዓለም ከተገታ ወዲህ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መጀመርና እንዲሁም ያስከተለው የማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከአቅም በላይ ነው፡፡ ይህ አልፎ አልፎ ከሚደርሰው የተፈጥሮ አየር መዛባት ጋር ሲጣመር ውጤቱ ምን እንደሆነ ማንም መገመት ይችላል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ