ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ይደረግ
በገነት ደጉ
በኢትዮጵያ የግብርና ሥራ በሁለት ዋና ዋና ወቅቶች የተከፈለ ነው፡፡ በበልግና በመኸር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበጋ ወቅት የመስኖ ስራ ሌላው የግብርና ስራ ሆኖ ቀጥሏል።
ግብርና የሀገር ዋልታና ማገር መሆኑን የተገነዘበው መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተግቶ እየሰራ ይገኛል። የዘርፉ ተዋንያንም ለአርሶ አደሩ መረጃ በማድረስ፣ ቴክኖሎጂ በማቅረብ፣ ሙያዊ ምክር በመስጠትና የተለያዩ የድጋፍ ስራዎችን የማቅረብ ሥራንም ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትና የግብርና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ሰሞኑን ከሰጡት መግለጫ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።
ከዚህ ወር ጀምሮ ያለው የአየር ትንበያ በደረሱ ሰብሎች ላይ እና በጤናው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተግዳሮት እና ተያያዥ ጉዳዮች ከማዕከሉ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ምዕራብ አና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው አየለ እንዳሉት በበጋ ወቅት እስከ ህዳር አጋማሽ ከቀላል እስከ መደበኛ ዝናብ ሊኖር ይችላል፡፡
የጥቅምት ወር ዝናብ በአብዘኛው ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ከመደበኛው በላይ ከመዝነቡ ጋር ተያይዞ እድገት ላይ ባሉ ሰብሎች እና ለአጨዳ በደረሱ ሰብሎች ላይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦም ሆነ ተፅዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ቀናቶች ከባድ ዝናብ የተመዘገበ ሲሆን አብዛኛው ጣቢያዎች ላይ ከመደበኛው በላይ ከባድ ዝናብ መመዝገቡን ኃላፊው ጠቅሰው አልፎ አልፎም አደጋዎችም መከሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ለግጦሽ ሳር እና እድገት ላይ ላሉ ሰብሎች ጥሩ ቢሆንም እድገታቸውን ለጨርሱ ሰብሎች ግን ጉዳት እንዳለው ጠቁመዋል። በቀጣይ ሳምንትም በአብዛኛው ሲዳማ ክልል ዝናባማ እንደሚሆንና ሌሎች አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል፡፡
ይህንን ተከትሎ ማህበረሰቡ የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ መሰብሰብ እንዳለበትና በደቦ፣ ተማሪዎችንና እንዲሁም የሀይማኖት ተቋማትን በማስተባበር ከሚከሰት የምርት ብክነት መታደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለህብረተሰቡ ከማድረስ አንፃር ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ከፍያለው ማህበረሰቡም በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎችን በመከታተል ተግባራዊ በማድረግ ምርት መሰብሰብ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
ያሳለፍነው ወር የአየር ንብረት ክስተቶች ተፅዕኖ የሚገለፀው ወደ ፊት ነው ያሉት አቶ ከፍያለው ከባድ፣ መደበኛና እንዲሁም ከመደበኛው በላይ ዝናብ ያስተናገዱ አካባቢዎች ከጤና ጋር ተያይዞ ለወባ፣ ኮሌራ እና ሌሎች በሽታዎች ስለሚጋለጡ የጤናው ዘርፍ መረጃውን በአግባቡ በመውሰድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ህብረተሰቡ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን በማዳፈንም ሆነ በማፋሰስ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው ያሉት ሥራ አስፈፃሚው በቀጣይ ሳምንት የሚዘንበው ዝናብ የውሃ አካላት እንዲጨምሩ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
ካሁን በኋላ የቀሩት ወራቶች መደበኛ፣ ደረቅ እና ማለዳ ቅዝቃዜ የሚስተዋልባቸው ስለመሆኑ አስረድተው በዚህ ዓመት ከበድ ያለ የማለዳ ቅዝቃዜ ባይኖርም ህብረተሰቡ የራሱን አለባበስ ስርዓት ማስተካከል አለበት ብለዋል፡፡
በተለይም ደጋማ አካባቢዎች ላይ የማለዳው ቅዝቃዜ ጠንከር እንደሚል እና በእንስሳትም ላይ እስከ ህይወት ማጥፋት ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምርት መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የአደጋ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቅድመ መከላከሉ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በማዕከሉ የልማት ሚትዎሮሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ አንዱአምላክ ክፍሌ በበኩላቸው አሁን ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየታየ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ለአጨዳ ወይም ለመሰብሰብ የደረሱ ሰብሎች በስፋት በማሳ ላይ አሉ ያሉት ባለሙያው የምርት መበላሸት እንዳይከሰት በወቅቱ መታጨድ እንዳለበት ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጤናው በኩልም አስጊ ሁኔታዎች እየታዩ ስለመሆናቸው ያሳሰቡት ባለሙያው የሙቀት መጠኑ እየጨመረ በመሆኑ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይም ባለፉት ሳምንታት የዘነበው ዝናብ ውሃ አቁሮ መቀመጡን ያስረዱት ባለሙያው የሚመለከተው አካል ወባ ላይ ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ተረድቶ ከወዲሁ አስፈላጊ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ብለዋል፡፡
ለወባ ብቻ ሳይሆን ለውሃ ወለድ በሽታዎች ጭምር ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አውቀው የጤናው ሴክተር ከወዲሁ የቅድመ መከላከል ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
እስከ ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ ያሉት ባለሙያው ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም ለሰውም ሆነ ለእንሰሳት ምቾት የማይሰጥ ሙቀት ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ ከአየር ንብረቱ ጋር መላመድ እና ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል፡፡
ማዕከሉ መረጃዎችን በቴሌግራም፣ በፌስ ቡክ እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲሁም የኤሌትሮኒክስ ሚዲያዎችን በመጠቀም እያሰራጨ መሆኑን ያስታወቁት ባለሙያው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መረጃዎችን በአግባቡ ወስደው ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት እንዲሰጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“ኩርፊያ እና ንትርክ አልወድም” – ጋዜጠኛ ገናናው ለማ
በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም
ኮንፈረንስ ቱሪዝም