በኢያሱ ታዴዎስ
በአውሮፓዊያኑ 1960 የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ሊካሄድ ሰከንዶች መቁጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶች ቦታቸውን ይዘው በሰፊው የሮም ጎዳና ላይ ሰውነታቸውን እያፍታቱ በተጠንቀቅ የጅማሮውን ማብሰሪያ ድምጽ ለመስማት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
የወቅቱ የሶቪየት ሕብረት አትሌት ሰርጌ ፖፖቭ በአውሮፓ የተካሄዱ የማራቶን ውድድሮችን ደጋግሞ በማሸነፉ የሮሙንም ውድድር እንደሚያሸንፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል። አካላዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ተፎካካሪዎቹን ወደ ግራ ወደ ቀኝ እየገላመጠ የሚሰጠው የማስፈራሪያ መልዕክት አብረውት የሚሮጡትን ሁሉ ያሸበረ ነበር፡፡
በ10 ሺህ ሜትር እና በሀገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ደጋግሞ ድል የነሳው ሞሮኳዊው ራዲ ቤን አብድልሰላምም ሌላው ተጠባቂ አትሌት ነበር፡፡ የኒውዚላንዱ ቤሪ ማጊም ማራቶኑን እንደሚያሸንፍ ታምኖበት የተሰየመ አትሌት ነበር።
በአጠቃላይ ከ35 ሀገራት የተውጣጡ 69 አትሌቶች ወሳኙን ማራቶን ለመወዳደር የሮምን ጎዳና ወርረዋል፡፡ የተጠበቀው የማስጀመሪያ ተኩስ ድምጽ ሽቅብ ሲለቀቅ አደባባዩ ላይ ተሰማ፡፡ 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር ርቀት የሚጠብቃቸው አትሌቶቹ ወደ ፊት መምዘግዘግ ጀመሩ፡፡
በግራ በቀኝ እጭቅ ብለው የድጋፍ ጩኸት በሚያሰሙ ተመልካቾች ታጅበው መሮጣቸውን ቀጠሉ፡፡ እንደ ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ የተሰማሩት የሮም ጎዳናዎች ሯጮችን በፍጥነት እያንደረደሩ እርስ በእርስ ያፋትጓቸዋል፡፡
ሩጫው የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮችን ካስተናገደ በኋላ አረንጓዴ ጃፖኒ መሳይ መለያ በቀይ ቁምጣ የለበሰ አንድ ኢትዮጵያዊ አትሌት፣ በጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ የተዋበው አፕያ ጎዳና ከሙቀቱ ጋር ተደምሮ ምቾት ነስቶት ያጠለቀውን ጫማ ሲያወልቅ ተስተዋለ፡፡
1 ሜትር ከ77 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው አበበ ቢቂላ ጫማውን አውልቆ መሮጥ ሲጀምር የተመልካቹን ሁሉ ትኩረት ሳበ፡፡ በርካቶች ሩጫውን እንደማይጨርስ አምነው ነበር፡፡ ማራቶን አይደለም በባዶ እግር፣ ምቾት ባለው ጫማ እንኳን ሮጦ ለማሸነፍ እንደሚከብድ አልጠፋቸውም፡፡
ከባልደረባው አበበ ዋቅጂራ ጋር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሮጠው አበበ ግን በዓይነ ሕሊናው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ውልብ እያለበት መሮጡን ቀጠለ፡፡ ሩጫው ግለቱ ጨምሮ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት ሞሮኳዊው ራዲ ቤን አብድልሰላም እና አበበ ቢቂላ ለብቻቸው ተነጥለው አንገት ለአንገት ተናነቁ፡፡
የሮምም ሰማይ በሁለቱ ብርቱ ፉክክር ታጅቦ መጨለሙን አሳበቀ፡፡ ወዲያውም ሮም ባማሩ መብራቶች ተሞልታ ጨለማውን አሸንፋ ውድድሩን አስቀጠለች፡፡ ድብቅ በሚመስሉ አካባቢዎች ደግሞ የተቀጣጠሉ ችቦዎች ይበሩ ጀመር፡፡ በዚሁ በምሽቱ ድባብ አሁንም ፉክክሩ በሁለቱ አትሌቶች መካከል ሆኗል፡፡
ከዚያም አበበ ከራዲ ፊት ወጥቶ መምራት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁሉ ሩጫው ደክሟቸው ያቋረጡ፣ ቆም ብለው ውሃ የሚጎነጩና ብርቱ ድካም የሚስተዋልባቸው ሯጮች ብዙ ነበሩ፡፡ ምንም ድካም የማይታይበት አበበ ግን ጭራሽ ፍጥነቱን ጨምሮ ሮጠ፡፡
ከኋላ የሚከተለውን አትሌት በብዙ ርቀት እየመራ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደረሰ፡፡ ምንም ግምት ያልተሰጠው አበበ ቢቂላ አስደናቂ ፍጥነቱን አክሎበት አሸናፊነቱን የሚያበስረውን ገመድ በጥሶ ገባ፡፡ 2፡15፡16.2 የገባበት ሰዓት ነበር፡፡
አበበ ሩጫውን እንደጨረሰም አካላዊ እንቅስቃሴውን አላቆመም፡፡ በአሸናፊነቱ የተደመሙ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ከብበውት የፎቶግራፍ ብልጭታ ፊቱ ላይ ቢያሳርፉም ከምንም ሳይቆጥር ድካም በማይታይበት አካሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡
ድሉን የተመለከቱ ተመልካቾች ግን መታገስ አልቻሉም፡፡ አፈፍ አድርገውት ከአናታቸው በላይ ከሰቀሉት በኋላ፣ ጉሮ ወሸባዬን በራሳቸው ቋንቋቸው አዜሙለት፡፡ ውድድሩን በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዩት ጋዜጠኞችም “አበበ የተባለ ኢትዮጵያዊ አትሌት ማራቶንን በባዶ እግሩ ሮጦ አሸነፈ” ሲሉ ታሪክ ዝንተ ዓለም ይዘክረው ዘንድ በደማቁ ከተቡ፡፡
አበበ በኦሎምፒክ መድረክ ማራቶንን ያሸነፈ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ጥቁር አፍሪካዊ አትሌት ስለመሆኑ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ተበሰረ፡፡ ኢትዮጵያም በጀግና ልጇ ከአድዋውና ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ድል በኋላ ዳግም በሮም አደባባይ ዝናዋ ናኘ፡፡
በዚህ የደስታ ሀንጎቨር ውስጥ ስትዋኝ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ 4 ዓመታት ቆይታ ዳግም በ1964 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተከሰተች፡፡ በታሪክ ሰሪው አበበ ቢቂላ፣ ደምሴ ወልዴ እና ማሞ ወልዴ ተወክላለች፡፡
ሮም ላይ በባዶ እግሩ ድል የነሳው ጀብደኛው አበበ የቶክዮን ማራቶን ዳግም ያሸንፋል ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም፡፡ አበበ በኦሎምፒኩ ከመሰየሙ ከ40 ቀናት በፊት የትርፍ አንጀት ቀዶ ጥገና አድርጎ ነበር፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ቁስሉ ሽሮለት ወደ ልምምድ ተመልሶ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ በውድድሩ መሳተፉ በራሱ ከፈጣሪ የተቸረው ተዓምራት ነበር፡፡
የስፖርት ቤተሰቡ ለዚሁ የማራቶን ውድድር ተሳታፊ ከነበሩት 68 አትሌቶች መካከል የማሸነፍ ቅድመ ግምት ከሰጣቸው አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ አበበ ቢቂላ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በ1963 በጃፓን በተካሄደው የቤፑኦይታ ማራቶን ውድድር የራሱን የአበበን ክብረ ወሰን ጭምር በማሻሻል ያሸነፈው ጃፓናዊው ቶሩ ቴራሳዋ ነበር ለአሸናፊነት በቀዳሚነት የታጨው፡፡
በሌላ በኩል በ1963 በለንደን በተካሄደው የፖሊቴክኒክ ማራቶን ዳግም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ አሸናፊ የሆነው አሜሪካዊው ሊዮናርድ ኤደሊን ለአሸናፊነት ተገምቷል። ከሊዮናርድ ኤደሊን በ1964ቱ የፖሊቴክኒክ ማራቶን ክብረ ወሰን ነጥቆ ለግሉ የጨበጠው የታላቋ ብሪታኒያ አትሌት ባሲል ሂትሊም ተጠባቂ ነበር፡፡
ውድድሩ በቶኪዮ ታላቁ ጎዳና ስለመጀመሩ የሚያበስረው ተኩስ ሲሰማም አትሌቶቹ ቦታቸውን ይዘው ሩጫቸውን ጀመሩ፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያ የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ያገኘው ይኸው የማራቶን ውድድር፣ ካሜራው ለእይታ ሲቀርብ ደጋግሞ ያሳይ የነበረው የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኙትን ነበር፡፡ አበበ ግን ከእነዚህ መካከል አልነበረም፡፡
የሆዱን በሆዱ ይዞ ጥርሱን ነክሶ የሮጠው አበበ እንደ ልማዱ ኪሎ ሜትሮች በጨመሩ ቁጥር ከመሪዎቹ ተርታ በመሰለፍ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጉን ተያያዘ፡፡
ውድድሩ 4 ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት የደከመው እና ምቾት ያልተሰማው እያቋረጠ፣ ሩጫውን ለመጨረስ እልህ የተናነቀው ደግሞ እየቀጠለ ይካሄድ ያዘ፡፡ የሮሙ ኦሎምፒክ ልማደኛው አበበ ግን ብቻውን አፈትልኮ ወጥቶ ያለመታከት ይሮጣል፡፡
በዚሁ ፍጥነት ሩጫውን ካስቀጠለ በኋላ 2፡12፡11.2 በመግባት ውድድሩን በአሸናፊነት ደመደመ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የገባበት ሰዓት አስቀድሞ የታላቋ ብሪታኒያ አትሌት ባሲል ሂትሊም የጨበጠውን ክብረ ወሰን የግሉ ማድረግ ያስቻለው ነበር፡፡
ሩጫውን በበላይነት ማጠናቀቁ ከተረጋገጠ በኋላ የእሱ ብቻ ባህል ተደርጎ የሚወሰደውን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረጉን ቀጠለ፡፡
ይሄኔ በሮሙ ተዓምር የተገረሙ ተመልካቾች እና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ተዓምራቱ በጃፓኗ መዲና ሲደገም ሲመለከቱ ዝም ማለት አልቻሉም። ቶኪዮን በአድናቆትና በጭፈራ በአንድ እግር አቆሟት፡፡ ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ ተመልካቾችም በቶኪዮ ስቴዲየም በአካል የተገኙ ይመስል በመስኮቱ የሚንጸነባረቀውን የአበበን ምስል እየሳሙ በፈንጠዝያ ተሞሉ፡፡
ዓለም ሁሉ አበበ ቢቂላን ደግሞ ደጋግሞ አነሳው፡፡ አበበ የሚለው ስም የጀግንነት መለያ ሆነ ልክ እንደ አንበሳ፡፡ የሮሙን የባዶ እግር ገድል በቶክዮ ከሕመሙ ጋር እየታገለ በቁርጠኝነት ሲደግም ዓለም አይቷልና “ኢትዮጵያ ታላቋን ጣሊያን ያሸነፈችበትን ምክንያት አሁን አወቅን፤ እንደ አበበ በጀግኖች የተሞላች አስደናቂ ምድር ናት” ሲልም ምስክርነቱን ሰጠ፡፡
ታዲያ እነዚህ ሁለቱ የአበበ ቢቂላ የኦሎምፒክ የማራቶን ድሎች ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ ይወራሉ፡፡ ከ1960 እስከ 1966 በሮጠባቸው 13 ዓለም አቀፍ ማራቶኖች 12ቱን ድል አድርጓል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በቅርቡ “ለአፈታሪክ የቀረበ ጀብድ” በሚል ርዕስ በይፋዊ ድረገጹ፣ የአበበ ቢቂላን በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለተከታታይ ማራቶንን ያሸነፈበትን ክስተት 60ኛ ዓመት አስመልክቶ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ዘገባው የዓይን እማኞችን አስተያየትም አካትቶ ክሽን፣ ምጥን ያለ አርቲክል ነበር ለአንባቢያን ያበቃው፡፡
ከእነዚህ የዓይን እማኞች አንዱ በወቅቱ በየሳምንቱ የሩጫ ውድድሮችን በጋዜጣ በመዘገብ የታወቀው የታላቋ ብሪታኒያ ጋዜጠኛ ሜል ዋትማን ነው፡፡ ጋዜጠኛው፡-
“አበበ ቢቂላን ማራቶን ሲሮጥ ማየት ለአፈታሪክ የቀረበ ጀብድ እንደማየት ነበር፡፡ እንዴት አንድ ሰው 26 ማይሉን በየ5፡2 ሰዓት እየሮጠ ሲጨርስ ምንም ዓይነት ድካም ሳይሰማው ጉልበቱ ሩጫውን ሲጀምር እንደነበረው ይሆናል? ሌሎቹ የርቀቱ ሯጮች ይህ ምስጢር እንደሚሆንባቸው አልጠራጠርም፡፡” ሲል ነበር ታሪካዊውን ጀብድ በአድናቆት በጋዜጣው የከተበው፡፡
የወቅቱ ሌላኛው የስፖርት ጸሃፊ አሜሪካዊው ጆን አሸርዉድ ከአበበ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ድል በኋላ ከስኬቱ ጀርባ ያለውን ምስጢር ይመለከት ዘንድ ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ነበር፡፡ አበበ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኝ ስፍራ የዕለቱን የጠዋት ልምምድ ለ2 ሰዓታት ካደረገ በኋላ ሲመለስ ያገኘዋል፡፡
ጆን አሸርዉድ ከቶኪዮ ማራቶን ድል በኋላ፡- “አበበ ሩጫውን ከጨረሰ ወዲህ አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተመልክቼ ‘ምንም ላብ አላሰመጠውም፣ ቁናቁና አይተነፍስም፤ ድካምም አይታይበትም’ ብዬ አስቤ ነበር፡፡” ብሎ ነበር የጻፈው፡፡
ታዲያ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የዚህ ምስጢሩ ምን ይሆን ብሎ የጓጓለትን ጥያቄ መልስ ያገኝ ዘንድ ያስስ ጀመር፡፡ በኋላም ላይ የተረዳው ነገር ቢኖር የአበበ ብርታትና ጥንካሬ በተፈጥሮ የተለገሰው አለመሆኑን ነበር፡፡ ከስኬቱ ጀርባ ትውልደ ስዊድናዊው አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን እንዳለበት ነው፡፡
አሰልጣኙ ለስፖርት ጸሃፊው አሸርዉድ የነገረውን እውነታ አሸርዉድ ሲጽፈው እንዲህ አለ፡-
“ከ1995 በፊት አበበን እምብዛም አላውቀውም ነበር፡፡ ለሮም ኦሎምፒክ ዝግጅት ሲያደርግ አሯሯጡ አዝጋሚ ነበር፡፡ በወቅቱ ዕድሜው 27 ነበር፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ብዙ ስጋት ነበረብኝ። ጭንቅላቱን በአግባቡ መሸከም አይችልም ነበር። ክንዶቹን እዚህም እዚያም ያበርራቸዋል። ሚዛኑ መጥፎ የሚባል ነበር፡፡ እሱን ለማሳመን በተደጋጋሚ በቁጣ አምባርቅበት ነበር፡፡
“ይሁን እንጂ እንደ እሱ በቆራጥነትና በመሰጠት የተሞላ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡ ሁሌም የሚያልመው አሸናፊነትን ነበር፡፡ ከእሱ ጋር የሚወዳደሩትን አትሌቶች እንኳን በቅጡ አያውቃቸውም፡፡ ክሌርክ ሆነ ሂት፣ አሊያም ኤደሊን ለእሱ በቃ ስሞች ብቻ ናቸው፡፡”
ተፎካካሪዎቹን ስላለመፍራቱ አበበ ራሱ ለአሸርዉድ “ማንንም አልፈራም፡፡ አብሬ የምወዳደራቸውን አትሌቶች ስምም ሆነ ፊታቸውን ማወቅ አያስፈልገኝም፡፡” ሲል አረጋግጦለታል፡፡
እርግጥም አበበ በደረሰበት የመኪና አደጋ ምክንያት ከሩጫ እስኪ ገለል ድረስ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ሁሉ ስኬታማ የመሆኑ ምክንያት ቆራጥነቱ፣ የድል ረሃብ እና ደፋርነቱ እንደ ነበር ያዩት ሁሉ በዘመኑ መስክረውለታል፡፡
ይህ ጀግና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁሮች ሁሉ ኩራት ሆኖ እስካሁን ድረስ የዘለቀው አርዓያነቱ የተለየ አትሌት ያደርገዋል፡፡ አበበ ቢቂላን የወለደው የኢትዮጵያ ማህጸንም፣ ማሞ ወልዴን፣ ምሩጽ ይፍጠርን፣ ሃይሌ ገብረስላሴን፣ ቀነኒሳ በቀለንና ሌሎች አያሌ ጀግኖችን ሳይነጥፍ ወልዶ ዓለምን አስደምሟል። ቀጣይ ጀግኖችንም እንዲሁ እንጠባበቃለን…
More Stories
ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ይደረግ
“ባንሄድ ይሻላል”
“ህሊናን አሳምነው ከሰሩ ሁሉም ስራ ቀላል ነው” – ወ/ሮ ሮማን አጥናፉ