በመለሠች ዘለቀ
በአስተሳሰብ ስሜት እና በተግባር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር፣ ሀዘን ውስጥ የሚከትና ተስፋ የሚያስቆርጥ ስሜት በሰዎች ላይ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ በነገሮች ባለመደሰት፣ ተስፋ በመቁረጥ እንዲሁም በተለያዩ ሀዘን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ሰዎች በድብርት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
በአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ መሠረት፣ በአለም ላይ ከ264 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድባቴ ይጠቃሉ። ድባቴ በማንኛውም ሰው ላይ ማለትም ዕድሜ፣ ዘር፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የትምህርት ደረጃን ሳይለይ ሰዎችን ሊያጠቃ የሚችል የአእምሮ ህመም አይነት ነው፡፡ በዚህ ስሜት የተነሳ ብዙ ወጣቶች በዘመናዊ ቋንቋ “ብንሄድ ይሻላል” እያሉ በለጋ እድሜያቸው ራሳቸውን ሲያጠፉ መስማት እየተለመደ መጥቷል።
የእንደዚህ አይነት የስሜት መቃወስ ምክንያቶች እና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ የዘርፉን ባለሞያዎች አነጋግረናል።
“የድባቴ ህመም ከአእምሮ ህመም አይነቶች አንዱ ነው” ይላሉ አቶ ሙሉቀን ግርማ በእፎይታ የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ማዕከል የስነ አእምሮና የስነ ልቦና ህክምና ባለሙያ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የድባቴ ህመም ከአእምሮ ህመም አይነቶች አንዱ ሲሆን ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ የቆየ የመደበር ስሜት ማለት ነው፡፡
ድባቴ ከተለመደው የስሜት ለውጥ እና በዕለት ተለት የህይወት ፈተናዎች ምክንያት ከምናሳየው የስሜት መልስ የሚከሰት የባህሪ ለውጥ ነው። ድባቴ በአንድ ሰው አስተሳሰብ፣ ስሜት እና በተግባር ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሀዘን፣ ገለልተኛነት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት መንፀባረቅ ነው፡፡
ድባቴ ደስታን በሚያመጡ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ማጣትን ያመጣል። የአንድን ሰው ሀሳቦች፣ ባህሪ፣ ተነሳሽነት፣ ስሜቶች እና ደህንነትንም ይለውጣል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያ አቶ ሙሉቀን፡፡
ድባቴ ያጋጠማቸው ሰዎች የመጥፎ ስሜትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ ይህም በአንድ ሰው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ ከፍ ሲልም ራስን የማጥፋት ሀሳቦችን ሊያስከትል ይችላል።
የድባቴ ምልክቶችን አቶ ሙሉቀን ሲገልጹ፣ የድብርት ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በብዙ ሰዎች ሊታዩ የሚችሉ የተለመዱ ምልክቶች አሉ፡፡
እነዚህም ሀዘን፣ ጭንቀት ወይም የባዶነት ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ /ጨለምተኝነት፣ ያልተገባ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጥቅም አልባነት፣ ረዳት አልባነት ስሜት፣ በፊት የሚወዱት እና የሚደሰቱበት ነገር ላይ ፍቅር መቀነስ ወይም መጥላት፣ ድካምና የሃይል ማነስ፣ የትኩረት ማነስ ወይም አለማስተዋል፣ የእንቅልፍ እጦት ወይም ከልክ በላይ ማንቀላፋት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የክብደት ለውጥ፣ ስለ ሞት ወይም እራስን ስለ ማጥፋት ማሰብ ወይም ራስን ለማጥፋት መሞከር፣ ራስ ምታት ህመም፣ ድካም እና ትክክለኛ የሆነ አካላዊ ምክንያት የሌለው ወይም በህክምና የማይድን የምግብ መንሸራሸር ችግር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ምልክቶች ውስጥ ቢያንስ አምስት ምልክቶች ሲታዩ ድባቴ ህመም ይባላል፡፡ ይህም በግለሰቡ ማህበራዊ ህይወትና በስራ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ቢያንስ ለሁለት ሳምንት ያክል ጊዜ ከታየ የባለሙያ እርዳታ መጠየቅ ተገቢ ነው። በማንኛውም ጊዜ ራስን የመጉዳት ወይም ራስን የማጥፋት ስሜት የሚሰማ ከሆነ በአስቸኳይ የስነ ልቦና ወይም የህክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል።
የድባቴ ህመም መንስኤዎችን ሲገልጹ፤ ለችግሩ ይሄ ነው የሚባል መንስኤ ባይኖርም አጋላጭ ምክንያቶቹ አሉ፡፡ እነዚህም ከስነ-ልቦና፣ ከማህበራዊ እና ከስነ -ህይወታዊ አንጻር ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
ከስነ-ልቦና አንጻር አስጨናቂ የሕይወት ክስተቶች፣ አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜታዊ በደሎች፣ ለአካባቢያችን እና ለራሳችን ያለው አመለካከት ያልተስተካከለ መሆን፣ የደረሰብንን ችግር ማሸነፍ ሲያቅተን ሊከሰት የሚችል አይነት ነው፡፡
ከስነ- ህይወታዊ አንጻር ከወሊድና ከህመም ጋር፣ የተወሰኑ የህክምና መድኃኒቶች ማለትም ለካንሰር፣ ለልብ ህመሞች የሚወሰዱ መድሀኒቶች፣ እናት ወይም ወላጆች ድብርት ካለባቸው ልጃቸው የመያዝ እድሉ ይጨምራል፡፡
ከማህበራዊ ጉዳዮች አንጻር ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት መቀነስ ወይም ደጋፊ ሰው ማጣት፣ አካባቢያዊ አስጨናቂ የልጅነት ገጠመኞች፣ የብቸኝነት ስሜት መሰማት፣ አንድ ሰው ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞቹ ጋር የማይገናኝ ከሆነ ወይም ከቤተሰቡ ጋር ጊዜ የማያሳልፍ ከሆነ ወይም ቤተሰብ ከሌላው ሊከሰት የሚችል የድባቴ አይነት ነው፡፡
ድባቴ የሚከሰተው በአማካይ ከ20 እስከ 50 ባሉ የእድሜ ክልል ውስጥ ነው፡፡ የህመሙ መንስኤዎችን መሰረት በማድረግ የተለያዩ አይነት ህክምናዎች የሚሰጡ ሲሆን በአብዛኛው ውጤታማ የሚባለው የመድሃኒትና የንግግር ህክምና በአንድ ላይ ሲሰጥ ነው ይላሉ የስነ-ልቦና ባለሙያው፡፡
ማዕከሉ እንደዚህ አይነት ችግር ላጋጠማቸው ታካሚዎች የስነ-ልቦናና የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት ባለሙያው የመድሃኒት ህክምና የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ወደ ጤና ተቋማት እንደሚልኩ ነው ያብራሩት፡፡
በአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል የስነ አእምሮ ህክምና ባለሙያ ሩሃማ ጌታሁን በበኩላቸው ድባቴ ወይም ዲፕሬሽን ማንኛውም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል የአእምሮ ጤና ህመም እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህም ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ የድብርት ስሜት ወይም ከዚህ ቀደም በሚያስደስቱን ጉዳዮች ላይ ፍላጎት በማጣት ይገለፃል።
ይህ ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱት የተለመዱ የስሜት መለዋወጥና መረበሽ የተለየ ነው። ድባቴ የሚፈጠርባቸው ጊዜያት በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ማለት ይቻላል ወይም በየቀኑ ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት ይቆያሉ።
ድባቴ ያጋጠማቸው ሰዎች የተረበሸ እንቅልፍ (እንቅልፍ ማጣት ወይም መብዛት) እና የምግብ ፍላጎታቸው ሊለወጥ (ማጣት ወይም መጨመር) ይችላል። ዝቅተኛ በራስ የመተማመን ስሜትም ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ራስን ስለ ማጥፋት ሀሳቦች እና ስለ ወደ ፊቱ ተስፋ ማጣት እንዲሁም ድካም እና ትኩረት ማጣት የተለመደ እና የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ድባቴ በማህበራዊ፣ በስነ-ልቦናዊ እና ስነ-ሕይወታዊ ምክንያቶች ውስብስብ መስተጋብር ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ በጦርነት፣ በከባድ ኪሳራ፣ የሚወዱትን ሠው ማጣት ወይም በሌሎች አሉታዊ ክስተቶች የኖሩ ሰዎች የድብርት ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል። በትምህርት ቤት እና በሥራ ላይ ያሉ ችግሮች ድባቴ ሊያስከትሉ ይችላሉ።
እንደ ባለሙያዋ ገለጻ በአለም አቀፍ ደረጃ 5 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በድብርት ይሰቃያሉ። የድባቴ ሕመምን ለመከላከል ውጤታማ የሆኑ ሕክምናዎች ቢኖሩም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት ሕክምና አያገኙም።
ለውጤታማ እንክብካቤ እንቅፋት የሚሆኑትም በአእምሮ ጤና እንክብካቤ ላይ ትኩረት አለመስጠት፣ የሰለጠኑ የጤና አጠባበቅ አቅራቢዎች እጥረት እና ከአእምሮ መታወክ ጋር የተያያዘ ማህበራዊ መገለል ናቸው።
ከዚህ በፊት ያስደስታቸው የነበረውን እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ለመቀጠል መሞከርና፣ ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን ቋሚ የሆነ የአመጋገብና የእንቅልፍ መዛባት ሲኖር የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን ማግኘት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ስነ አእምሮ ባለሙያዋ ለዲፕሬሽን/ድባቴ/ ውጤታማ ህክምናዎች አሉ። እነዚህም የስነ-ልቦና ህክምና (የንግግር) እና መድሃኒቶችን ያካትታሉ። በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ይህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው “ብንሄድ ይሻላል” ብለው ራሳቸውን ለማጥፋት ከመወሰን ይልቅ ወደ ሞት “ባንሄድ ይሻላል” ብለው ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ