በገነት ደጉ
የዛሬዋ እቱ መለኛችን ከወትሮው ለየት የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም ወትሮ ለወንዶች ብቻ ተለይቶ እንደተሰጠ የሚታመን ስራ ላይ መሰማራታቸው ነው፡፡
አሁን ላይ ልክ እንደ እቱ መለኛችን ሁሉ ሴት እህቶቻችን ከዚህ ቀደም የማይደፈሩ ስራዎችን እችላለሁ ብለው ደፍረው በመግባት ውጤታማ መሆናቸውን ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ወ/ሮ ሮማን አጥናፉ ይባላሉ፡፡ ትውልድና እድገታቸው ከይርጋለም ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ልዩ ስሙ ቤራ የሚባልበት አካባቢ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ነዋሪነታቸው ደግሞ በሀዋሳ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው፡፡ የተሰማሩበት ስራ ያገለገሉ ዕቃዎች ንግድ (በቆራሊዮ) ላይ ነው፡፡
ወ/ሮ ሮማን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በቤራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር የተከታተሉት፡፡
ከ8ኛ ወደ 9ኛ ክፍል ከተዛወሩ በኋላ በቤራ ከ8ኛ ክፍል በላይ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ይርጋለም ከተማ መጥተው እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ተከታትለው በ2009 ዓ.ም ማጠናቀቃቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በልጅነታቸው ሩጫ ይሞክሩ ነበር፡፡ ከሩጫ ልምምድ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ተጠልፈው ወደ ትዳር ዓለም መግባታቸውን ነው ያስታወሱን፡፡
የአንዲት ሴት እና የሁለት ወንድ ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሮማን፣ ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ከትዳር አጋራቸው ጋር እንጀራ ፍለጋ ወደ ሚዛን ተፈሪ ከተማ ለመሄድ ተገደዱ፡፡ ለ16 ዓመታት ያህል በሚዛን ተፈሪ ኖረዋል፡፡
ልጆቻቸውን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንጀራ እና አምባሻ በመጋገር ኑሮአቸውን ሲመሩም ቆዩ፡፡ በዚህ መሃል ግን ከትዳር አጋራቸው ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ከ16 ዓመታት የትዳር ቆይታ በኋላም ከትዳር አጋራቸው ጋር ተለያዩ። ከዚያም ወ/ሮ ሮማን ሁለቱ ልጆቻቸውን፣ እንዲሁም ሶስተኛዋን ልጅ የስድስት ወር ነፍሰጡር ሆነው ወደ ሀዋሳ መጡ፡፡
ወደ ሀዋሳ ከመጡም በኋላ ልጆቻቸውን ለማሳደግ በመቸገራቸው ወደ ቀበሌ በመሄድ የደሃ ደሃ በመባል በሴፍትኔት ፕሮግራም ይረዱ ጀመር። በወቅቱ ለልጆቻቸው የሚመግቡት ምንም እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡
የኑሮው ፈተና ሲከብዳቸውም የመንግስት ስራ አስቀጥሩኝ በማለት ሴቶች እና ህፃናት ቢሮን ደጅ ጠኑ፡፡ በቢሮው አቤቱታቸውንና የደረሰባቸውን ጉዳይ ቢያሳውቁም የትምህርት ማስረጃቸውን ሚዛን ተፈሪ ጥለው በመምጣታቸው፣ ምንም ዓይነት የትምህርት ማስረጃ ሳይኖራቸው መቀጠር እንደማይችሉ ተነገራቸው፡፡
በወቅቱ ሶስተኛ ልጃቸውን መውለጃ ጊዜያቸው ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ መሃል መልካም አጋጣሚ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ የከተማው ሴቶችና ህፃናት ቢሮ “እርዳታ ይሰጥሽ ወይስ ስራ መስራት ይሻልሻል?” የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ እሳቸውም “እርዳታ ለአጭር ጊዜ ነው፤ ስራ ብትሰጡኝ ግን ልጆቼን ማሳደግ እችላለሁ” የሚል ምላሽ በመስጠታቸው ቢሮው ከግብረሰናይ ድርጅት ጋር አጣምሮ አነስተኛ ስራ እንዳስቀጠሯቸው ይናገራሉ፡፡
“በወቅቱም ስራውን እንጂ በሆዴ ውስጥ የነበረውን ጽንስ አላስተዋልኩም ነበር” ያሉት ወ/ሮ ሮማን፣ ለአንድ ወር ስልጠና በመውሰድ በማህበር ተደራጅተው በሻይ ቡና ስራ ተሰማሩ፡፡ ከዚያም ሶስተኛ ልጃቸውን በሰላም ተገላገሉ፡፡
ሶስተኛ ልጃቸውን በወለዱ በስምንተኛ ቀናቸው ከችግራቸው አንፃር ወደ ስራቸው ለመመለስ ተገደዱ፡፡
በማህበሩም ሰብሳቢ በመሆን ሻይ ቡናውን በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ ከቆዩ በኋላ ሁሉም ሰው እርሳቸውን ብቻ እየጠበቀ ብዙም ውጤታማ ባለመሆናቸው ማህበሩን ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡
በዚህም ምክንያት ከማህበሩ ራሳቸውን በማግለል ብቻቸውን ሻይ እና ቡና እንዲሁም ቁርሳቁርስ ማቅረባቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ሮማን፣ ቀስ በቀስ ውጤታማ እንደሆኑ ነበር ያስታወሱት፡፡
በወቅቱ በሀዋሳ ከተማ የኮሮና ገበያ ተብሎ በሚጠራው ገበያ ውስጥ ትንሽዬ ሸራ በመዘርጋት ነበር ስራቸውን ይሰሩ የነበሩት፡፡ ሻይ ቡናቸውን ሰዎች ወደው መጠቀማቸው ለስራው እጅግ ያገዛቸው ሲሆን ከለመደላቸው በኋላም ገበያው ከዚያ ቦታ መነሳቱን አጫውተውናል፡፡
ስራ በመስራት ሰዎች መቀየር እንደሚችሉ የሚያምኑት ወ/ሮ ሮማን፣ ተስፋ ባለመቁረጥ ሌላ ስራ መፍጠር እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡
በሻይ ቡና የቆጠቡትን ትንሽዬ ገንዘብ የሲሚንቶ ካርቶኒ በየቦታው ተንቀሳቅሰው በሶስት ብር ገዝተው 12 ብር በማስረከብ ወደ ሌላኛው የንግድ ምዕራፍ ተሸጋገሩ፡፡
ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉት እኚህ ወ/ሮ፣ በ2014 ዓ.ም ለሰዎች ከማስረከብ ይልቅ ራሳቸው ለመስራት በማሰብ በቆራሊዮ ንግድ ስራ መሰማራታቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
ወ/ሮ ሮማን ምንም ዓይነት ነገር ሳይገድባቸው ሁለቱ ወንድ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እስኪሄዱ ማለዳ ከ12 ሰዓት ጀምሮ ማዳበሪያ አስይዘው ለውሃ ኮዳ ለቀማ እንደሚልኳቸው ተናግረው፣ የውሃ ኮዳውን አዲሱን በአንድ ብር በመሸጥ አሮጌውን ለማስረከብ ያስቀምጡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ድካማቸውንና ታታሪነታቸውን ያየ አንድ ግለሰብ አዲሱ ገበያ ቀበሌ መስሪያ ቦታ ሲሰጣቸው ግማሹን አካፍለው መኖሪያቸውን እዛው አደረጉ፡፡
“ከሰሩ እና ከለፉ ችግር ያልፋል“ የሚሉት ወ/ሮ ሮማን፣ ሴት ልጅ በቤት ውስጥ ቁጭ ከምትል እና የባሏን እጅ ከምትጠብቅ ጠንክራ በመስራት ራሷን እንደምታሻሽል መወሰን አለባት” ሲሉም መክረዋል፡፡
“ለመጀመሪያ ጊዜ ‘እድር ግቢ’ ተብሎ እድር መግባት የቻልኩ ቀን እጅግ ሀሴት አድርጌ ነበር። እኔም መኖር እንደምችል እና ልጆቼንም ማኖር እንደምችል ለራሴ ቃል የገባሁበትም ቀን ነበር” በማለት በሕይወታቸው ደስታ የተጎናጸፉበትን ቀን ያስታውሱታል፡፡
ዛሬ ላይ ከልጆቻቸው አልፈው ለአራት ልጆች የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ራዕይ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ነገን ማየት እና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያለሙ ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡
አሁን ላይ ወደ አዲስ አበባ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሲሚንቶ ካርቶን እና የውሃ ኮዳዎች በአይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሞልተው ይጭናሉ፡፡ ከአንድ ሊትር እስከ ሀያ ሊትር ባዶ ጀሪካን በየሰፈሩ ዞረው በመግዛት እና ቸርችረው በመሸጥም የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ህይወት የተሻለ ማድረግ ችለዋል፡፡
የእያንዳንዳቸው ዕቃ እዚሁ በኪሎ ተመዝኖ ስለሚጫን ከወጪም ሆነ ከእንግልት ለመዳን ከመሰል ጓደኞቻቸው ጋር አዲስ አበባ ተራ በተራ እንደሚሄዱ አጫውተውናል፡፡
“ስራው በእርግጥ ለሴት ከባድ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሴት እና ወንድ ተብሎ ተለይቶ የተሰጠ ስራ የለምና በስራው እጅግ ደስተኛ ነኝ” ይላሉ፡፡ ወ/ሮ ሮማን አይሱዙ ላይ ሲጭኑ እንኳን የጉልበት ሰራተኞች “የሮማን ነው ተዋት” እንደሚሏቸውና እርሳቸው ጋዋን ለብሰው መሰላል ላይ በመውጣት ሙሉ አይሱዙውን ልጆች እያቀበሏቸው እንደሚጭኑ ነግረውናል፡፡
“ስራ ራስንና ህሊናን አሳምነው ከገቡ ቀላል ነው” የሚሉት ወ/ሮ ሮማን፣ በተለይም መኪና ላይ ሲጭኑ ፎቶ የሚያነሱ፣ ተገርመው የሚያዩ እና ቪዲዮ የሚቀርፁ ብዙዎች ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡
ለሴቶች ዕቃ መጫን በሀገራችን የመጀመሪያ ባለመሆኑ ልጆቻቸውን ያስተማሩበት እና የእለት ጉርስ ያገኙበት በመሆኑ በስራቸው እጅግ እንደሚኮሩ አጫውተውናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የገበያ አድማሳቸውን ያሰፉ ሲሆን ልጆቻቸውን ጨምሮ ለሰባት ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ የቦታ እጥረት ባያጋጥማቸው ከዚያ በላይ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ነው የነገሩን፡፡
ወ/ሮ ሮማን ቤት ሁሉም ልጆች የየራሳቸው የስራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን ትንሿ ልጃቸው እንኳን ትምህርት ቤት እስክትሄድ ድረስ ቡና አፍልታ እና ምሳ ሰርታ በማቅረብ የራሷን አስተዋጽኦ ታደርጋለች፡፡
ቀጣይ እቅድዎስ ምንድነው? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሻቸው፡-
“የፈጣሪ ፈቃድ ቢሆን ያሳለፍኳቸው ጎዳናዎች ለብዙዎች አስተማሪ ናቸው፡፡ መስራት ለሚፈልጉ ሴቶች የስራ ዕድል መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡” የሚል ነበር፡፡ በቀጣይ የውሃ ኮዳውን መጨፍለቂያ ማሽን ለመግዛት ጠይቀው 2 መቶ ሺህ ብር ስለተጠየቁ ማሽኑን ለመግዛት አቅደው እየቆጠቡ ስለመሆናቸው ነው የገለፁት፡፡
ስራ እቀይራለሁ ብዬ አላስብም ያሉት ወ/ሮ ሮማን ሰፋ ያለ ጊቢ በመከራየት ስራውን ወደ ዘመናዊነት እና የሰውን ጉልበት በሚቆጥብ መልኩ ለመስራት አቅደዋል፡፡ በመሆኑም ሴቶች ስራ መስራት ከፈለጉ ሳይንቁ ቢሰሩ ዙሪያቸው ሁሉ ስራ እንደሆነም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ