“የሚስተዋለው እንግልት ደረጃ በደረጃ እየቀነስ መምጣቱን ማረጋገጥ ችለናል” – አቶ ሻፊ ሙዜ

“የሚስተዋለው እንግልት ደረጃ በደረጃ እየቀነስ መምጣቱን ማረጋገጥ ችለናል” – አቶ ሻፊ ሙዜ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ሻፊ ሙዜ ይባላሉ፡፡ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ከንቲባ ናቸው፡፡ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ እና የከተማዋን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

በደረጀ ጥላሁን

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሻፊ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ ለመነሻ እንዲሆነን ስለ ወራቤ ከተማ ይንገሩን!

አቶ ሻፊ፦ የወራቤ ከተማ ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እንደተቆረቆረች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የስልጤ ማህበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ ደመቅ እያለች ሄደች፡፡ በ1995 ዓ.ም ከተማዋ የዞን መቀመጫ ሆነች፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በፕላን እንድትመራ ተደረገ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች በመምጣት በ2007 ዓ.ም ከአጎራባች ወረዳዎች የተከለሉ ቀበሌያት ጨምራ ስፋቷ አሁን ላይ 15 ሺህ 722 ሄክታር ነው፡፡

ከተማዋ በሶስት ቀበሌያት የተዋቀረች ሲሆን የህዝብ ብዛቷ 100 ሺህ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ብዝሀ ሀሳብ የሚንጸባረቅባት እና የተለያዩ የእምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት ናት፡፡ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከክላስተር ከተሞች አንዷ ስትሆን የስልጤ ዞን መቀመጫም ናት፡፡

ንጋት፦ የከተማዋ መሰረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አቶ ሻፊ፦ በወራቤ ከተማ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነው ወራቤ ዩኒቨርስቲ ይገኛል፡፡ 22 ትምህርት ቤቶች በከተማዋ ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሶስቱ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ናቸው፡፡ በጤናው ዘርፍ ወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል እና ሁለት ጤና ጣቢያዎች ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቅርቡም አንድ ጤና ጣቢያ ለመጨመር እቅድ ተይዟል፡፡

በከተማዋ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት 35 በመቶ ሽፋን አለው፡፡ ይህ በቂ ስላልሆነ ከአለም ባንክ በተደረገ ድጋፍ እየተሰራ ያለ የውሀ ፕሮጀክት አለ፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተሰራ ሲሆን ሲጠናቀቅ ለሰላሳ አመታት ያህል የከተማዋን የውሀ ችግር የሚፈታ ይሆናል፡፡

የመንገድ መሠረተ ልማትን በተመለከተ÷ ለከተማዋ አማራጭ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለመስራት በተያዘው እቅድ መሰረት በዚህ አመት የሚጀመር 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፓልት መንገድ ለመስራት ዲዛይኑ ተጠናቆ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ ሌላ 30 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ ተሰርቷል፡፡ እንዲሁም 25 ኪሎ ሜትር የውሀ መውረጃ ቦይ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ንጋት፦ ከተማዋን በኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሻፊ፦ ወራቤ ካላት አቀማመጥና ለተለያዩ ከተሞች ባላት ቅርበት የተነሳ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ናት፡፡ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በከተማው በዋናነት የነበረው 10 የዱቄት ፋብሪካ ነበር፡፡ በዘርፉ ለምግብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከተማዋ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኗ አኳያ የኢንዱስትሪ ማእከል መገንባት አለብን በማለት 420 ሄክታር የኢንዱስትሪ መንደር ተመስርቶ ባለሀብቶች ገብተውበታል፡፡

ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሚያደርጋት ምክንያት አንዱ በዋናነት በቂ መሬት መኖሩ ነው፡፡ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ የተደረጉ 147 ፕሮጀክቶች ናቸው። ለዚህም ተጨማሪ 320 ሄክታር መሬት ፕላን ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚያ ውስጥ 194ቱ ፕላን ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ አሁን በእጃችን 300 ሄክታር መሬት አለ፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በራችን ክፍት ነው፡፡

በከተማዋ የፕላስቲክ ፋብሪካ ሥራ የጀመረ ሲሆን በምግብ ኮምፕሌክስ፣ የእንጨትና ብረት ውጤቶች እንዲሁም በከተማ ግብርና ጭምር የተሰማሩ አሉ፡፡ ከዚህ ሌላ አንድ የካናዳ ባለሀብት የአቡካዶ እና ማንጎ ጁስ ለማምረት ግንባታ እያካሄደ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በአጠቃላይ 30 ባለሀብቶች ግንባታ እያካሄዱ ሲሆን በእኛ በኩል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እያደረግን ነው፡፡ ለዚህም 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ፈንድ ተደርጎ መብራት ለማስገባት የመጨረሻውን ሥራ እየሰራን እንገኛለን፡፡

ንጋት፦ የከተማዋን የማዘጋጃ አገልግሎት ለማሻሻል ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሻፊ፦ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ አገልግሎት ቀደም ሲል ከሚሰጠው አገልግሎት በተሻለ መልኩ ተገልጋዩን ለማርካት የሚያስችሉ ሥራዎች ሰርቷል። ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የፋይሎችን ቁጥር እንኳን ለማወቅ እንቸገር ነበር፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ ማድረግ በማስፈለጉ ከባለፈው ግማሽ አመት በኋላ ተቋሙ ቴክኖሎጂውን ወደ ሥራ ማስገባት ችሏል፡፡

ከዚህ አኳያ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ይዞታዎችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ከሚያስችሉ ሥራዎች አንዱ አስቀድሞ በወረቀት /ሀርድ ኮፒ/ የነበረውን መረጃ ወደ ኮምፒውተር አሰራ ሂደት /ሶፍት ኮፒ/ የመቀየር ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህም በ1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር ሶፍት ዌር ከሚያበለጽግ ድርጅት ጋር ውል ተገብቶ ሥራ ተጀመረ፡፡ ለስራው የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በማሟላት ሶስት የሥራ ዘርፎችን ዲጂታል ማድረግ ችለናል፡፡ በዚህም 13 ሺህ ፋይሎችን ወደ ኮምፒውተር አሰራር ሂደት ለመቀየር አቅደን 10 ሺህ 400 ፋይሎችን ወደ ሲስተም ለማስገባት ተችሏል፡፡

ንጋት፦ ወደ ዲጂታል የተቀየሩ የሥራ ዘርፎች መመዘኛቸው ምን ነበር?

አቶ ሻፊ፦ በአብዛኛው የባለጉዳይ እንግልት የሚታይባቸው የሥራ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው የሚለውን በመለየት ነበር ወደ ሥራ የተገባው፡፡ ከዚህ አኳያ በአንደኛ ደረጃ የተለየው በመሬት ዘርፍ ሥር የሚገኙት የመሬት አስተዳደር፣ የመሬት ዝግጅት እና የመሬት ግብይት ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በግንባታ ፈቃድ እንዲሁም ሶስተኛው በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ላይ ሲሆን ይህም በተለይ በማዘጋጃ የሚሰበሰበው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ ስለማይታወቅ በዲጂታል ሲስተም ዘመናዊ በማድረግ ለተገልጋዮች ምቹ እንዲሆን የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ ቀደም ሲል ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የሚሰበሰበው በሌላ ተቋም የነበረ በመሆኑ የባለጉዳይን እንግልት የሚያቀል ሆኗል፡፡

ከዚህ ሌላ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡ ተገልጋዩ የመሬት ዘርፍ እና የኮንስትራክሽን ግንባታ ፈቃድን በአንድ ቦታ ላይ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። በአጠቃላይ ሶስቱ ዘርፎች ላይ ከሰኔ 30/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከወረቀት ነፃ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል፡፡ ለዚህም 3 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

ንጋት፦ ሥራዎቹን ዲጂታል ማድረጋችሁ ለተገልጋዮች ያለውን ፋይዳ ቢገልጹልን?

አቶ ሻፊ፦ የማዘጋጃ ቤት ሥራዎች ወሰብሰብ ያሉ በመሆናቸው ተገልጋዮች የሚጉላሉባቸው ናቸው፡፡ በተለይ ለሙስና የተጋለጡ ስለሆኑ ይህን አሰራር መቀየር አስፈላጊ ነበር፡፡ ተቋሙ አገልግሎቱን በማዘመኑ ተገልጋዮችን በቀላሉ ለማገልገል ይረዳዋል፡፡ ሌላው በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ የሙስና ችግርን ለመቅረፍ ይረዳል፡፡ ስራው በሲስተም በማለፉ ባለጉዳዩ የደረሰበት ሁሉ ለመቆጣጠር ስለሚቻል የሙስና ተጋላጭነትን ይቀንሳል፡፡

በመሬት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለው የአሰራር ብልሽት ተገልጋዩን የሚያማርር ነበር። ከአሰራርና ደንብ ውጪ መሬት ይተላለፋል÷ የሚል ግምገማ ነበረን፡፡ መሬት የመሬት ባንክ ውስጥ ሆኖ ነው መተላለፍ ያለበት። ቴክኖሎጂውን በመጠቀማችን የአሰራር ሥርዓቱ እየተስተካከለ መጥቷል፡፡ በተለይ ምን ያህል መሬት በባንክ እንዳለና ምን ያህሉ እንደተላለፈ በቀላሉ ማወቅ ስለሚያስችል ተቋሙን ከሌብነት የጸዳ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ለማሳያነትም የምንሰጠው የመሬት ማረጋገጫ ሰነድ የራሱ ባር ኮድ ያለው ስለሆነ ከተመሳሳይ የሰነድ ማጭበርበር ስጋት ነፃ ይሆናል፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀማችን የተገልጋይን እንግልት ያስቀራል፡፡ ከዚህ አኳያ ከቴሌ ጋር በመቀናጀት የተቋሙ መረጃዎች በሙሉ በቴሌ ሰርቨር /ክላውድ/ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ይህም የመረጃውን ደህንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ሌላ ባለሞያው የትም ሆኖ አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር እየተዘረጋ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ተገልጋዮች ቤታቸው ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተሰራ ሲሆን ይህም ደንበኛው ያለውን ሰነድ በኮድ ገብቶ የሚያረጋግጡበት አሰራር ነው፡፡

ንጋት፦ የተገልጋዮች ግብረ መልስ ምን ይመስላል?

አቶ ሻፊ፦ አብዛኛው ተገልጋዮች ለጉዳይ ሲመጡ ፋይሎቻቸው በቶሎ መገኘቱን በመልካም ጎኑ ያነሳሉ፡፡ በእኛ በኩል ዋና ፋይሎች ቴሌ እንደሚገኙ ለተገልጋዮች ገልጸናል፡፡ ስለዚህ መረጃዎች እንደማይጠፉ ይታወቃል፡፡ ይህም ፋይል ይጠፋብኛል የሚል ስጋት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በምንሰጠው አገልግሎት የሚስተዋለው እንግልት ደረጃ በደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን ማረጋገጥ ችለናል፡፡፡

በሌላ በኩል ይህን የቴክኖሎጂ አሰራር ሂደቱን ጠብቀው ለመገልገል የማይፈልጉ ጥቂት ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ጉዳይ ለማስፈጸም በሚል ከተገልጋዮች የሚጠቀሙ ጥቂት ደላሎች በዚህ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎት ባይኖራቸውም አብዛኛው ተገልጋይ ግን ተቀብሎ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡

ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሰለጠኑ ባለሞያዎች አሉ፡፡ በክልሉ ሥራን ቀድመን በመጀመራችን የዋንጫ ተሸላሚ ሆነናል፡፡

ንጋት፦ የካዳስተር አገልግሎት ምንድነው?

አቶ ሻፊ፦ ካዳስተር የከተማ መሬት መመዝገብና ማረጋገጥ የሚል ሀሳብን ይይዛል፡፡ ካዳስተር የራሱ የሆነ አሰራር አለው፡፡ የመሬት ዘርፍ የሚሰጠውን መብት ካዳስተር በማረጋገጥ ይመዘግባል፡፡ የከተማ መሬት ማረጋገጥ እና መመዝገብ በመመሪያው መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ ማፕ /ፕላን/ መሰራት አለበት፡፡ የመሬት ባለቤትነት መብት የተረጋገጠባቸው ቦታ ላይ በቀጠና እና በሰፈር ይሰራል፡፡ በአንድ ቀጠና ወይም ሰፈር የሚያረጋግጡ ባለሞያዎች አሉ፡፡ ለዚህም የራሱ ኮሚቴዎች ያሉት ሲሆን ይህን ሥርዓት ተከትሎ ነው የሚሰራው፡፡ እንዲሁም ታዛቢና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችም የተዋቀሩበት ነው፡፡

በዚህ መሰረት በከተማዋ 4 ሺህ ለሚሆኑ ግለሰቦች የመሬት መብት የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 900 መዝግበን የምስክር ወረቀት ወስደዋል፡፡ በዚህም ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ድረስ እናስከፍላለን፡፡

ንጋት፦ ተጨማሪ ሀሳብ ካለዎት እድሉን ልስጥዎት!

አቶ ሻፊ፦ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የሚታየውን መጉላላት ለማስቀረት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለህብረተሰቡ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ተገልጋዩ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ ማሟላት ያለበትን መረጃዎች በአግባቡ አሟልቶ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡

በሌላ በኩል ከተማዋ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የመሬት አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሟላት መዋእለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ዝግጁ መሆኗን እየገለጽኩ ወራቤ በቀጣይ የከተማዋ ብቻ ሳይሆን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ትልቁ የኢንዱስትሪ ማእከል ትሆናለች የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሻፊ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡