የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ አልሚ ባለሀብቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ አልሚ ባለሀብቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ

በምዕራብ ኦሞ ዞን በቤሮ ወረዳ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት በግል ባለሀብቱ አቶ ሪያድ ኡመር የተገነባው ዘመናዊ TAF የነዳጅ ማደያ ተመርቋል።

በምረቃው መርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳው አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በምረቃው ስነ-ስርአቱ ላይ የማደያው ባለቤት አቶ ሪያድ ኡመር፤ የአካበቢው መንግስት ባደረገላቸው ያልተቋረጠ የሞራል ድጋፍ ከ25 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቱ በቀጣይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራትና አካባቢውን ለመለወጥ ሰፋፊ የልማት እቅዶች ያሉአቸው መሆኑን ገልጸው፤ የሚደረገውን ሁሉ አቀፍ የመንግስት ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ቡርጂ እንደገለፁት፤ አካባቢው ከፍተኛ የማዕድን ሀብት የሚመረትበት በመሆኑ ወርቅን በዘመናዊ መንገድ በማምረት ስራ ላይ ለተሰማሩ አልሚዎች የማደያው መገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው፤ የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ አልሚ ባለሀብቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ ተመስርቶ ወደስራ ሲገባ በክልሉ 12 ማደያዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አሁን ላይ 40 ማደያዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንዳሉም ገልጸዋል።

በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፤ በክልሉ የሚገኙ ማደያዎችና ባለሀብቶች ፍትሐዊ የነዳጅ ስርጭት እንዲፈጠር በማድረግ ለአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን