የጌዴኦ ዞን አስተዳደር በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ላይ በሚታዩ ተግዳሮቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው
የጌዴኦ ዞን አስተዳደር በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን የመለየትና መፍትሔ ማስቀመጥን ያለመ ውይይት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በዲላ ከተማ ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የጌዴኦ ዞን ሥራ ዕድል በፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመለየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ በሚካሄደው ውይይት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ በንቃት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንገብጋቢነት አንጻር መንግሥት ለወጣቶች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ሥራ ለማስያዝ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተው በዞናችን በሁሉም መዋቅሮች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች ቢኖሩም በተሰማሩበት ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሥራ አጥነት ችግር አንጻር እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎች ውስን መሆናቸውን ያነሱት አቶ ተገኝ ከችግሩ ስፋትና አንገብጋቢነት አንጻር የባለድርሻዎች ቅንጅት ማነስ፣ የሀብት እጥረት፣ ያሉ ፀጋዎችን እንደ ዕድል ያለመጠቀም ችግር፣ የሥራ ባህል ያለማዳበርና የተነሳሽነት ችግር ካሉት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው እነዚህን ለመቅረፍ ከልየታ ጀምሮ እስከ ሥራ ሥምሪት ድረስ ያሉ ጉዳዮችን በትኩረት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙንም ችግሮቹን በማለፍ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በሀገር ደረጃ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ መንግሥት የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ዝናቡ፤ የሥራ አጥነት ችግር አገራዊ አጀንዳ ተደርጎ እየተሠራ ቢሆንም ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ወጣቶችን በዕውቀት፣ በክህሎትና በሀብት በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በዞናችን ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ተራማጅ ቢሆኑም በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የፋይናንስ ተቋማትንና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ጨምሮ በደንብ ልንደግፋቸውና ልናጠናክራቸው ይገባል ነው ያሉት።
በመጨረሻም ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን የመለየት፣ የሥራ ስምርት የመሰጠትና ሀብት በመንግሥት ብቻ ሰለማይቻል ማህበራዊ መሠረቶችን በማንቀሳቀስ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ አመራር አካላትም በቁርጠኝነት መደገፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ አልሚ ባለሀብቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ክልል ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ስራ ላይ ናቸው
በየአካባቢው ስኬታማ የሆኑ ሀሉ አቀፍ የልማት ተግባራትን ወደ ህዝቡ በማስፋፋት የኢትዮጵያ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተጠቆመ