በደረሰ አስፋው
“ህይወት በምዕራፍ የተከፋፈለች ናት” ሲል ሃሳቡን ይጀምራል። በብዙ ባህላዊ ተጽእኖ ውስጥ የነበረውን ህይወት አልፎ ወደ ትምህርት ቤት ሲያቀና፣ ለብዙዎች አጃኢብ የሚያሰኝ ክስተት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ይህንንም የህይወቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ አድርጎ ይወስደዋል። በእንብርክኩ ኪሎ ሜትሮችን እየተጓዘ መማሩ የእሱን መንፈሰ ጠንካራነት የሚያመላክት ስለነበር።
እንዲህ እየሆነ ፊደልን ሀሁ ብሎ ቆጥሮ እስከ 8ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ የመለሰ የመማር የህይወት ምዕራፍ ግን ከ8ኛ ክፍል አልዘለለም፡፡ መማር ባይችልም ለቀጣዩ ህይወቱ በአዲስ ምዕራፍ ውስጥ ራሱን ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ተመፅዋች ከመባል ይልቅ ሰርቶ መኖርን መረጠ፡፡ በሚኖርበት አካባቢ ጫማ ወደሚሰፉ ባለሙያዎች ጎራ እያለ ሙያውን ቀሰመ፡፡ መንገዱ ረጅም፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና እርሱም በእንብርክክ የሚሄድበት ቢሆንም፣ ለዚህ ግን እጅ አልሰጠም።
መለሰ ሾጤ የተወለደው ሀዋሳ ከተማ ሎቄ አካባቢ ነው፡፡ አሁን መኖሪያው ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ጨፌ ቀበሌ ነው፡፡ በትውልድ አካባቢው ሎቄ እስከ 6ኛ ክፍል፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍልን ደግሞ ጨፌ ኮቴ ጀቤሳ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደተማረ ያወሳል፡፡
የመለሰ ችግር ድርብ ነው፡፡ ቤተሰቡም ቢሆኑ ከእጅ ወደ አፍ የሚባለውን ኑሮ እንኳ መኖር የተሳናቸው ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲማር በአንድ በጎ አድራጊ መምህር ድጋፍ ሲሆን፤ ደብተርና እስክሪብቶ ድጋፍ ያደርጉለት እንደነበር ነው ያስታወሰው። አልፎ አልፎ ቀለቡንም ቢሆን ሸጎጥ ያደርጉለት እንደነበር በመጠቆም፡፡
አባቱን ገና በህጻንነቱ ማጣቱን ይገልጻል። የእለት ጉርሱን አፈላልገው ያጎርሱት የነበሩት ወላጅ እናቱንም በሞት ማጣቱ ሌላው የመለሰን ችግር ተከትሎ የመጣ ፈተና ነበር፡፡ ችግር ቢደራረብበትም እጁን ግን ለልመና አልዘረጋም። መለሰ ከአቅሙ ጋር ሊጣጣም የሚችለውን የጫማ መስፋት ስራ ለመልመድ የወጠነውም በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ወደ ጫማ ሰፊዎች ጎራ እያለ ሙያውን መመልከትም የሱ የዘወትር ስራ ሆነ። የሚንቀሳቀሰውም እንዳሁኑ በክራንች ሳይሆን በእንብርክክ ነበር።
የአካል ጉዳቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ትክክለኛ መረጃ ባይኖረውም፣ ፖሊዮ ይሆናል የሚል ግምት አለው፡፡ ሁለቱም እግሮቹ መንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህም ለበርካታ ዓመታት በእንብርክኩ ሲሄድ መቆየቱን ነው የገለጸው፡፡ መለሰ አሁን ላይ ቸሻየር ኢትዮጵያ፣ ሀዋሳ ቅርንጫፍ ባደረገለት የክራንች ድጋፍ የቀድሞ ችግሩን እንዳቀለለት ይናገራል፡፡ እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ለመስራትም አስችሎታል፡፡ መለሰ ችግር ቢፈትነውም፣ ህይወቱን ቢያጎሳቁለውም ልመናን መጠየፉ ደግሞ በአካባቢው ማህበረሰብ ልዩ መታወቂያው ነው፡፡ እንዲያውም ለሌሎች አካል ጉዳተኞችም ሆነ ሙሉ አካል ላላቸው ምሳሌ መሆኑን ጭምር ይገልፃል፡፡
“ልመናን እጠየፋለሁ፣ ልመና ለችግር ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ህይወትን ተስፋ ቢስ ከማድረግ ውጪ፡፡ ይልቁንስ የምመኘው ሰርቼ በመኖር ህይወቴን ተስፋ ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ መስራት የውስጥ እርካታን ይፈጥርልኛል። በርካታ አካል ጉዳተኞች ሲለምኑ ሳይ ውስጤ ይረበሻል፡፡ ያም ቢሆን ስሩ እያልኩ መክሬ ካለኝ ለማካፈል ግን አልነፍግም፡፡ እኔ እጄን ለልመና ዘርግቼ አላውቅም” ሲል ነው የተናገረው፡፡
መለሰን ያገኘሁት ከአንድ ደሳሳ ቤት በረንዳ ስር ነው፡፡ የሚሰሩ ጫማዎች በፊት ለፊቱ ሰብሰብ ብለዋል፡፡ ደንበኞቹም እንዲሁ። ከደንበኞቹ ማረፊያ ወንበር ላይ ተቀምጬ ስራውን መመልከት ቀጠልኩ፡፡ የተቀመጡት ደንበኞችም መነጋገሪያቸው የመለሰ ጉዳይ ነበር። “እንዲህ ሰርቶ መኖር እየተቻለ መለመን ለምን አስፈለገ? ለማኞችን ያባለገው ሰው ነው” እያሉ ይጨዋወታሉ፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት የልመና መስፋፋት ሊኮነን ይገባል ሲሉ አምርረው ይናገራሉ፡፡ አካል ጉዳተኛው እንዲህ ከሰራ ጤናማው ለምን መለመን አስፈለገ በማለት፡፡
የመለሰን የስራ ቅልጥፍናን ለተመለከተ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ትናንት ሰዎችን በመመልከት የለመደው ሙያ ዛሬ ግን ተክኖበታል፡፡ አዳዲስ ጫማዎችን በስውር ይሰፋል፡፡ የጫማ ሶል ይቀይራል፡፡ የተበላሹ ጫማዎችን በመጠገን መልሶ መልክ ይሰጣቸዋል፡፡ በርካታ ደንበኞችም አፍርቷል፡፡ በእሱ ዘንድ ስራዎችን ለነገ ብሎ መቅጠር የማይፈቀድ ተግባሩ እንደሆነም አጫወተኝ፡፡
የመለሰ የስራ ተነሳሽነት ቀልባቸውን የሳባቸው ወደ ስራ ቦታው ጎራ ይላሉ፡፡ የሚሰራው በእጅ ቢሆንም የማሽን ያህል ፈጣን ነው፡፡ ለደንበኞች ቀጠሮ ከመስጠት ይልቅ ወዲያው ሰርቶ መስጠትን ይመርጣል፡፡ “ስራን ለነገ ማለት ስንፍና ነው፡፡ ለነገው ነገ ሌላ ስራ አለው” ያለ ሲሆን፣ ለእሱም ለእለት ገቢው ጠቃሚ እንደሆነ ነው የሚገልጸው።
መለሰ ትዳር መስርቶ የሁለት ልጆች አባት ሆኗል፡፡ አንዷን ከፍሎ ያስተምራል፡፡ በወር 1 ሺህ 500 ብር የቤት ኪራይ ይከፍላል፡፡ የቤተሰቡ የቀለብ ምንጭም ይሄው ስራው ነው፡፡ የደንበኞች ቁጥር መጨመር ሲልም ከጎኑ አስቀምጦ ያስለመዳት የትዳር አጋሩም ወስፌና ክርን አዋዳ በስራው ታግዘዋለች፡፡ ለመንደሩ ትልቅ ምሳሌ ሆነው የታዩ ጥንዶች እንደሆኑም በብዙዎች ዘንድ ይነገራል፡፡ ሙሉ አካል እያላቸው ካለስራ በአልባሌ ቦታ ለሚውሉ ወጣቶች ምሳሌ ናቸው፡፡
“ትናንት ወደ ሌሎች ሰዎች ጠጋ ብዬ የቀሰምኩት ሙያ ዛሬ መተዳደሪያዬ ሆኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‘ሰው ሳትሆን ሰው አትፍጠር’ ቢሉኝም ትዳር መስርቼ እና ልጆች ወልጄ እነሱንም ማስተዳደር በመቻሌ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ለቀናት በእንብርክክ በመሄድ ሙያውን የለመድኩት ባለ ስራ ለመሆን እንጂ ስራ አልባ መሆን ስለማልመኝ ነው፡፡ እነሆ ያሰብኩት ተሳክቶ በፈጠርኩት ስራ ከራሴ አልፌ ለቤተሰቤ መትረፍ ቻልኩ። በመኖሪያ መንደሬ ማህበራዊ ጉዳይ ሲያጋጥም እጄን አልሰበስብም፡፡ ሰው ሲታመምም ሆነ ሲሞት የማህበረሰቡ አካል ነኝና እሳተፋለሁ፡፡”
የመለሰ ሀሳብ በዚህ ብቻ የሚገታ አይደለም፡፡ ስራውን ከተለምዶ ወይም ከእጅ ስራው በተጨማሪ አጋዥ ግብአቶችን በማሟላት የማዘመን ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህ ግን የብድር ተቋማትን ድጋፍ እንደሚሻ አልሸሸገም፡፡ ቦታው ቢመቻችለትና ተጨማሪ የገቢ አቅምን መፍጠር ቢችል፣ ጎን ለጎን ካልሲ፣ የጫማ ሶል እና ሌሎች ቁሳቁሶችን የመነገድ ዕቅድም አለው፡፡
ከዚህ በፊት በየቀኑ ከሚያገኘው ይቆጥባል፤ እቁብም ይጥላል፡፡ አሁንም ቢሆን የቀድሞው ተግባር የተወሰነ የመቀነስ አዝማሚያ ቢታይበትም እቁብ የመጣሉን ልማድ ግን አልዘነጋውም፡፡ “ነገን ማሰብ ከችግር ያሻግራል” ሲል ነው የተናገረው፡፡ የወቅቱ የኑሮ ውድነት እንደፈተነው የሚገልጸው መለሰ፣ ከዚህ ችግር ለማምለጥ መስራት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነም ነው የገለጸልኝ፡፡
“ልመና ከችግር አያወጣም፡፡ ልመና እሳት ነው ይፋጃል” የሚለው መለሰ፣ ሰርቶ የሚያገኘው ገቢ እርካታን እንደሚፈጥርለት ነው የተናገረው።
ለዚህ ግን ድጋፍ የሚያደርግለትን አካል ነው የሚፈልገው፡፡ ድጋፉም የብድር እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ይህ ሀሳቡ እውን ቢሆን ከጫማ ስፌቱ ጎን ለጎን በርካታ ስራዎች እንዳሉ እና ባለቤቱንም ወደ ስራ በማሰማራት ተጨማሪ የገቢ አቅምን ለመፍጠር ነው ሀሳቡ፡፡
መለሰ የተሰማራበት ስራ በሰዎች አይን ሲታይ አነስተኛ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በስራው በርካታ ቁምነገሮችን እየሰራበት ነው፡፡ እጁን ለልመና አልዘረጋም፡፡ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ቀለቡን ሸፍኖ ምጽዋት ለሚጠይቁትም እጁን ሳይሰበስብ እየኖረ ይገኛል፡፡ በዚህ ስራውም አድጎ የተሻለ ሰው ሆኖ መታየትን ይመኛል፡፡ አካል ጉዳተኝነቱ እግሩ እንጂ መላው አካሉ ባለመሆኑ ባለው አቅም ሰርቶ ለማደግ ነው የዘወትር ምኞቱ፡፡
እኛም የመለሰ ሀሳብ እውን ይሆን ዘንድ የብድር ተቋማት ድጋፋቸውን በማሳየት ነገ የተሻለ ሰው ሆኖ እንዲታይ ሊያግዙት ይገባል እንላለን፡፡ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው በህይወታቸው የልብ መሻታቸው ለመድረስ በራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት እና ትጋት ባሻገር፣ የማህበረሰቡ ዕገዛ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። አካል ጉዳተኞችን ማህበረሰቡ ባይነቅፍ፣ ነገ ተምረው የት ይደርሳሉ በቃ ስፍራቸው ይሄ ዝቅተኛ ቦታ ነው ባይል የተሻለ ነው ለማለትም እንወዳለን፡፡
More Stories
“ለአፈታሪክ የቀረበ ጀብድ”
“ባንሄድ ይሻላል”
“ህሊናን አሳምነው ከሰሩ ሁሉም ስራ ቀላል ነው” – ወ/ሮ ሮማን አጥናፉ