የልማት ዕድሎችና ተግዳሮቶች
በፈረኦን ደበበ
አሁን አሁን በአፍሪካ ጎልቶ የሚታየው የድህነትና ኋላቀርነት ትርክት ሳይሆን የመሻሻልና የአብሮነት ዕሳቤ መሆኑ ተስፋ ይጭራል፡፡ ሀገራትም ራሳቸውን ወደ ኋላ ቀስፈው ከያዙ ችግሮች ለመውጣት መጣጣራቸው ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ መፍትሄ እንደሚያገኙ ታምኖበታል፡፡
በርካታ ሀገራት ከችግሮች ለመውጣት መነሳሳታቸውና ይህም ቀደም ሲል የነበሩበትን ዘይቤ ለመቀየር አስተዋጽኦ ሲያደርግ የተዘረጋው ዓለም አቀፋዊ የድጋፍ ማዕቀፍም ጉድለቶቻቸውን እየሞላ ህልሞቻቸውን ለማሳካት እገዛውን ቀጥሎበታል፡፡
አዎን ከእንደዚህ ዓይነት መስተጋብሮች አንጻር ስንመለከተው አሁን የምንገኝበት ጊዜ ለአፍሪካ የሞት ሽረት ሆኖ ይታያል፡፡ ጥረቱ ከተዳከመና የነበረው ኋላ ቀር አስተሳሰብ ቦታውን መልሶ ከተቆጣጠረ የተለፋው ሁሉ ከንቱ እንዳይሆን መንግሥታትና ህዝቦች ይረዳሉ፡፡ ለዚህ ነው አጋጣሚዎቻቸውን በመጠቀም የልማት ዕድሎቻቸውን ለማስፋት ጥረት እያደረጉ የሚገኙት፡፡
የዓለም ሀገራት የሚያደርጉትን የልማት ጥረት በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የዓለም የገንዘብ ተቋም ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርትም በተለይ ከሠሀራ በታች ያሉ ሀገራት እየገጠማቸው ያለውን ውጣ ውረድ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል፡፡ ልማትና ዕድገትን ለማረጋገጥ ምን ምን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባቸውም ጠቁሟል፡፡
በየጊዜው ተቋሙ እያተመ የሚያወጣው መረጃ “አውትሉክ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ከብዙ የዓለም ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ውይይት አድርጓል፡፡ ዕድገቱ ከሠሀራ በታች ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሶ ያሉ ተግዳሮቶችንም ዘርዝሯል መወሰድ ስለሚገባቸው የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች ሁሉ በመጠቆም፡፡
ትንበያው ከሠሀራ በታች ላሉ አመርቂ መሆኑን ጠቅሶ ለውጡን ለመተግበር ግን ከፊት ለፊት የተደቀኑ ችግሮች መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡ በከፍተኛ መጠን የተንሰራፋው ድህነት፣ ሥራ አጥነትና ዕድሎች ካለመኖር ጋር ተያይዞ ደካማ የአስተዳደር ሥርዓት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሷል፤ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማምጣት እነዚህ ችግሮች መቀረፍ እንደሚገባቸው ሁሉ በማሳሰብ፡፡
በሀገራቱ የሚመዘገበው አማካይ ዕድገት በያዝነው ዓመት በ3 ነጥብ 6 በመቶ ላይ እንደሚቆይና ነገር ግን ቀጣይ ዓመት እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ 4 ነጥብ 2 በመቶ መድረስ እንደሚችል የጠቆመው መግለጫው ይህ ሁሉ እንዳይሳካ እንቅፋት ስለሚሆነው የዋጋ ንረትም አንስቷል ሩብ በሚሆኑ ሀገራት በባለ ሁለት አሀዝ እንደሚቀጥል ሁሉ በማመልከት፡፡
ሌላው የታዳጊ ሀገራት የልማት እንቅፋት የተባለው የውጭ ዕዳ የመክፈል አቅም ማነስ ሲሆን ይህም እያደገ ካለው የዕዳ ክፍያ ጋር ተጣምሮ የሀገራትን ሀብት እያመናመነ መገኘቱን ጠቅሷል በብዙ ሀገራት ካለው የውጭ ምዛሬ ክምችት ችግር ጋር ተዳምሮ፡፡
በተቋሙ የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ካትሪን ፓቲሎ ተናግረዋል በማለት የመረጃ ምንጫችን እንዳስታወቀው ከሆነም የአካባቢው ሀገራት በአሁኑ ጊዜ በአስቸጋሪ ምርጫ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በአንድ በኩል የተዛባ የገንዘብ አጠቃቀማቸውን ለመቀየር የዋጋ ግሽበት ማስተካከል፣ የገንዘብ አቅማቸውን ማጠናከርና በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲኖራቸው ሲያስፈልግ ይህም የምጣኔ ሀብት ያለመረጋጋት ሲከሰት በቀላሉ ለማስተካከል ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ሆኖም በሌላ በኩል ሀገራትን ለችግር የሚዳርጉ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ሳያነሱ አላለፉም ምክትል ዳይሬክተሯ በየጊዜው እያደገ ያለውን የህዝብ ቁጥር ከፖለቲካዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቻቸው ጋር በማዋሃድ ድጋፍን ማግኘት እንደሚጨንቃቸው ሁሉ በማውሳት፡፡
ባደረጉት ሰፊ ገለጻ የአፍሪካ ሀገራትን የሚጎዳቸው ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ያነሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ወጥነት የሌለው የዕድገት ዘይቤ ተጠቃሽ ነው በዕጥረቶች ከታጀበው የገንዘብ አቅርቦት ተነስቶ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስን ስለሚያስከትል፡፡
የእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች መኖር ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ቅሉ “ምንም ያለመሥራት” ራሱ የባሰ ችግር እንደሚያስከትልም ነው የአፍሪካ ኒውስ ሀሳባቸውን ያሰፈረው፡፡
ስለ መንግሥት ፖሊሲ ሲያወሱም በአንድ በኩል የሀገር ውስጥ የገንዘብ እጥረት ችግሮችን በመቀነስ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ም/ዳይሬክተሯ በሌላ በኩል ደግሞ አሉ፤ በሌላ በኩል የሚደረጉ የለውጥ ሥራዎች በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ዘይቤ ተቀባይነት እንዲኖራቸው መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ ተመን የቀየረች እንደመሆኗ ገለጻቸው ጠቃሚ ነጥቦችን ሲያሳይ ከለውጡ ዓላማ ጋርም ተያይዟል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መንከባከብ የሚመለከት ሲሆን ሌላው ደግሞ ሁሉንም ያካተተ ዕድገት ማረጋገጥ ነው በቂ የሥራ ዕድሎች መፍጠርን ጨምሮ፡፡
ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ማህበራዊ ሴፍትኔት ማጠናከርም ሌላው ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ያወሱት ካትሪን፣ እነዚህ ተግባራትን ለማከናወን ጠቃሚ የተባለ የአሠራር ሥርዓትንም ጠቁመዋል በተለይ ለውጡን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረጽ የሚረዱ የግንኙነትና የምክክር አግባቦች ማስፈለጋቸውን በመጠቆም፡፡ የህዝቡን አመኔታ ማሳደግ እንዲቻል የአመራር ቁመና ማሻሻልም እንዲሁ፡፡
በመንግሥት የገንዘብ ፖሊሲ ላይ የህዝብን አመኔታ የሚሸረሽሩ ነገሮችን እንዳወሱት ከሆነም የአንዳንድ ሀገራት ማዕከላዊ ባንኮች ለህዝቡ እና ለኢንቨስተሮች ታማኝ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው ይህም የሚረጋገጠው የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋት አቅማቸው ነው ብለዋል፡፡
አሠራሩ ካለምንም ውጣ ውረድ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ በባለብዙ ወገን የሚደረጉ የፋይናንስ ድርድሮች ጠቃሚ መሆናቸውን አሳይተው እንዲህ አይነት ገንዘቦች በጣም ድሃ ለሆኑ ሀገራት መስጠት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
ከውጭ ገንዘብን የማግኘት ችግር ላለባቸው ሀገራት የዓለም የገንዘብ ተቋም አስተማማኝ አቅርቦት ለማድረግ መዘጋጀቱን የገለጹት ኃላፊዋ በዚህም ከ2020 ወዲህ 60 ቢሊዮን ማሠራጨቱን አስታውቀዋል ይህም ከ1990ዎቹ ጋር ሲነጻጸር ዕጥፍ እንደሆነ በመጠቆም፡፡
ከአቅም ግንባታ አንጻርም በተለይ ተቋሙ ከሠሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሰጠው ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
More Stories
“ለአፈታሪክ የቀረበ ጀብድ”
“ባንሄድ ይሻላል”
“ህሊናን አሳምነው ከሰሩ ሁሉም ስራ ቀላል ነው” – ወ/ሮ ሮማን አጥናፉ