በእንስሳት ሃብት ልማትና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በእንስሳት ሃብት ልማትና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ርዕይ እና ጉባኤ እንደሚካሄደ ተገለጸ።
አውደ ርዕይ እና ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አደራሽ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡
በአውደ ርዕዩ ከ14 ሃገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች እና የሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካለት የሚሳተፉበት ይሆናል ተብሏል።
ከጥቅምት 21 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ የሚካሄደው አውደ ርዕይ በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት፣ በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ በኔዘርላንድስ ልማት ድርጅት ፕሮግራም (ኤስ.ኤን.ቪ) እና በዓለም አቀፍ የነፍሳት ፊዚዮሎጂና ሥነ-ምህዳር ማዕከል (ICIPE) የሚዘጋጅ መሆኑን የንግድ ትርኢቱ አዘጋጅ የሆነው ፕራና ኤቨንትስ አስታውቋል።
የፕራና ኢቨንትስ መስራችና ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነብዩ ለማ ከተባባሪዎቹ ጋር በመሆን በአጠቃላይ ዝግጅቱ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በአውደ ርዕዩ ከቻይና፣ ከቼክ ሪፐብሊክ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከኬኒያ፣ ከጆርዳን፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከስኮትላንድ፣ ከቶጎ፣ ከቱርክ፣ ከዩጋንዳ እና ከአሜሪካ የእሴት ሰንሰለቱን የሚወክሉ የዘርፉ መሪዎችና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከንግድ ጎብኚዎች ጋር የስራ ግንኙነት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ከ5000 በላይ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካ እና ዓለም አቀፍ ሀገራት ጎብኚዎች እንደሚሳተፉም ተጠቁሟል።
ተሳታፊዎቹ በእንስሳት ሃብት ልማትና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ የገበያ ተስስር፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚቃኙበትን ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸውም በመግላጫው ተብራርቷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ፍቃዱ በበኩላቸው አወደ ርዕዩ የእንስሳት ዘርፉን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምን ጨምሮ በመንግሥት በኩል እየተተገበሩ ያሉ ተግባራትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ ተሞክሮዎች የሚገኙበት ይሆናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ውስጥ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ
More Stories
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ማሻሻልና ማዘመን እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
ጥራት ያለው ኮረሪማ ለገበያ ለማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትኩረት መደረጉን የአሪ ዞን ቡናና ቅመማቅመም ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ