የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በወቅቱ ቢጀመርም የትምህርት አመራር ምደባ መዘግየትና በመምህራን ደመወዝ አከፋፈል ላይ የሚስተዋል መንጠባጠብ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የአንዳንድ ት/ቤት መምህራን ገለፁ
ችግሩን ለመቅረፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የልዩ ወረዳው ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ገልጿል።
ተማሪ ቢንያም አድማሱ፣ መሠረት ዝናቡ እና አበበ ግርማ በሙዱላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት የ10ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ላለፉት ተከታታይ የትምህርት ቀናት መምህራን እያስተማሩ እንደሆነ ጠቁመው አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የመንጠባጠብ ችግር ግን መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠይቀዋል።
መምህርት አለሚቱ አዋኖ፣ ሀብታሜ ህቤቦ እና ሽታ በቀለ በሙዱላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ መምህርት መሠረት አበበ እና ታምራት ታደሰ በሙዱላ ከፍተኛ 2ኛ ደረጀ ት/ቤት የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል መምህራን በበኩላቸው በመንግስት ለትምህርት ጥራት የተሰጠውን ትኩረትና የተማሪዎችን ውጤታማነት ታሳቢ በማድረግ የሙያ ግዴታቸውን እየተወጡ ቢሆንም አሁን አሁን እየተስተዋለ ያለው የደመወዝ አከፋፈል ችግር መንግስት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የሁለቱም ትምህርት ቤት ተወካዮች መምህር ተስፋዬ ታደሰ እና መምህር ኃይሉ ሀደሮ በሰጡት አሰተያየት የመማር ማስተማር ሥራው በአሁኑ ወቅት በተቻለ መጠን እየተሠራ ቢሆንም የትምህርት አመራር ምደባ እና የመምህራን ደመወዝ መዘግየት የትምህርት ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱ እንደመሆናቸው መጠን መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ብለዋል።
መምህራን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የትምህርት ጥራትና የተማሪዎችን ውጤታማነት ከግምት በማስገባት ያለባቸውን የትኛውንም ጥያቄ በሥራ ላይ ሆነው መጠየቅ እንዳለባቸው በመጠቆም ለጥያቄያቸው ምላሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የልዩ ወረዳው የመምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ተከተል ደበላ ናቸው።
የልዩ ወረዳው ትምህርት ቤቶች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበራ እንደተናገሩት የዓመቱን የመማር ማስተማር ሥራ በወቅቱ ለማስጀመር በተደረገው እንቅስቀሴ አንዳንድ ት/ቤቶች አካባቢ ክፍተቶች ቢኖሩም በአሁን ሰዓት በተለያዩ የግልና የመንግስት ት/ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
በተለያዩ መንገዶች የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ መንግሥቱ ተናግረዋል።
በየትምህርት ቤቶቹ የተወከሉ አካላትና መምህራን ሥራቸውን በተገቢው በማከናወን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉም ኃላፊው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የጌዴኦ ዞን አስተዳደር በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ላይ በሚታዩ ተግዳሮቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ክልል ከ16 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ስራ ላይ ናቸው
በየአካባቢው ስኬታማ የሆኑ ሀሉ አቀፍ የልማት ተግባራትን ወደ ህዝቡ በማስፋፋት የኢትዮጵያ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተጠቆመ