በዞኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብርና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

በዞኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብርና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

የዞኑ ግብርና መምሪያ የ2017 ዓ.ም የበጋ የተቀናጀ ግብርና ልማት የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተከናውኗል።

የተቀናጀ ግብርና ልማት ለቤተሰብ ብልፅግና በሚል መሪ ቃል ነው ውይይቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት ባለፈው በጀት አመት በተደረገው ርብርብ ሰፋፊ የግብርና ስራዎች በውጤታማነት መሰራታቸውንና የለማው ሰብል ከብክነት የነፃ ምርት መሰብሰብ ይጠይቃል።

የጉራጌ ቡና ብራንድ አግኝቷል ሆኖም በማስተዋወቅ፣ በማስፋት እና ይበልጥ በማልማት በገበያ ስርአት እንዲመራ በትኩረት መሰራት ይጠበቃል ብለዋል።

እንሰት ለጉራጌ ዞን ህዝብ ዋነኛ የምግብ ዋስትና በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዝርያውን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋትን ስኬታማ ለማድረግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ ማድለብ፣ በግና ፍየል ማሞከት እና ዶሮ ማርባት ላይ በቀጣይም ይበልጥ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።

ጉራጌ ካለው የግብርና አቅም አኳያ ከዞን አልፈን ለሀገር ማሳያ መሆን ይቻላል ብለዋል አቶ ላጫ። ከወዲሁ የጤፍና በቆሎ መውቂያ ማሽኖች ማዘጋጀት ይገባል ያሉት አስተዳዳሪው የምርት ብክነት እንዳይኖር መስራት ይጠበቃል ሲሉም ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በበጋ እና በመደበኛ መስኖ በስንዴ በተሰራው ስራ ውጤታማ ተግባር መታየቱን በመግለፅ፤ ለመስኖ አልሚዎች ነዳጅ በአግባቡ ለማቅረብ ይሰራል ብለዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራል ብለዋል።

በዘንድሮው በጀት አመት በመደበኛ መስኖ ከ25 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት በላይ እንደሚለማ ገልጸው ከዚህም ባለፈ በበጋ መስኖ ስንዴ 650 ሄክታር መሬት ይለማልም ነው ያሉት።

ለዚህ ተግባር አጋዥ የሆኑት ግንባታቸው ተጀምረው የተቋረጡ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለማልማት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በበጋ በመደበኛ መስኖ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በእንስሳት ልማት ላይ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ሞዴል መንደር መፍጠር እና የተሻሻሉ ዝርያ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ የናይትሮጂን አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እደሆነም አንስተዋል።

በፍራፍሬ ልማትና በአረንጓዴ ልማት ስራ የተያዘውን ግብ ለማሳካት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ይለማል ብለዋል።

በዞኑ ያሉ ጸጋዎችን በተገቢው በመጠቀም የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የጉራጌ ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ የተሰሩ ስራዎችና ጠቋሚ እቅድ ያቀረቡ ሲሆን የቡና ምርት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን በሌማት ትሩፋት 111 መንደሮች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የባህር ዛፍ ተክልን በማንሳት በሌሎች ልማት መተካት መጀመሩና በዞኑ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ዝንጅብልና ኮረሪማ ማልማት መቻሉንም በሪፖርቱ አመላክተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ጥላሁን ሽምንሳ፣ ሚፍታ ሁሴን እና ከረሙ ጀማል ይገኙበታል። ከዚህ በፊት ባገኙት ልምድ በመነሳት በበጋ መሰኖ ለማልማት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየአካባቢያቸው ምርት ያለብክነት ለመሰብሰብ በሚቻልበት ዙሪያ መወያየታቸውን አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋት ከዚህም በላይ ለማሳካት እንዲቻል እንዲሁም በቡና ልማት፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦት ዙሪያ መደጋገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን