የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሴንተር ፎር ኢምፓወርመንት ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን ለሲቪክ ማህበራት ስልጠና ሰጠ
ሴንተር ፎር ኢምፓወርመንት ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ብስራት ኤሊያስ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በንቃት በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታማኝነት ያለው እንዲሆንና ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ የሲቪክ ማህበራት ድርሻ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
የማህበሩ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ታደሰ በበኩላቸው፥ የሲቪክ ማህበር አመራሮች በቂ ግንዛቤ አግኝተው መራጩ ሕዝብ ወቅቱን ጠብቀው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱና በምርጫ ቀንም እንዲሁ በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ድምፅ እንዲሰጡ ለማስቻል ትምህርት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ ነው ብለዋል።
ስልጠናው በመራጮች ትምህርት ላይ ያተኮረ ሲሆን የመምህራን ማህበር፣ የሴቶችና ወጣቶች ማህበራት፣ የሃይማኖት ፎረም የአካል ጉዳተኛች ማህበር የጸጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በስልጠናው መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የጎፋ ዙርያ አንድ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ በላይ ባበና በምርጫ ክልሉ ባሉ 81 ምርጫ ጣቢያዎች ለመራጮች ምዝገባ በቂ ዝግጅት ተደርጎ የመራጮች ምዝገባ በተሳካ ሁነታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ካነጋገርናቸው የሲቪክ ማህበራት አመራሮች መካከል መሪጌታ ቀለመወርቅ ደረሰ፣ አቶ ኩኛኬ ኩርካ እና ወ/ሮ ሳባ ዘክዮስ በሰጡት አስተያዬት ከስልጠናው በቂ ግንዛቤ በማግኘታቸው ዜጎች በመራጮች ምዝገባ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በምርጫው የሚፎካከሩና የሚሳተፉ ሁሉ ከምንም በላይ የሀገርን ሰላምና ህልውና ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ሠላምን በሠላም ጊዜ እንደሚሠራ ተገለጸ
የሃይማኖት ተቋማት ፅንፈኝነትን፣ አክራርነትንና ከፋፋይ አጀንዳዎችን በመጠየፍ ሰላምና አንድነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለጸ
በኩታ ገጠም እርሻ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል አይነተኛ ሚና እንዳለው ተገለጸ