ሀብታሞቹ የአፍሪካ ሀገራት
በፈረኦን ደበበ
በግለሰቦች ደረጃ ሀብት የሚገኘው በሥራና ጥረት ነው፡፡ በሀገራት ደረጃ ግን ከጥረት ባለፈ ተፈጥሯዊ ልገሳም ያስፈልጋል። የሰው እጅ ሳይገባበት የሚታፈሱ ሀብቶች መኖር የብዙ ሀገራት የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ስላደረገ፡፡
ከህይወት ቀጥሎ የሰው ልጅ ከፍተኛው ፍላጎት የሆነው የኑሮ መሻሻል ወይም ብልጽግና ትልቅ ዕሴት ነው፡፡ ብዙዎች ይህንን ደረጃ ለመቆናጠጥ ደፋ ቀና ሲሉ ጥቂቶች ደግሞ ውጤታማ በመሆን የተትረፈረፈ ህይወት መምራት ችለዋል፡፡
ግለሰቦችም ሆኑ ሀገራት ዕድገትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ያሉበት የአሁኑ ዘመን፤ በአንድ በኩል ደስታና ህይወትን ለማቃለል ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ሲሸለም፤ በሌላ በኩል እንደ ግጭት ያሉ አውዳሚ ተግባራት የኑሮ ምስቅልቅልነትን አምጥተዋል።
ሀገራትም ሆኑ ዜጎቻቸው ለእንቅፋቶች እጅ ሰጥተው ቁጭ አላሉም፡፡ ከደረሱባቸው ችግሮች የተሻለ ትምህርት እየወሰዱ ትጋታቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ያጋጠሟቸውን መሰናክሎች እያለፉ አርአያ ለመሆንም በቅተዋል፡፡
የዕድገት መሠረት የሆኑ የሥራ ፈጠራ፣ የገንዘብ ምንጭና የትብብር መስኮች በተስፋፉበት ዓለም አፍሪካዊያንም የዕድሉ ተቋዳሽ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አቅማቸውን አቀናጅተው የዓለምን ገበያ ሰብረው መግባትም ችለዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ለደቡብ አፍሪካዊ ባለሀብት ደረጃቸውን እንደለቀቁ የሚነገርላቸው ናይጀሪያዊው ባለሀብት ዳንጎቴ የዚህ አንዱ ማሳያ ናቸው፡፡
ሀገራት የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪነት አቅማቸውን ለመለካት ሲያስችል ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ሊጎናጸፉ የሚችሉባቸው ተጨማሪ ድሎችንም ለመተንበይ ያስችላል፡፡
አፍሪካን ኒውስ የተባለው የዜና ምንጭ እነዚህን የመሳሰሉ የሀገራት ተነጻጻሪ አቅሞቻቸውን አስፍሯል “ሀብታም ሀገራት በአፍሪካ” ብሎ ባወጣው ዘገባ ሥር፡፡ ምጣኔ ሀብትን እንደ ዋና መስፈርት አድርጎ ዜናውን ሲጀምር በሀገራት ውስጥ ያለው ዓመታዊ የምርት መጠንን ደግሞ መለኪያ ነጥብ አድርጓል፡፡
በአህጉሪቱ ግዙፍ ምጣኔ ሀብት መገንባት እንደቻለች ከሚነገርላት ሀገር ሲጀምር ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት መጠኗም 447 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በተሰበሰበው መረጃ መሠረት፡፡
በምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ይህች ሀገር ናይጀሪያ ስትሆን የደረጃውን ማማ እንደተቆጣጠረችም ነው ያስታወቀው፤ ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽን በማስከተል፡፡ በአፍሪካ ከ200 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዳላት ተጠቃሽ የሆነችው ይህች ሀገር፤ ከዛሬ አራት ዓመታት በኋላ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቷን እስከ 915 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ እንደምትችልም ተተንብዮአል፡፡
መረጃው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ትንበያን ጠቅሶ እንደገለጸው ደረጃዋ በቀጣይ ዓመታት ሊነሱ የሚችሉ ብጥብጦችና ቀውሶችን የማያካትት ሲሆን በመጪዎቹ ረጅም ዓመታት ውስጥም አህጉሪቱን በበላይነት መምራት እንደሚያስችላት አስታውቋል።
ዘገባው በአህጉሪቱ ተንሰራፍተው የቆዩና የልማት ጠንቅ የሆኑ እንደ ሙስና፣ መልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ግጭትና በአንድ ወይም ጥቂት ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራውን አሀዳዊ የአመራረት ዘይቤ ባልጠቀሰበት ሁኔታ ተጨባጭ ለማለት ባይቻልም ሀገሪቱ ተከታትለው የተቀመጡትን ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽን በልጣ ማደግ መቻሏንም ነው ያወሳው፡፡
በሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት፣ ከዚያ ውስጥ እያንዳንዱ ዜጋ በሚያገኘው የገቢ መጠንና በሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ማሳያዎች ላይ የተመሠረተው ደረጃ አዳዲስ ከሚገኙ መረጃዎች አንጻር ሊለወጥ እንደሚችል ሁሉ ያስታወቀው አፍሪካን ኒውስ፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሀገራት ያሳደጉት የመግዛት አቅምም እዚሁ ውስጥ ይካተታል ብሏል፡፡
በድህነትና ኋላ ቀርነት ተተብትባ ቆይታለች የምትባለው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉ የተካተተችበትን ይህ ደረጃ ሲገልጽም እስከ ስምንት የሚደርሱ ሀገራትን ዘርዝሯል ምንም እንኳን ነዳጅና ሌሎች ተፈጥሮ ሀብቶችን እንደ ዋነኛ የሀብት ምንጭ አድርጎ መጥቀሱ በፈጠራና ክህሎት የተገኙ ለውጦችን ዝቅ አድርጎ የሚያሳይ ቢያስመስልም፡፡
የሀገራት ደረጃና የሀብት ምንጮቻቸው
1. ናይጄሪያ፡- በአህጉሪቱ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ ባለ ብዙ የአመራረት ዘይቤ እና በተለይ በነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ የታደለች ሀገር ናት፡፡
2. ደቡብ አፍሪካ፡- ማዕድን፣ እርሻ እና አገልግሎትን ጨምሮ የባለ ብዙ የአመራረት ሥርዓት ትከተላለች፡፡
3. ግብጽ፡- ለባለ ብዙ የአመራረት ዜይቤ አመቺ የሆኑት እንደ ቱሪዝም፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም በእርሻ ላይ የተመሠረተች ሀገር ናት።
4. አልጀሪያ፡- ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅና ተፈጥሮ ሀብት ክምችት አላት፡፡
5. ሞሮኮ፡- እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና አገልግሎትን ያካተተ ባለ ብዙ የአመራረት ዘይቤ አላት፡፡
6. አንጎላ፡- ነዳጅና ተፈጥሮ ሀብቶቿ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
7. ኬኒያ፡- እርሻ፣ ቱሪዝምና አገልግሎትን ያካተተ የባለ ብዙ የአመራረት ዘይቤ ለአካባቢው ምጣኔ ሀብት ማዕከል አድርጓታል፡፡
8. ኢትዮጵያ፡- በፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ውስጥ እንድትገባ ያስቻሉ እንደ ግብርና፣ አምራችነት (ማኑፋክቸሪንግ) እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ አላት፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው