በገነት ደጉ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ኢያሱ ኤልያስ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ በሚገኙት አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል እና በናኦል ሆስፒታል አጠቃላይ ቀዶ ህክምና ሀኪም ናቸው፡፡ በህክምና ሙያ ለ14 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ እንቅርት ምንድነው? መንስኤውና ምልክቶቹስ ምንድናቸው? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
ዶክተር ኢያሱ፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!
ንጋት፡- ከልጅነት ጀምሮ ያለው የትምህርት ዓለም ጉዞዎን በማንሳት እንጀምር?
ዶክተር ኢያሱ፡- ትውልድና እድገቴ ከምባታ ዞን ነው፡፡ በዳምቦያ ወረዳ ነው የተወለድኩት፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ፉንጦ ለመጃ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምሬ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በአንጋጫ፤ የመሰናዶ ማለትም 11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ደግሞ ዋቻሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት፡፡
በወቅቱ ጎበዝና የደረጃ ተማሪ ብሆንም ወደ ህክምናው ዘርፍ እገባለሁ ብዬ አስቤ አላወቅም ነበር፡፡
በልጅነቴ የነበረኝ ህልም ወላጅ አባቴ መምህር ስለነበር መምህር መሆንን እመኝ ነበር፡፡ በኋላም ውጤቴ ጥሩ ስለነበር የመጀመሪያ ምርጫዬ ህክምና፣ ሁለተኛ ምርጫ ደግሞ ኢንጂነሪንግ ነበር። ወደ ህክምና በአንደኛ ምርጫ መሰረት በማግኘቴ ነው የገባሁት፡፡ በኋላም ወደ ሙያው ስገባ ግን ህክምናውን እየወደድኩ መጣሁ፡፡
የመጀመሪያ ድግሪዬን ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄያለሁ፡፡
የህክምናውን ሙያ የጀመርኩት በሀዋሳ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ሲሆን ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ካገለገልኩ በኋላ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ህክምና ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በኋላም የቀዶ ህክምናውን ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሆሳዕና በንግስት እሌኒ መታሰቢያ ሆስፒታል በመግባት ስሰራ ከቆየሁኝ በኋላ ወደ ሀዋሳ አዳሬ ሆስፒታል ተመለስኩኝ፡፡
በአዳሬ ሆስፒታል አሁን እስካለሁበት ድረስ ከስድስት ተከታታይ ዓመታት በላይ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
በትርፍ ሰዓት ሌሎችም ሆስፒታሎች ላይ አገልግያለሁ፡፡ ሆኖም ግን አሁን ላይ በዋናነት በትርፍ ሰዓት በናኦል እና በአቤም ሆስፒታል እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ንጋት፡- ታይሮይድ ምንድነው?
ዶክተር ኢያሱ፡- ታይሮይድ የሚለው ግላንድ ከአንገታችን ፊት ለፊት ወደታች ወረድ ብሎ በግራና በቀኝ እንዲሁም መሀል ላይ የምናገኘው ሆኖ በስዕል ሲገለጽ የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ታይሮይድ በተፈጥሮ ለሰውነታችን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሆርሞኖችን የሚያመነጭ ኖርማል ግላንድ ነው፡፡ ይኸው ግላንድ ሲያብጥ እንቅርት ወይም በእንግሊዝኛው ጎይተር እንለዋለን፡፡
ይኸው ግላንድ በቀኝም ሆነ በግራ ወይም መሀሉ እንዲሁም ወደ ውስጥ እና ሙሉ ለሙሉ ሊያብጥ ይችላል፡፡
በዚህን ጊዜ ሰዎች ሊደነግጡ ይችላሉ፡፡ ይህም በተፈጥሮ ሲፈጠር ከጉሮሮ ጀምሮ ወደ ታች ስለሚወርድ ሰዎች ምራቅ በሚውጡበት ወቅት የሚንቀሳቀስ ከሆነ እንቅርት ወይም እባጭ ነው ማለት ነው፡፡
ታይሮድ ትክክለኛ ቅርፅ ይዞ ሳለ በሚያብጥበት ጊዜ ነው ጎይተር የሚባለው፡፡ ጎይተር የተለያየ ቅርጽ ይዞ እንዲሁም ትንሽም ሆኖ ሊያስቸግር ይችላል፡፡
ታይሮድ ግላንድ የሚያመነጨው ሜታቦሊዝም ለሰውነት ኡደት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህ ሆርሞን እጥረት ካለ ሰዎች ሰነፍ ሊሆኑ፣ ንቃተ ህሊናቸው ዝቅ ሊል ይችላል። ይህም የሰዎች የንቃተ ህሊናቸው ጭምር የነቃ እንዲሆን የሚያደርግ ሆርሞን ነው ማለት ነው ታይሮይድ ሆርሞን፡፡
ንጋት፡- ይህ አስፈላጊ የሆነው ሆርሞን ነው በሚያብጥበት ወቅት እንቅርት የምንለው፡፡ ምን ሲሆን ነው የሚያብጠው?
ዶክተር ኢያሱ፡- ለማበጡ ብዙ መንስኤዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡
እንደ ሀገራችን በዋናነት ትልቁ ችግር የአዮዲን ንጥረ ነገር በምግባችን ላይ እጥረት መኖር እንቅርት እንዲያድግ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በሀገራችን አሁን ላይ እንቅርት በሽታ በስፋት ይስተዋላል፡፡ አሁን ላይ በሆስፒታሎች ከሚደረጉ የቀዶ ህክምናዎች መካከል አብዛኛዎቹ በሁሉም ሆስፒታሎች በሚባል ደረጃ የእንቅርት ቀዶ ህክምና ሲሰራ መታየት የተለመደ ሆኗል፡፡
ይህም የምንመገበው ምግብና የምንወስደው ውሃ የአዮዲን ማነስ ስለሚኖረው ነው፡፡ ሌላው የራሳችን በሽታን የመከላከል አቅም ማነስ ታይሮይድን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቁጣ እና በብግነት እንዲሁም በዘር (በቤተሰብ) የሆርሞኖች ማነስ ሊኖር ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ ጎመን አዘውትሮ በመመገብ ሊከሰትም ይችላል፡፡
እንቅርት አንዳንዴ የካንስር ምልክቶች የሚኖረው ሲሆን በልጅነት ዕድሜያቸው ለአንገት ጨረር የተጋለጡ ልጆችም ለእንቅርት ተጋላጭ የመሆን ዕድል አላቸው፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በሀገራችን ያሉ ምግቦች አብዛኞቹ የአዮዲን ዲፊሸንት(እጥረት) አላቸው። በተለይም አዮዲን ሊይዙ የሚችሉ ወተትና የወተት ተዋጽዕኦ፣ እንቁላል፣ አሣ የመሳሰሉ ሲሆኑ በእኛ ሀገር እነዚህን ምግቦች በብዛት አንወስዳቸውም፡፡
በተለይም ወደ ተራራማ አካባቢዎች አዮዲን በጣም ያንሳቸዋል፡፡ ውሃ ደግሞ ወደ ዝቅተኛ አካባቢ አዮዲን ያለው አይደለም፡፡ ለዚህም ነው እንቅርት በሀገራችን የተለመደ ነው ማለት ይቻላል።
ይህንንም ለመከላከል ምግባችን ላይ የምንጠቀመው የገበታ ጨው አዮዲን ያለው መሆንና በቅርበት የምናገኛቸው ወተት ተዋጽኦዎች መመገብ ቢቻል መልካም ነው፡፡
ንጋት፡- ጎይተር ወይም እንቅርት ዓይነቶች አሉት ይሆን?
ዶክተር ኢያሱ፡- አዎ! ብዙ የእንቅርት ዓይነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ልጆች በፍጥነት በሚያድጉበት ዕድሜ (ከ6 እስከ 12) ዓመት ውስጥ የሚያብጥ ጎይተር ዲፊቶዝ ወይም ፊዚዮሎጂክ ጎይተር ይባላል፡፡ ይሄ ሁኔታ በእርግዝና ወቅትም ሊከሰት ይችላል፡፡ይሄም የሚሆንበት ምክንያት ከፍተኛ የአዮዲን ፍላጎት ስለሚኖር ነው። ከሆርሞን አመንጪነት አንፃር ጎይተር በሶስት ዓይነት ይገለፃል፡፡ 1. ሲምፕል ጎይተር (የሆርሞን መዛባት ወይም ማነስ የሌለው) 2. HyperthYroidism (ቶክስኪ ጎይተር) 3. Hypothyroidism( የሆርሞን ማነስ የሚታይ ጎይተር) በሌላ መንገድ ጎይተር እራሱ ምንም ዓይነት cell ወይም እባጩ ምን ዓይነት ፀባይ አለው በሚለው ብንከፍል
1. Benign( አደገኛ ያልሆነ ሞኝ እባጭ)
2. Borderline (አጠራጣሪ የሆነ)
3. ንኦፐላስቲክ (የካንሰር ፀባይ ያለው)
4. ቁጣ ያለበት (እንፍላማቶሪይ) ሊባል ይችላል፡፡ እንዲሁም አልፎ አልፎ ከኢንፌክሽንም ሊፈጠር ይችላል፡፡
ንጋት፡- በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የትኛው የጎይተር ዓይነት ነው በብዛት ሊያጠቃ የሚችለው?
ዶክተር ኢያሱ፡- በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አብዛኛውን የሚያጠቃው አዮዲን ዲፊሸንሲ ጎይተር ነው፡፡ ይህም ጎይተር በጣም የተለመደ እና የሚታወቅም ነው፡፡ አዮዲን ዲፊሸንሲ ወይም ሲምፕል ጎይተር የምንለው በጊዜ ሂደት እያደገ እና ከቆይታ ብዛት ቶክሲክ ጎይተር ሊሆን ይችላል፣ በጣም ከቆይታ ብዛት ደግሞ ወደ ካንሰር ሊቀየር ይችላል፤ ባለበትም ሊቆይ ይችላል፡፡
በቀላሉ፣ ማለት ደማችን ላይ አሲድ የሚረጭ አይደለም ግን ሲምፕል ሆኖ የሚረብሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ባህሪያቸው የተለያየ ነው፡፡
ንጋት፡- እንቅርት ምን ዓይነት በሽታ ነው?
ዶክተር ኢያሱ፡- እንቅርት ለሚመለከተው ሰው ሁሉ ሲታይ ፊት ለፊት ያለ እባጭ ወይም እጢ ነው፡፡ ይህ እባጭ ለሰውየው ወይም ለታካሚው እረፍት የሚነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ሁል ጊዜ እያዩ ይህ ምንድነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ሰዎች ተሸፋፍነው የመሄድ ነገር አላቸው፡፡
እባጩ ለእይታችንና ለእጃችን ቅርብ ስለሆነ ሁልጊዜ እየነካካን የምናየው ነገር ስለሆነ ሰዎች እያዩ ዝም ብለው ለመኖር እረፍት የሚሰጣቸው አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እያደገ ሄዶ አተነፋፈሳችን ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል። በተለይም እባጩ ትልቅ ሲሆን የሰዎቹን የደም ግፊት ጨምሮ መተንፈስና መዋጥን ሊከለክል ሁሉ የሚችል በሽታ ነው፡፡
ንጋት፡- እንቅርት የሚያጠቃው የትኛውን የሰውነታችንን ክፍል እና የህብረተሰብ ክፍሎችን ነው?
ዶክተር ኢያሱ፡- ቀላል ያልኩት እባጭ ከመፍጠር በዘለለ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ቶክስክ ጎይተር በምንልበት ሰዓት ግን የማያጠቃው የሰውነታችን ክፍል የለም፡፡ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍሎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩም ያጠቃል፡፡
እንቅርት ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በተለይም የአዮዲን ተዋጽኦ የማይጠቀሙ በተራራማ አካባቢ ያሉ ሰዎችን በይበልጥ ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በሀገራችን በአሁን ሰዓት ላይ በስፋት የሚታይ በሽታ ነው፡፡
ንጋት፡- ምልክቶችስ ምን ምንድናቸው?
ዶክተር ኢያሱ፡- ሁሉንም ነገር የመረበሽ ባህሪ አለው፡፡ ያም ማለት ቶክሲክ በምንልበት ሰዓት በጣም ሆርሞን እየረጨ ነው ማለት ነው። በዚያን ውስጥም ቲ-3 እና ቲ-4 የምንላቸው ሆርሞኖች በጣም እየረጨ ነው ማለት ነው፡፡ ይህን በሚረጭበት ጊዜ ሁሉን ነገር ነው የሚያዛባው፡፡
ለምሳሌ ሰዎች ነጭናጫ መሆን፣ እንቅልፍ በደንብ አለመተኛት፣ የልባችን ምት እስኪታወቀን ድረስ መምታት፣ ከመጠን ያለፈ ላብ፣ አንዳንዴ እጅ መንቀጥቀጥ ሊኖር ይችላል፣ ህክምና ካላገኘ እስከ ልብ ድካም፣ በሴቶች ላይ የወር አበባ መዛባት ያመጣል፤ በጣም እየበላን የመክሳት፣ እንዲሁም አይን ላይ ምልክቶችን ሊታይ ይችላል፡፡
በቀዶ ህክምናው ወቅት ሙሉ በሙሉ አይወጣም፡፡ ሙሉ በሙሉ የወጣ ከሆነ እድሜ ልካቸውን መድሀኒት ይወስዳሉ ማለት ነው፡፡ ግን በአብዛኛውን ጊዜ የምናደርገው ትንሽ እንተዋለን፡፡
በህክምናው ወቅት አንዳንድ የሆርሞን እጥረት እንዳይከሰት ተብሎ ተለቅ ያለም ሊተው ይችላል። ይህም መልሶ ሊያድግ ይችል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የግራ ወይም የቀኝ በኩሉ ብቻ አብጦ የመሃሉ ካላበጠ ያበጠውን ብቻ ማውጣት ይቻላል፡፡ ይህም በሌላኛው በኩል ሊያድግ ይችላል፡፡
በሌላም በሽታው የካንሰር ምልክት ካለው ምንም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ተጠርጎ መውጣት አለበት፡፡ አሊያም ሊያድግ ይችላል፡፡ ካንሰርንም ሊያስከትል ስለሚችል ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ እስከ እድሜ ልክ መድሀኒት እንዲውጥ ይደረጋል፡፡
ንጋት፡- ህክምናው ተለይቶ ይሰጣል ወይስ የተቃራኒው በኩል እስኪያብጥ ይጠበቅ ይሆን? ዶክተር ኢያሱ፡- በህክምናው መጀመሪያ የሆርሞኑ ማነስ ወይስ መብዛት ነው የሚለው ይታያል፡፡ ህብረተሰቡ አብዛኛውን ጊዜ በዝቶ ነው ይላል። ይህም የተሳሳተ ነው፡፡ ሊያንስም እንደሚችል መታሰብ አለበት፡፡
በተለየ መልኩ ወደ ውስጥ የሚያድግ የእንቅርት ዓይነትም አለ፡፡ ይህም የሚታወቀው በአልትራ ሳውንድ ምን ዓይነት ነው የሚለውን በመለየት ነው፡፡ ከዚያም በዘለለ ወደ ታች ያደገ ነው የሚለውን የደረት እና የአንገታችንን የታችኛው ክፍል ሲቲ ስካን በማድረግ አሊያም ራጅ በማስነሳት ማወቅ ይቻላል፡፡
ሌላው እንቅርቱ ምን ዓይነት ነው የሚለውን ለማወቅ ከእብጠቱ ቦታ በመርፌ ናሙና ወይም በህክምናው (ANAC) የሚባለውን የደም ናሙና በመውሰድ መለየት ይቻላል፡፡
ቲ3፣ ቲ4 እና ኤስኤች መመርመር ግዴታ ነው፡፡ የሆርሞኑ መብዛትና ማነስ ከምልክቱ ባለፈ የሚታወቀው በዚህ ነው፡፡ ያም ካልሆነ ራጅ በማስነሳት ሊታወቅ ይችላል፡፡
ንጋት፡- የሆርሞኑ መዛባት በሰውነታችን ኡደት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምንድነው?
ዶክተር ኢያሱ፡- ሆርሞኑ ሲያንስ ክብደት ይቀንሳል፣ የንቃተ ህሊና ዝቅ ይላል፣ ንቁ አለመሆን፣ ብርድን አለመቻል፣ ያም ሲባል ሌሎች ሰዎችን ሳይበርድ የሆርሞን ማነስ ያለበት ሰው ይበርደዋል፣ ቆዳው ሻካራ መሆን እነዚህ የሆርሞን ማነስ ምልክቶች ናቸው፡፡
ሆርሞን በሚበዛበት ሰዓት ላይ ብዙ ችግሮች ናቸው የሚመጡት፡፡ ለአብነት ዓይን ላይ የሚያመጣው ችግር፣ በሰውነታችን ነርቨስ ሲስተም ላይ (ሴ.ነ.ስ ሴንተራል ነርቨስ ሲስተም) ከእነዚህም ውስጥ እንቅልፍ ማጣት፣ ነጭናጫ መሆን፣ ፀባይ መቀየር፣ ሙቀት አለመቻል፣ ከመጠን ያለፈ ላብ፣ ከፍተኛ የልብ ምት፣ በተለይም ሴቶች የወር አበባ መዛባት፣ የክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎታቸው ጨምሮ እና በልተውም አለመወፈር ሌሎችም ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ንጋት፡- መፍትሄውስ ምን ይሆን?
ዶክተር ኢያሱ፡- በሽታውን ለመከላከል ዋናውና ትልቁ መፍትሄ አዮዲን ጨው በምግባችን መጠቀም ነው፡፡
ሌላው የሆርሞን ማነስ ያለባቸው ሰዎች ሆርሞኑን ማስተካከል ነው፡፡ ሆርሞኑን በመድሀኒት ማስተካከል ይቻላል፡፡ አንዳንዴ ሆርሞን በመስጠት እድገቱን ማስቆም ይቻላል፡፡
ቶክሲክ ወይም ደማችን ላይ አሲዲ የሚረጭ ከሆነ ሁሉም ምርመራ ካለቀ በኋላ የሚረጨውን ሆርሞን መቆጣጠር ይቻላል፡፡
ይህም እንደ የሰው ሊለያይ ይችል ይሆናል። አንዳንድ ሰው ለስድስት ሳምንታት መድሀኒቱን ሊወስድ ይችላል፤ አንዳንዱም ከዚያ በላይ ሊቆይ ይችላል፡፡ መጀመሪያ ከቀዶ ህክምናው በፊት ግዴታ ሆርሞኑን ለመቆጣጠር መድሀኒት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ያም ሆኖ ሰዎች ለቀዶ ህክምና ዝግጁ ላይሆኑ ስለሚችሉ መድሀኒቱን መቀጠል አለባቸው፡፡ የህክምና መርጃዎች ሁለት ወይም ሶስት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አንደኛው በመድሀኒት መቆጣጠር ሲሆን ሁለተኛው አይ መድሀኒቱ ይብቃኝ የሚል ከሆነ የቀዶ ህክምናውን መውሰድ አለበት፡፡
ሶስተኛው በሀገራችን አይሰጥም፡፡ ያም ራዲዮ አዮዲን( ጨረር) ባደጉት ሀገራት የሚደረግ ህክምና ነው፡፡ ያም ለህፃናት እና ለነፍሰጡር እናቶች አይፈቀድም፡፡ በተለይም ቶክሲክ ጎይተር የቀዶ ህክምና እስኪወሰድ ድረስ መድሐኒቱ በፍፁም አይቋረጥም ማለት ነው፡፡ ከቀዶ ህክምናውም በኋላ ለአንድ ሳምንት መድሀኒቱን መቀጠል አለበት፡፡
በተለይም ታካሚው በራሱ ፈቃድ እባጩ ለእይታ ያስጠላል ካለ ወይም ደግሞ መድሃኒት መዋጥ ላይ እየተቸገርኩ ነው ካለም ማውጣት ይቻላል፡፡
ቶክሲክ ጎይተር ከረጅም ጊዜ በኋላ ሰውዬውን በጣም ስለሚጎዳው ያም ማለት ምርመራው፣ የመድሀኒቱ ግዥ፣ ምልልሱ እና የበሽታው ጫና በተለይም ከረጅም ጊዜ ቆይታ መድሀኒቱ ራሱ ጎንዮሽ ጉዳት ስላለው ማቆም ወይም መድሀኒት መቀየር አሊያም ለማቆም ቀዶ ህክምና መደረግ አለባቸው፡፡
ማንኛውንም በሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠሩ እባጮች ጊዜ ሳይሰጣቸው መውጣት አለባቸው። ማንኛውንም እንቅርት መድሀኒት በመውሰድ መጠበቅ ይቻላል፡፡ የካንሰር ምልክት ያለው እንቅርት ግን ምንም ዓይነት ጊዜ ሳይሰጠው በቀዶ ህክምና መውጣት አለበት፡፡
ሰዎች እንቅርት አለ ተብለው ከተነገራቸው ወደ ሀኪም ቤት መሄድ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እንቅርት ፀባዩ አይታወቅም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከተነገራቸውም በኋላ ወደ ህክምና ለመምጣት ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ ያም ህክምናውን እና የሰውየውን ጤና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡
ንጋት፡- እንቅርት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል?
ዶክተር ኢያሱ፡- እንቅርት ከሰው ወደ ሰው በፍፁም አይተላለፍም፡፡ አካባቢ ግን የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በተለይም ለእንቅርት ተጋላጭ የሚሆኑ አካባቢዎች ይስተዋላሉ፡፡
ንጋት፡- እንቅርትን ያለ ቀዶ ህክምና ማጥፋት ይቻላል?
ዶክተር ኢያሱ፡- ምናልባት በልጅነት ዕድሜ ላይ ያለውን እንቅርት በመድሀኒት መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ነገር ግን እባጭ ወጥቶ በደንብ የሚታየውን እንቅርት ግን ያለ ቀዶ ህክምና በምንም ዓይነት ዘዴ ማጥፋት አይቻልም፡፡
ንጋት፡- ከዕድሜ እና ከፆታ አንፃር ተጋላጭነቱስ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ኢያሱ፡- ወንዶች ላይ ዕድሜያቸው 40 አካባቢ ያለው እንቅርት ከባድ ሊሆን ይችላል። ሴቶች ላይ ከ20 እስከ 40 ሊጠቁ ይችላሉ። ተጋላጭነትን በተመለከተ ከወንዶች ይልቅ ግን ሴቶች ተጋላጭ ናቸው፡፡ ሴቶችን ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ምክንያት ኦስትሮጂን የተባለው ሆርሞን ጋር ተያያዥነት ስላለው ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር በሴቶች የተለየ የሚያደርጋቸው ነገር የለውም፡፡
ሰዎች እንቅርት አለብህ ከተባሉ ምን ዓይነት እንቅርት ነው የሚለውን በጊዜ እና በወቅቱ ተመርምረው ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህም ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል፡፡
ንጋት፡- የእንቀርት በሽታ የጎንዮሽ ጉዳት ምንድነው?
ዶክተር ኢያሱ፡- አዎ አለው፡፡ እንቅርት ያለበት ሰው ቶክሲክ ከሆነ ለልብ ድካም ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ልብ ድካም ራሱን የቻለ አንድ በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን እንቅርት ከረጅም ጊዜ በኋላ መቆጣጠር ካልተቻለ እና ሰውዬው ካልታከመ የልብ ድካም ሊያመጣ ይችላል፡፡
ሁለተኛው ዓይናችንን እስከማጥፋት ድረስ ሊያደርስ የሚችል በሽታ ነው፡፡ ሴት ከሆነች የወር አበባዋ በትክክል ላይመጣ ይችላል፡፡ ሌላው የእጅ መንቀጥቀጥ በትክክል መያዝ አለመቻል ያስከትላል። በተመሳሳይም አንዳንድ ሰዎች ምላሳቸው ሊርገበገብ ይችላል፡፡ ይኸ የሆርሞኑ መብዛት ሲኖር ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ሲምፕል ጎይተር ከሆነ ግን ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ካንሰር ተለውጦ የመዋጥና መተንፈስ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ቶክሲክ ሆኖ ሊቀየር ይችላል። ፀጉር መነቃቀልን ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንቅርት ሁሉንም የሰውነት ክፍልና ሜታቦሊዝምን ሊያጠቃ የሚችል በሽታ ነው፡፡ በጊዜ እና በወቅቱ መታከም ግድ ነው፡፡
በጊዜ ወደ ህክምናው ካልመጣን ከራሳችን እስከ እግር ጥፍር ድረስ ያለውን የሰውነት ክፍልን እና ኡደት ሊያጠቃ ይችላል፡፡
በተለይም ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ የመጣ እንቅርት የአየር ቱቦ (Trachea) ተጭኖት ሊዘጋውና መተንፈስ ላያስችል ስለሚችል ሰዎች እንቅርትን በጊዜ ወደ ህክምና ተቋም በመምጣት ቢታከሙት ለታካሚውም ሆነ ለሀኪምም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ህክምናውንም ውስብስብ እና አድካሚ አያደርገውም፡፡ የእንቅርት ቀዶ ህክምና በአማካይ ከ2 እስከ 3 ሰዓት ይፈጃል። ነገር ግን የካንሰር ፀባይ ያለው ከሆነ እስከ ስምንት ሰዓት እና ከዚያ በላይ ሊፈጅ ይችላል፡፡
ንጋት፡- ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት፡፡
ዶክተር ኢያሱ፡- ለህብረተሰቡ ስለ አዮዲን አጠቃቀም ግንዛቤ በመፍጠር በሽታውን መከላከል ተገቢ ነው፡፡ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የእንቅርት ምልክቶችን ካየ ወደ ህክምና ተቋማት መምጣትና የሀኪሞችን ምክር ማግኘት አለበት፡፡ እንቅርት ትልቅም ሆነ ትንሽ የራሱ ባህሪ ስላለው እስኪተልቅ መጠበቅ የለብንም፡፡ ታካሚዎች በጊዜ ወደ ህክምና በመምጣት ሊያስከትል ከሚችለው የጎንዮሽ ጉዳቶች ራሳቸውን መታደግ አለባቸው መልዕክቴ ነው፡፡
ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ኢያሱ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
የልጅነት ፍቅር
መልካም ግብር በኃይማኖት ተቋማት እይታ
“ሰው የሚለኝን ብሰማ ኖሮ፥ ለዛሬ አልበቃም ነበር”