“ቡና አረንጓዴ ወርቃችን ነው” -አቶ መስፍን ቃሬ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ መስፍን ቃሬ ይባላሉ፡፡ የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በቆይታችን በክልሉ የቡና ጥራትንና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች በማንሳት ቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ፡፡

በመለሰች ዘለቀ

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ መስፍን፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ቡና ለሀገራችን ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ እንዴት ይለጻል?

አቶ መስፍን፡- ቡና ለሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አረንጓዴ ወርቃችን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እያስገኘ ያለ ሰብል ነው። ባለፉት ተከታታይ አመታት እድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን 2016 የምርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን ዶለር አስገኝቷል። ይህም በጣም ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት አመት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዓለም አቀፍ ንግድ ከነዳጅ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ቡና በማምረት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ስትሆን፤ ከዓለም አምራች አገራት ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ቡና ጣዕም በተለይም የጫካ ቡና በዓለም ላይ ተወዳጅ በመሆኑ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

የቡና ሰብል የውጭ ምንዛሬ የምናገኝበት ሰብል እንደመሆኑ መጠን እንደ ሀገር የተሻለ ገቢ ማግኘት የምንችልበት እድል ሰፊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቡናን ለዓለም ገበያ በብዛት ከሚያቀርቡ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ብትሆንም ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም አለመገኘቱ ደግሞ ተጨማሪ ስራን ይጠይቃል።

ንጋት፡- በክልሉ የቡና ምርታማነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ መስፍን፡- በክልሉ ቡና ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት የሚመረት ሰብል ነው፡፡ ከመሬት ሽፋን አንጻር ቡና ትልቁን ስፍራ ይይዛል። በክልሉ 170 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ 143 ሺህ ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ ነው። ከምርታማነት አኳያ በምናይበት ጊዜ በዚህ አመት አጠቃላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡

በአንድ ሄክታር የሚገኘው ምርታማነት ባለፈው አመት 9 ነጥብ 5 ኩንታል ነበር። ይህንን ወደ 11 ነጥብ 5 ኩንታል ለማድረስ ግብ አስቀምጠናል፡፡ እሰካሁን በተደረገው የምርት ትመና መሰረት 11 ነጥብ 4 ኩንታል በሄክታር ተገኝቷል፡፡ ይህም ከሀገሪቱ አማካይ ምርት አንጻር ሲታይ የተሻለ ቢሆንም ሞዴል አርሶ አደሮች የደረሱበት ደረጃ ያልደረስን ስለሆነ በቀጣይ አስፍተን መስራት እንዳለብን ያመለክታል፡፡ ሞዴል አርሶ አደሮች በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ እያመረቱ የሚገኙ ሲሆን፤ መደበኛ አርሶ አደሮች ደግሞ 9 ነጥብ 64 ኩንታል በማምረት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በምናይበት ጊዜ ብራዚል 17 ኩንታል በሄክታር፣ ኮሎምቢያ 16፣ ቬትናም 21 ኩንታል በሄክታር የማምረት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ስለሚጠቀሙ ነው ይህን ያህል ምርት ማግኘት የቻሉት፡፡

እኛ ግን ኦሪጋኒክ /ተፈጥሯዊ/ ቡና ወደ አለም ገበያ ስለምናቀርብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወይም ኮምፖስት በመጠቀም ብቻ ነው የምናመርተው። በአግባቡ ኮምፖስትን ተጠቅመው ያመረቱ አርሶ አደሮች ከ15 እስከ 20 ኩንታል እና ከዚያም በላይ እያገኙ ስለሆነ ይህንን ከፍ ብናደርግ አንደኛ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ንጋት፡- የቡና ማሳ ሽፋንን የማሳደግ ተግባር ምን ይመስላል?

አቶ መስፍን፡- ባለፈው አመት የቡና ማሳ ሽፋን 165 ሺህ ሄክታር ነበር፡፡ በዚህ አመት አምስት ሺህ ሄክታር በመጨመር ሽፋኑን ወደ 170 ሺህ ሄክታር ማድረስ ተችሏል፡፡ ክልሉ የመሬት ጥበት ያለበት ቢሆንም በየአመቱ ወደ 28 ሚሊዮን የሚሆን አዳዲስ ችግኝ እየተከልን ነው። በአብዛኛው ያረጁ ቡናዎችን ነቅለን በአዲስ የመተካት ስራ ላይ ትኩረት አድርገን ከ4 እስከ 5 ሺህ ሄክታር ድረስ በአዲስ የማስፋት ስራ ተሰርቷል፡፡ በተለይ ደጋማና ወይናደጋማ አካባዎች ላይ የማስፋት ስራ እየሰራን ነው፡፡

ንጋት፡- የቡና ጥራትን ከማስጠበቅ ረገድ የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለፃሉ?

አቶ መስፍን፡- ትኩረት አድርገን ከምንሰራቸው ስራዎች ዋነኛው ጥራት ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ከሁለትና ከሶስት አመት በፊት የነበረው የቡና ጥራት ደረጃው በጣም ዝቅተኛ ነበረ፡፡ በሂደት ግን ጥራቱ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው።

በ2016 የምርት ዘመን በለቀማ ወቅት በተለይ ጥቅምትና ህዳር ወር ከፍተኛ ዝናብ ስለነበረ ጥራቱ ላይ በተወሰነ መልኩ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ የታጠበ ቡና ከ24 እስከ 72 ሰዓት ድረስ ከተዘፈዘፈ በኋላ ታጥቦ ወጥቶ መድረቅ አለበት፡፡ ነገር ግን ሳይደርቅ ዝናቡ የሚያልፈን ከሆነ የጥራት ደረጃ የሚቀንስበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህም በመሆኑ 94 ከመቶ ቡናችን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ነው የወጣው። 5 በመቶ ደግሞ ሶስተኛ እንዲሁም 1 በመቶ የሚሆነው አራተኛ ደረጃ ነው የወጣው፡፡ የዚህ አመት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ 98 በመቶ እንዲሆን የማድረግ ስራ ነው እየሰራን ያለነው።

ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ በየአመቱ የግብረ ሀይል መድረክ እናዘጋጃለን፡፡ ይህንን መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው የሚመሩት። ግብረ ሀይሉ ጥራትን ባስጠበቀ መልኩ ህገ ወጥነትንና ብክነትን በመከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡

ንጋት፡- የክልሉን የቡና ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?

አቶ መስፍን፡- ለቡና ችግኝ ከዝግጅት ጀምሮ እሰከ ገበያ ድረስ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል። ከምርት ዝግጅት ጥንቃቄ መካከል ደግሞ በሽታን የመቋቋም አቅሙ የተሻለውን፤ አካባቢን መላመድ የሚችል እንዲሁም በጣዕሙ ተመራጭ የሆነ ዝርያ ያስፈልጋል።

አንድ የቡና ማሳ ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ከመጣ የመጀመሪያው አማራጭ አዲስ ችግኝ መትከል ሳይሆን የቡና ዛፎቹን በጉንደላ ማደስ ነው። አዳዲስ የቡና ዛፎች ከመትከል ባለፈ ያረጁትን ምርታማ ለማድረግ በጉንደላ ማደስ ይገባል። ከእድሳት በኋላም ምርታማ ካልሆነ ዛፉን ነቅሎ በተሻለ ዝርያ መተካት ያስፈልጋል።

የድህረ ምርት ጥንቃቄዎች ቡና ከተለቀመ በኋላ አስፈላጊው ሂደት አልፎ እንዲታጠብ ማድረግ ጥራቱን ለመጨመር ይረዳል። የታጠበ ቡናን ደግሞ በንፋስ እና በጸሃይ አማካኝነት ከደረቀ በኋላ ወደ መጋዘን መግባት ይኖርበታል። ነገር ግን አንዳንድ አምራቾች በተገቢው መንገድ ድርቀቱን ያልጨረሰ ቡና በማከማቸት ጥራቱን ሲያጓድሉ ይስተዋላል።

ድርቀቱን ጨርሶ ወደ ማከማቻ የሚላክ ምርት የእርጥበት መጠኑ በመሳሪያ መለካትና መረጋገጥ ይኖርበታል። መሳሪያ በማይኖርበት ወቅት ደግሞ በጥርስ ሲነከስ የሚሰበር እና በስለት አማካኝነት ሲቆረጥ የሚፈናጠር ከሆነ በጥሩ የድርቀት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል። ነገር ግን ፍሬው የመልዘዝ ወይም የመጨፍለቅ ባህሪ ካሳየ ለተጨማሪ ጊዜያት እንዲደርቅ ማድረግ ጥራቱን ይጨምረዋል።

በሌላ በኩል ቡና ሲጓጓዝና ወደ ገበያ ሲላክ በተፈጥሮው ሽታን የመሳብ ኃይሉ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም በተሽከርካሪዎች በሚጫንበት ወቅት ሽታን ከሚያመጡ እንደ ናፍጣ፣ የተለያዩ ቅባቶች፣ ቆዳ እና ቅመማቅመም ከመሳሰሉት ጋር እንዳይነካካ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ ዝናብ በማያስገባ ሸራ ተሸፍኖ መጓጓዝ ይኖርበታል። በአጠቃላይ ቡና ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ ገበያ እስኪወጣ ድረስ ሂደቶቹ ተከታታይ በመሆኑ አንደኛው ሂደት ላይ ችግር ቢፈጠር ልፋትን መና ያስቀራል።

በዚህ መልኩ ጥራቱን ከማስጠበቅ ረገድ በየአመቱ ለባለሙያና ለአርሶአደሮች ስልጠና እንሰጣለን፡፡ አርሶአደሩ ቀይ ቡና ብቻ ለቅሞ ወደ ኢንዱስትሪ እንዲያቀርብ የማድረግ ስራ በተለይ የቀበሌ ግብረ ሀይል አባላት ትልቅ ሚና ነው የሚኖራቸው፡፡

ንጋት፡- በክልሉ ምን ያህል የቡና መፈልፈያ ጣቢያዎች አሉ?

አቶ መስፍን፡- ቡና ኢንዱስትሪ ከቀረበ በኋላ የሚፈጠረውን የቡና ጥራት ችግር ለመፍታት በዚህ አመት 350 የሚሆን ኢንዱስትሪ ኃላፊዎች የታጠበ ቡና አዘገጃጀት መመሪያ ዙሪያ ስልጠና ሰጥተናል፡፡ በክልሉ ወደ 443 የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፡፡

ሁለት ሄክታርና ከዚያ በላይ ማሳ ያላቸው አርሶአደሮች ፈቃድ ወስደው ቡናቸውን ወደ ውጪ እንዲልኩ የማበረታታት ስራ ይሰራል፡፡ ወደ 262 የሚሆኑ አርሶ አደሮች ፍቃድ ወስደው ምርታቸውን ወደ ውጪ መላክ የጀመሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች በዚህ አመት በአለም ደረጃ በተካሄደው ልዩ ባለጣዕም ቡና ውድድር ላይ የተወዳደሩ ሲሆን ከኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ውድድር ካለፉ 40 ተወዳዳሪዎች ውስጥ 34ቱ ቡና አምራች አርሶ አደሮች የሲዳማ ክልል ናቸው፡፡

በዚህ “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” ላይ ከተካሄደው የኦንላይን ጨረታ ሂደት በአጠቃላይ 27 የሲኦኢ የጨረታ ተወዳደሪ አርሶ አደሮች ያቀረቡት ቡናዎች 4 ሺህ 870 የተለያየ ዋጋ የተሰጠ ሲሆን በርካታ ፉክክር ከተደረገ በኋላ አንድ ኪሎ ቡና በ980.64 ዶላር ($445/ፓውንድ) መሸጥ ተችሏል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ በልማቱ ላይ እንዲሳተፍ እያበረታታ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ዋጋ በኢትዮጵያ እስካሁን ከተካሄዱት ውደድሮችም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎችም እጅግ ከፍተኛ እና አዲስ ሪከረድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ባለፈው ዓመት 25 ሺህ 573 ቶን የታጠበና ያልታጠበ የቡና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ የተላከ ሲሆን በዚህ ዓመት 36 ሺህ 100 ቶን የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። ሰሞኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሺንና የእውቅና ፕሮግራም ላይ ክልሉ እውቅና አግኝቷል፡፡

ንጋት፡- የቡና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ከመተግበር ረገድ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል?

አቶ መስፍን፡- የቡና አመራረት የራሱ የሆነ ፓኬጅ አለው፡፡ ፓኬጁ በዋናነት የተለያዩ ተግባራትን የያዘ ነው፡፡ አንደኛውና ዋናው በሽታን መቋቋም የሚችልና ምርታማ የሆኑ ዝርያዎችን መጠቀም ነው፡፡ ከምርምር የወጡ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የማስፋት ስራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ በሌላ በኩል ምርታማነትን ከሚያሳድጉ ፓኬጆች አንዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ነው፡፡ በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ነው እየሰራን ያለነው፡፡ እያንዳንዱ አርሶ አደር ኮምፖስት አዘጋጅቶ እንዲጠቀም የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው። በተለይ ኢንዱስትሪዎች ከቡና ተረፈ ምርት ኮምፖስት እንዲያዘጋጁ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል ያረጁ ቡናዎችን በመጎንደል የማደስና ተጎንድለውም ውጤታማ የማይሆኑ ቡናዎችን ነቅሎ በአዲስ የመተካት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ሌላኛው ፓኬጅ ደባል ሰብሎችን መትከል ነው፡፡ ቡና በተለይ ጥራጥሬ ሰብሎችን በውስጡ ሲተከል የበለጠ ምርታማነቱን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በተለይ ቦለቄ፣ ባቄላ አተርና የመሳሳሉትን በቡና ውስጥ የመዝራት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቡና በተፈጥሮ ጥላ ስለሚፈልግ ተስማሚ የሆኑ የጥላ ዛፎችን እንደ ግራር፣ ኮርች፣ ዋንዛ፣ እንሰት የመሳሰሉ ሀገር በቀል ዛፎችን መትከል ተገቢ ነው። በቡና ውስጥ እርጥበትን ሊያቆዩ የሚችሉ ስትራክቸሮችን በመስራት ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፡- በቡና ጥራት ላይ ተጽእኖ ሊያደርስ የሚችለውን ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ መስፍን፡- በተለያዩ ሁኔታዎች ህገ ወጥነት ሊስፋፋ ይችላል፡፡ ቡና ወደ አጎራባች ክልሎች ጭምር በህገ-ወጥ መንገድ የመዘዋወር ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህንን ለመከለከል የቀበሌ፣ የዞን፣ የክልል ግብረ ሀይል ተቀናጅተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በተለይም የጸጥታ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ህገ ወጥነትና ብክነትን በመከላከል ጥራት ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ አመት በተደረገው ቁጥጥር ከ22 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ እሸት 175 ኪሎ ግራም መርቡሽ /ደረቅ/ ቡና መያዝ ተችሏል፡፡ በቀጣይም ህገ-ወጥ የቡና ዝውውርና ንግድን የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ንጋት፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካልዎት?

አቶ መስፍን፡- የቡና ምርትና ምርታማነትንና ጥራትን ከማስጠበቅ ረገድ አመራሩ የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት አለበት፡፡ ምርታማነት ላይ ዘንድሮ ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን አቅደን የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብተናል፡፡

በዋናነት ልዩ ትኩረት አድርገን የቴክኖሎጂ መንደር በመፍጠር ቡናን በክላስተር የማምረት ስራም ተጀምሯል፡፡ አርሶ አደሩም የቀረበለትን ፓኬጅ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ይህንን ማድረግ ከተቻለ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል የሚል መልዕክት አለኝ፡፡

ንጋት፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ መስፍን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡