“ከፈተና ውጪ የሆነ ስኬት የለም” –  ቃልኪዳን ሸዋረጋ

በደረሰ አስፋው

ችግሮችን በጽናትና በትዕግስት ማለፍ ልዩ ባህሪዋ ነው፡፡ በዚህ ባህሪዋ በህይወቷ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራለች፡፡ ዛሬም በምታሳየው ትጋት ብዙዎች “ንብ” ናት ይሏታል በጣፋጭ ምግቦቿም አድናት አግኝታለች፡፡ በርካታ ደንበኞችንም አፍርታበታለች፡፡

የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ የሆነችው የዛሬዋ እቱ መለኛችን በንግድ ከተሰማሩ ቤተሰቦች የተገኘች ናት፡፡ በልጅነት የጀመረችው የጉልት ንግድም ለዛሬ ስራዋ ተሞክሮ ሆኗታል፡፡ “የሰው እጅ አይቶ መኖር ለኔ የህይወት መርሆ አይደለም፤ ይልቁንስ ሰርቶ እራስን መቻል ተቀዳሚው ተግባሬ ነው” የሚል አስተሳሰብም አላት፡፡ እነዚህ ክህሎቶቿ ዛሬ ለደረሰችበት የህይወት ምዕራፍ ስንቅ እንደሆናት ነው የተናገረችው፡፡

የባለታሪካችንን ትጋት ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ የምግብ ቤቱ ተጠቀሚ ደንበኞቿ የሚሰጡት አስተያየት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ “ለሌሎች ሴቶች መነሳሳትን የፈጠረች ልክ እንደ ንብ ትጉህ ናት በማለት። እሷ ሰርታ የምታቀርብልን ምግብ ይጣፍጣል። ለመለወጥ የምታደርገውን ትጋት እናደንቃለን። የሚያጋጥሟትን ተግዳሮቶች ሁሉ በብልሃት የምታልፍ ናት” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ወላጅ አባቷ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ነበሩ። ታላላቅና ታናናሽ እህትና ወንድሞቿ ሳይቀሩ በመርካቶና አካባቢው በንግድ የተሰማሩ ናቸው። ከቤተሰብ በወረሰችው እና እሷም ከልጅነቷ ከትምህርት ቤት መልስ የጉልት ንግድን ባህል አድርጋ ላደገችው መለኛዋ እንስት ይህ ልምዷ ለዛሬው ህይወቷ መንገድ ከፍቶላታል፡፡

ወ/ሮ ቃልኪዳን ሸዋረጋ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ነው። እድገቷ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ። ወላጅ አባቷ በስራ ምክንያት አዲስ አበባ ይኖሩ ስለነበር እሳቸውን ተከትላ በመሄድ እድገቷን ያደረገችው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ አስከ 9ኛ ክፍል አዲስ አበባ ካራማራ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡

ትምህርቷ ግን በትዳር ምክንያት ከ9ኛ ክፍል አልተሻገረም፡፡ ወደ ሀዋሳ የመጣቸውም በትዳር ምክንያት ነው፡፡ ትዳርና የሀዋሳ ቆይታዋ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ የኑሮ ውጣ ውረድ የመጋፈጡ እጣ ፈንታ የወደቀውም በሷ ላይ ሆነ፡፡ ካለ ስራ ቤት መዋል ማደር ለቃልኪዳን ምቾትን አልፈጠረላትም፡፡ ስራ ባህሌ ነው ለምትለው ባለታሪካችን ያልተለመደ ባህሪ በመሆኑ ያስጨንቃት ነበር፡፡

“ከልጅነቴም ስራን ተለማምጄ ያደኩ ነኝ፤ ለሰዎች ትንሽ መስላ የምትታየው ጉልት ንግድ ለኔ ልዩ መልክ ነበራት፡፡ ባለቤቴ ባለው አቅም ሊያስተዳድረኝ ቢችልም እኔም በአንድ በኩል ማገዝ አለብኝ የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ፡፡ የሰው እጅ ከማየት ሰርቶ መለወጥ ይሻላል አልኩ፡፡ ስራ ፈት ሆኖ መቀመጥ ከተለማመድኩት የስራ ባህል ውጪ በመሆኑ የስራ አማራጮችን እንድመለከት አስገደደኝ” በማለት በሀዋሳ የነበራትን የስራ አጀማመርና ህይወት ተረከችልን፡፡

ሀዋሳ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነው የባልትና ውጤቶች ንግድ ነው፡፡ ይህ አላዋጣ ሲላትም በመንገድ ዳር የሻይ ቡና ስራ ተሰማራች፡፡ የጀመረችው የሻይ ቡና ስራም ገበያው ሰምሮ ሁለት ሰራተኞችንም ቀጥራ ታሰራ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ስራ ከ2 ዓመት በላይ አልተሻገረችም። የምትሰራበት ቦታ ምቹ ባለመሆኑ የሻይ ቡና ስራውን አቁማ በጎዳና ምግብ “እርጥብ” በመስራት ላይ ተሰማራች፡፡ ለስራው የሚሆን ግብአትም ሆነ የገንዘብ አቅም ስላልነበራት ከሌሎች ሰዎች ጋር በጋራ ነበር የምትሰራው፡፡

እሷ በጉልበቷ እነሱ ደግሞ በገንዘባቸው በሚሰሩት ስራ ትርፉን በጋራ ይካፈሉ ነበር። ስራው ግን በተመኙት ልክ ውጤታማ አላደረጋቸውም። የሽርክና ንግዳቸውም ፈርሶ የሚሰሩበት ቁሳቁስ በገንዘብ ታስቦ ቃልኪዳን ከፍላ እንደትረከበው ሆነ፡፡ ቃልኪዳን ለብቻዋ መስራት የምትችልበት ዕድል ቢፈጠርም ስራው ግን አዋጭ አልሆነላትም። ቢሆንም ይህ ስራ አሁን ወደ ምትሰራው የምግብ ቤት ስራ አመላከታት። በምግብ ቤት ስራዋ 2 ዓመታትን እንደቆየች የምትገልጸው ቃልኪዳን ከቀድሞው ይልቅ ውጤታማ እንዳደረጋትም ነው የምትገልጸው፡፡

በከፈተችው “አሀዱ ቁርሳ ቁርስና ምግብ ቤት” የለም የሚባል ምግብ እንደሌለ ታነሳለች። ሰው ጠይቆ የሚያጣው የምግብ አይነት የለም። ከሷ በተጨማሪ ሁለት ሰራተኞችን  ታሰራለች። “ህይወት በራሷ ትምህርት ቤት ናት” ያለችው ቃልኪዳን “ጥንካሬን ህይወት አስተምራኛለች” ነው ያለችው፡፡ ትዳር ስትመሰርት አልጋ ባልጋ የሆነ ህይወት እንዳልገጠማት አስታውሳ ያጋጠማትን ተግዳሮት ለማሸነፍ ግን ጥረት ታደርግ እንደነበር ታወሳለች፡፡ በሰዎች አሉባልታ ሳትንበረከክ የነገን ተስፋዋን ብቻ በመመልከት ችግሯን አሸነፈች። ለዚህም የሷ ቁርጠኝነት የላቀውን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ይህ የዓላማ ጽናትም አቅም ሆናት፡፡ ዛሬ ላይ ጽናቷ ሰምሮ የትዳር አጋሯም በሌላ የግል ስራ ተሰማርቶ ውጤታማ እንደሆነና ህይወታቸው ያማረ እንደሆነ ነው የተናገረችው። ከሰው ቤት ተቀጣሪነት ወጥቶ የራሱን ግሮሰሪ ከፍቶ በመስራት ላይ ነው፡፡ የትናንቱ ትእግስት ለዛሬው ስኬት እንዳበቃው ነው የገለጸችው፡፡

የሁለት ልጆች እናት መሆኗን የምትገልጸው ቃልኪዳን ነገን በማየት የተሻለ ነገር ለማድረግ ሁል ጊዜ የምትታትር ናት፡፡ አሁን የምትሰራበት ምግብ ቤት በኪራይ ነው፡፡ በወር የውሃና መብራት ወጪን ጨምሮ እስከ 4 ሺህ ብር ትከፍላለች፡፡ ወደፊት ይህንኑ ስራ የማሳደግ፣ የማስፋፋት እቅድ አላት፡፡ የተሻለ ቤት ተከራይታ ቅርንጫፍ ከፍታ የመስራት ውጥን አላት፡፡ በዘርፉ የሰለጠኑ ሰራተኞችን ቀጥራ ወደ ሆቴል በማሳደግ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆንና ደንበኞቿን ለማገልገል ትመኛለች፡፡

ቃል ኪዳን በዚህ ስራ መሰማራቷ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳስገኘላት ነው የተናገረችው። የራሴ የምትለው የስራ ባለቤት መሆኗ አንዱ ነው። ልጆችን በሚገባ ማስተማርም ሌላው ጥቅም ነው ትላለች። ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ልምድም አግኝታበታለች። ባለራዕይ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ከ20 ሺህ ብር በታች መነሻ ካፒታል የጀመረች ቢሆንም ዛሬ ግን ካፒታሏ አድጓል። መቆጠብ የምትችልበት አቅም ፈጥራለች። ስራው ከብዙ ሰዎች ጋርም አስተዋውቋታል፡፡

“ሰው ለኪሳራ አይሰራም በዚህም በጣም ተጠቃሚ ነኝ፡፡ የምግብ ቤት ስራ አድካሚ ቢሆንም በድካም ሳልሸነፍ ከዚህ የበለጠ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት አደርጋለሁ” ነው ያለችው፡፡ ቀጣይነት ያለው ቋሚ ደንበኞችን ለመፍጠር ጥረት ወሳኝ እንደሆነ ገልጻ ለዚህም ደንበኞቿን በስስት እንደምትንከባከባቸው ነው የተናገረችው፡፡

“ሴቶች ትዳር ከያዙ በኋላ ቤት ላይ ብቻ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የቤተሰብ ኃላፊነት፣ ተከትሎ የሚመጣ የእናትነት ህይወትም ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ግን ሊያዘናጋቸው አይገባም። ይህ ተጽእኖ በኔም ላይ ደርሷል፡፡ ችግሩን ግን ተጋፍጨ አልፌዋለሁ፡፡ የቤቱንም ሆነ የውጭ ስራ በአግባቡ መምራት የምንችልበት የጊዜ አጠቃቀም መዘርጋት ይገባል፡፡ የውጭውንም ሆነ የቤቱ ስራ እንዳይበላሽ አድርገን መምራት የምንችልበት አስተሳሰብ መፍጠር አለብን ብላለች፡፡

“ቤቴ እያልን ወደ ኋላ የምንቀር ከሆነ የምንመኘውን ለውጥ ማምጣት አንችልም። በተፈጥሮዬ ሰው የሚሰጠኝ ገንዘብ አያረካኝም። በልጅነቴ ነግጄ ገንዘብ መቁጠር ስለጀመርኩ በሰው ትከሻ ላይ መንጠልጠል አልመኝም፡፡ እኛ ሴቶች በራሳችን እንችላለን የሚል አስተሳሰብ መፍጠር አለብን፡፡ ወጥቶ በመስራት ችግርን ማሸነፍ ይገባል፡፡ እኔ ያለኝን ልምድ ለሌሎች በማካፈል በርካታ ሴቶች ወደ ስራ እንዲያማትሩ አድርጌያለሁ፡፡ በራስ መተማመን የሚጎለብተው ሰርቶ የራስን አቅም በመፍጠር መሆኑን እመክራለሁ በማለትም አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ከፈተና ውጪ የሆነ ስኬት የለም፡፡ ይሁን እንጂ የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች ማሸነፍ የምችልበትን ጥበብ ፈጣሪ ሰጥቶኛል፡፡ ከብዙ ሰው እንደመዋሌ መጠን ብዙ አይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ያጋጥማሉ፡፡ የሚያጋጥመኝን ጥሩም ይሁን መጥፎ ባህሪ በማሸነፍ ለራሴ ጥቅም አውለዋለሁ። በዚህም ነገሮችን በመጽናትና በትዕግስት ማሸነፍ ይቻላል ብላለች፡፡