የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በሸማቾች ማህበር የሚቀርቡ ምርቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሸማቾች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሚዛን አማን ከተማ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በሸማቾች ማህበር የሚቀርቡ ምርቶች በቀጣይም ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሸማቾች ተናገሩ።

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ንግድ ጽ/ቤት በበኩሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጿል።

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በሰንበት ገበያ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሸማቾች እንደገለፁት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በሸማቾች ማህበር የሚቀርቡ ምርቶች የተሻለ ቢሆንም ከመደበኛ የገበያ ዋጋ ጋር ተቀራራቢነት ያለውና በቀጣይም ተጨማሪ ማህበራትን በመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የኑሮ ውድነትና ገበያን ለማረጋጋት በሚደረገው ጥረት የተለያዩ ምርቶችን ካቀረቡት መካከል ወይዘሮ ሀውለት ይማም እና የብርሃን ሁለገብ ማህበር ሰብሳቢ ቄስ አሸናፊ ተገኝ በሰጡት አስተያየት የእንሰሳት ተዋፅኦ፣ አትክልትና የፋብሪካ ውጤቶች ዕንቁላል፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ስኳር የመሳሰሉትን ከተለያዩ አከባቢዎች በማምጣት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናገረዋል።

የግብርናና የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ሲያቀርቡ የምርት አቅራቢዎችና ሸማቾች ከንግድ ተቋማት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የዋጋ ተመን አውጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ የገለፁት የምርት አቅራቢ ሸማቾችም በቀጣይም በደቡብ ቤንች በጉራፈረዳና በተለያዩ አካባቢ ካሉት አባላት ጋር እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በሚዛን አማን እየተካሄደ ባለው በሰንበት ገበያ የግብርናና የእንሰሳት ተዋፅኦ ምርቶች እየቀረቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጠነኛ ቅናሽ መኖሩ በቀጣይ ማህበራትን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ በከተማ አስተዳደሩ የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ሄኖክ በላቸው ገልፀዋል።

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ንግድ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታቻ በበኩላቸው በበዓላት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር ቀደም ተብሎ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናገረዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን