“ዋናው ራስን ማሳመን ነው” – ወ/ሮ መኪያ ኑረዲን
በጋዜጣው ሪፖርተር
አካል ጉዳተኝነት፣ ሴትነት፣ ድህነት፣ የህረተሰቡ አመለካከት ተደማምረው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ፈተና ሆነውባት አልፈዋል፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁማ ዩኒቨርስቲ ገብታ የመማር ፍላጎት ቢኖራትም፤ በቤተሰቦቿ አቅም ውስንነት ምክንያት ደግሞ ትምህርቷን ዘልቃ መሄድ አልቻለችም፡፡
እድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ እንደ እድሜ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ገብታ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የ3ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ወድቃ እግሯ ተሰበረ። በዚህም ምክንያት አንድ እግሯ ላይ ጉዳት ደረሰባት፡፡ ለአንድ ዓመት ያክልም ትምህርቷን አቋርጣለች፡፡ በወቅቱ ህክምና የተከታተለች ቢሆንም ምንም ለውጥ አላገኘችም፡፡
ስታገግም ተመልሳ ያቋረጠችውን ትምህርት ቀጠለች፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ቀቤና ልዩ ወረዳ እድገት በር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተንፏቀቀች (በመቀመጫዋ) ተምራ አጠናቃለች፡፡ ጥረቷን ያዩ አካላት የተሻለ ህክምና እንድታገኝ አመቻቹላት፡፡ ባገኘችው ዕድል አዲስ አበባ ቼሻየር የአካል ጉዳተኞች ማዕከል ውስጥ ህክምና ተከታትላ የእግር ድጋፍ ተደርጎላታል፡፡ 2ተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ጎሮ አጠቃላይ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡
መሰናዶ የሚያስገባት ውጤት ብታመጣም መማር ግን አልቻለችም፡፡ አባቷ በህይወት ባለመኖራቸው ምክንያት ኑሯቸው ላይ ጫና ተፈጠረባቸው፡፡ ይህም ትምህርቷን ለመማር ሌላ ፈተና ሆነባት፡፡ በዚህም 11ኛ ክፍል መማር ጀምራ አቋረጠች፡፡ ወደ ኋላ ተመልሳ በ10ኛ ክፍል ውጤቷ በዲፕሎማ መርሃ-ግብር ለመማር ወሰነች፡፡ ተወዳድራም አለፈች፡፡ ከዚያም ሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በላብራቶሪ ትምህርት ክፍል ለ3 ዓመታት ተከታትላ በ2011 ዓ.ም ተመርቃለች፡፡ አሁን ላይ ቀቤና ልዩ ወረዳ በሚገኝ ሌንጫ ጤና ጣቢያ የላብራቶሪ ባለሙያ ሆና እያገለገለች ሲሆን ጎን ለጎን ድግሪዋንም በላብራቶሪ እየተማረች ትገኛለች፡፡
የዛሬ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን መኪያ ኑረዲን ትባላላች፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ጸሀፊ እና የቀቤና ልዩ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ ነች። ተወልዳ ያደገችው ቀቤና ልዩ ወረዳ ሌንጫ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ናት፡፡
ወ/ሮ መኪያ ስትማር የገጠማትን እንግልት ስታነሳ፡- “የአመለካከት ችግሩና ፈተናው የሚጀምረው ከቤት ነው፥ ከዚያም ማህበረሰቡ ይቀጥላል። በአካባቢዬ የተለያዩ ስያሜዎችን ይሰጡኝ ነበር፡፡ እናቴን መውጫ መግቢያ ያሳጧት ነበር÷ ‘ተምራ የት ልትደርስ ነው?፣ ምን ለመሆን ነው እየተንፏቀቀች የምትማረው እና የቤተሰቦቿ እርግማን ነው እንዲህ ያደረጋት’ የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ክብር ነክ ቃላቶችን ለጆሮዬ እስኪከብደኝ ድረስ ለእናቴ ሲሏት እሰማ ነበር፡፡ እኔ ምንም አይመስለኝም ነበር:: እናቴ ግን ታፍርብኝ ስለነበር ከቤት ይዛኝ መውጣት እንኳን አትፈልግም ነበር፡፡
“በዚህም በጣም ይሰማኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የህብረተሰቡ ተጽዕኖ እልህ ውስጥ እንድገባ አደረገኝ:: ተስፋ ሳልቆርጥ ዝናቡም፣ ጸሀዩም፣ ጭቃውም ሆነ አሉታዊ አመለካከቶቹ ቢፈራረቁብኝም ተቋቁሜ በመማር እዚህ ደርሻለሁ፡፡
“ኮሌጅ ስማር የኢኮኖሚ ችግሮች ይገጥሙኝ ነበር፡፡ ስመረቅም የተሰማኝን ስሜት መቼም አልረሳውም፡፡ ደስተኛ አልነበርኩም፤ በዕለቱ እያለቀስኩ ነበር፡፡ በዕለቱ ጓደኞቼ አዳዲስ ልብስ ለብሰው ሲወጡ የበታችነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር” ስትል ስትመረቅ ያጋጠማትን የሀዘን ስሜት አጋርታናለች፡፡
በተመሳሳይ ሥራ ለማግኘት የገጠማትን ስታወሳ፡-
“ተመርቄ ስመጣ ጥሩ ውጤት ነበረኝ። ማስታወቂያ ወጥቶ ስወዳደር ግን አትችይም ተባልኩኝ፡፡ ለሚመለከተው አካል ጉዳዬን አቅርቤ ለመብቴ ብዙ ተሟግቻለው። ምክንያታቸው የነበረው አካል ጉዳተኛ ናት መሥራት አትችልም እና እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዳ አትሰራም፥ የሚሉ እዚህ ግባ የማይባሉ ነበሩ” ትላለች፡፡
“አንዴ አስገቡኝ እንጂ ሠርቼ አሳያችኋለሁ፡፡ እስከ ቀበሌ ድረሰ ወርጄ አሰራለሁ፤ ትራንስፖርት አመቻቹልኝ እያልኩ ለረጅም ጊዜ ተከራክሬ ሥራ ተቀጥሪያለሁ” ስትል ሥራ ለማግኘት ከባድ ውጣ ውረድ መጋፈጧን አጫውታናለች። ወ/ሮ መኪያ ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች ቢገጥማትም ተከራክራ መብቷን አስከብራለች፡፡
“ከተቀጠረኩ በኋላም ፈተናው አላበቃም። የተሰጠኝን ስራ ሠርቼ ባሳያቸውም ሠራች አይሉኝም፡፡ ብዙ የሚመጡ ጥቅማ ጥቅሞችን ያሳጡኛል፡፡ በዚህም የተነሳ በስራዬ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ሞራሌን የሚነኩ ነገሮች ያሳዩኛል። እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ አንዱ ቢከፋብኝም ሌላው ጥሩ እየሆነልኝ የቻልኩትን ያህል እየሰራው እገኛለሁ፡፡ መቼም ቢሆን ለመብቴ እከራከራለሁ፡፡ ለየትኛውም ነገር የራስ ጥረት ያሥፈልጋልና በራሴ ጥረት ተምሬ ራሴን በመቻሌ ራሴን አደንቃለሁ” ስትል በልበ ሙሉነት ትናገራለች፡፡
በቀጣይ “አላህ ቢያሳካልኝ÷ ከዚህ በበለጠ ተምሬ በሙያዬ ህብረተሰቡን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ ምንም ነገር እንዳይገድበኝ ራሴን አሳምኜ ከግቤ እደርሳለሁ ብዬ አስባለሁ” ስትል የተናገረችው ተስፋ ሰንቃ ነው፡፡
“አካል ጉዳተኝነት ከምንም አይገድበንም። ሴትነትና አካል ጉዳተኝነት ሲደመር በጣም ሊከብድ ይችላል። ሆኖም ግን ህብረተሰቡ አካል ጉደተኞችን በብዙ መልኩ ከደገፈ ወደ ፊት ይመጣሉ፡፡ በአሉባልታና ወሬ ብዙ ጓዳ የቀሩ እህቶችና ወንድሞች አሉ፤ ለእንደዚህ ዓይነት አሉታዊ ነገሮች ቦታ ባይሰጡ ጥሩ ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወት ሲኖር ብዙ ነገር ሊደርስበት ይችላል፡፡ ለደረሰበት ነገር ራሱን አሳምኖ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ በመማርና በመስራት ራስን መቻል ያስፈልጋል፡፡
አካል ጉዳተኞች አቅም ካገኘን ህብረተሰባችንን ማስተማር እንችላለን፡፡ ለህብረተሰቡ ራሳችን ግንዛቤ በመፍጠር ለውጥ እንዲመጣ የበኩላችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንሰራለን። በተለይም ክብረ ነክ ቃላትን እንዳይጠቀሙ ቤተሰቦቻችንን፣ ህብረተሰባችንን ብሎም ሀገራችንን ለመለወጥ ራሳችን ግንዛቤ መፍጠር እንችላለን” ስትል ምክሯን ለግሳለች፡፡
የወይዘሮ መኪያ የህይወት ተሞክሮ ብዙዎችን ሊያስተምር የሚችል ነው። አትችልም እየተባለች ለመቻል ጥረት ማድረጓ፤ ምንም ደጋፊ በሌለበት ጠንክራ መገኘቷ የግል ጥንካሬዋን የሚያሳይ ነው። ጠንካራ በመሆኗ የገጠማትን ፈተናዎች ተቋቁማ ትልቅ ደረጃ ደርሳለች። ያለፈችበት መንገድ ነገም ለሚገጥማት ማንኛውም እንቅፋት እጅ እንደማትሰጥ ያሳያልና ብዙዎች ሊማሩበት ይገባል እንላለን።
More Stories
“ከፈተና ውጪ የሆነ ስኬት የለም” – ቃልኪዳን ሸዋረጋ
“እንቅርት ሁሉንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ የሚችል በሽታ በመሆኑ በጊዜ መታከም አለበት” – ዶክተር ኢያሱ ኤሊያስ
የልጅነት ፍቅር