“ነፍሰ ጡር እያለሁ የማህፀን በር ካንሰር እንዳለብኝ ተረዳሁ”
በደረጀ ጥላሁን
ዶሮቲ ማሳሳ በማላዊ በየዓመቱ በማህፀን በር ካንሰር ከሚጠቁ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሴቶች አንዷ ነች፡፡ የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ዶሮቲ ለቢቢሲ እንደተናገረችው የ13 ሳምንታት ነፍሰ ጡር ሆና የማኅፀን በር ካንሰር እንዳለባት ሐኪሞች ካረጋገጡ በኋላ እነዚህ ሁለት ነገሮች አብረው እንደማይሄዱ ነግረውኛል ብላለች፡፡
በማላዊ ያሉ ዶክተሮች ካንሰርን ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንደምትችል÷ ነገር ግን ይህ እርግዝናን እንደሚያቆም ወይም የኬሞቴራፒ ሕክምና ሊደረግላት እንደሚችል ገልጸው ሕፃኑ ግን አካል ጉዳተኛ ሆኖ እንዲወለድ ያደርገዋል ብለው ነግረዋታል፡፡
እሷም ህፃኑ እስኪወለድ ድረስ ኪሞቴራፒን መርጣለች፡፡ ይሁን እንጂ ኬሞቴራፒው እና ቀዶ ጥገናው ቢደረግላትም ካንሰሩን ለመፈወስ አሁንም ተጨማሪ ህክምና ያስፈልጋታል፡፡ ይሁንና ህክምና እስከዚህ አመት መጀመሪያ ድረስ በማላዊ አልነበረም።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች (ኤም.ኤስ.ኤፍ) የካንሰር ሕዋሳትን ለማጥፋት የራዲዮቴራፒ ሕክምና እንዲወስዱ በኬንያ ናይሮቢ ሆስፒታል ከተወሰዱት 30 ሴቶች ጋር ተቀላቅላለች። ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፕላን ትጓዝ ስለነበር በጣም ተጨንቃ ነበር፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው እ.ኤ.አ. ከ2022 ጀምሮ ለማህፀን በር ካንሰር ህክምና ከማላዊ ወደ ኬንያ ከተወሰዱ 77 ታካሚዎች መካከል አንዷ ዶሮቲ ማሳሳ ነች።
ማላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ አይነት ማሽኖችን ያገኘችው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ካንሰር ያለባቸው ሴቶች ለህክምና ወደ ውጭ አገር መሄድ አይኖርባቸውም፡፡
ከዩናይትድ ኪንግደም ነፃነቷን ካገኘች ከስልሳ ዓመታት በኋላ÷ ማላዊ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ የመጀመሪያውን የሬዲዮቴራፒ ሕክምና ማሽንን በግል ባለቤትነት በተያዘው ኢንተርናሽናል ብላንቲር የካንሰር ማእከል ተቋቁሟል፡፡ ተጨማሪ ማሽኖች በሰኔ ወር የደረሱ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ውስጥ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ይነገራል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ሀያ የሚሆኑት ካንሰርን ለመዋጋት ወሳኝ የሆነውን የራዲዮቴራፒ ህክምና ማግኘት አይችሉም።
ይህ ማለት ታካሚዎች ለህክምና ውድ እና አድካሚ ጉዞዎችን እንዲያደርጉ ይገደዳሉ፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በአለም አቀፍ ደረጃ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በሴቶች ላይ የሚከሰት ካንሰር ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 2022÷ 660 ሺህ አዳዲስ ታማሚዎች እና 350 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን የአለም ጤና ድርጅት (WHO) ገልጿል።
እንደ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ በ2018 የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ካለባቸው 20 ሀገራት ከአንዱ በስተቀር ሁሉም አፍሪካ ውስጥ መሆናቸውን አመላክቷል።
ለበሽታው መከላከያ የሚሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባቶችን (HPV) ማግኘት ባለመቻሉ በቂ ምርመራ እና ህክምና እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡
የንግስት ኤልዛቤት ማእከላዊ ሆስፒታል (QECH) የማላዊ ጥንታዊ እና ትልቁ በመንግስት ባለቤትነት የተያዘው የህክምና ማዕከል ሲሆን እጅግ በጣም ብዙ የማህፀን በር ካንሰር ታማሚዎችን ከመላ አገሪቱ ይቀበላል።
የሆስፒታሉ የጽንስና የማህፀን ሐኪም ዶክተር ሳሙኤል ሜጃ የማህፀን በር ካንሰር ለአብዛኞቹ የቀጣናው ሀገራት ትልቅ ችግር ነው ይላሉ።
“የምርመራው ደካማ ተደራሽነት እና ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ የአፍሪካ ክፍሎች ላይ እየደረሰ ያለው የኤች.አይ.ቪ በሽታ ሁኔታውን አባብሶታል” በማለት ይገልፃሉ።
ተሰናባቹ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኢቲ እንዳሉት በአለም አቀፍ ደረጃ 23 በመቶውን የሟቾችን ሞት የምትይዘው አፍሪካ ነች።
እነዚህን አስከፊ አሀዛዊ መረጃዎች ለመቀልበስ አፍሪካ የማህፀን በር ካንሰርን በሚያመጣው ኤችፒቪ (HPV) ላይ ልጃገረዶችን ለመከተብ ሰፊ ዘመቻዎችን እያካሄደች ነው።
ከዚህ አኳያ ሌሴቶ 139 ሺህ ሴት ልጆችን የኤችፒቪ ክትባት በመስጠት 93 በመቶ ሽፋን ላይ ደርሳለች። ነገር ግን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በማህፀን በር ካንሰር ዙሪያ ያለው መገለል እና የግንዛቤ ማነስ የሚከተቡትን ሰዎች ቁጥር አነስተኛ አድርጓል።
ወይዘሮ ማሳሳ አሁን በማላዊ ወደሚገኘው ቤቷ ተመልሳለች። በኬንያ የተደረገላት ህክምና አዲስ የህይወት ዘመን ፈጥሮላታል። ፀጉሯ አድጓል፣ ልጇን ጀርባዋ ላይ አድርጋ መዞር፣ ከብቶቿን መንከባከብ እና ስራ መስራት ትችላለች።
አሁን የማኅጸን በር ካንሰር እንደሚታከም እና ክትባቱ ሌሎች ሴቶች ከበሽታው እንዲድኑ እንደሚረዳ ስለምታውቅ ልጇን ስለማስከተብ ጥርጣሬ እንደሌላት ተናግራለች። “የማህፀን በር ካንሰር ከባድ ደረጃ ላይ አድርሶኝ ነበር÷ እና ሴት ልጄም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲገጥማት አልፈልግም” ትላለች፡፡ “ያኔ በነበርኩበት እና አሁን ባለው ሁኔታ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። በመፈወሴ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው