ደም በመለገስ በደም ዕጥረት የሚሞቱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ እንደሚገባ በደም ባንክ የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጥሪ አቀረበ

የሆሳዕና ቅርንጫፍ ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባሶሬ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በ2016 በጀት ዓመት 9ሺ 490 ዩኒት ደም በመሰብሰብ የዕቅዱን 85 በመቶ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የደም ባንኩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከየም ዞንና ምስራቅ ጉራጌ ዞን በስተቀር ለሁሉም አከባቢዎች የሚያቀርብ በመሆኑ የተሰበሰበው ደም ካለው የደም ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል።

በተለይም ትምህርት ቤቶች በክረምት ተዘግተው በመቆየታቸው በተማሪዎች ክበባት አማካኝነት የሚሰበሰበው ደም ባለመኖሩ የደም ዕጥረት ባለበት ወቅት የወባ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨቱ በደም ዕጥረት የሚሞቱ የእናቶችና ህጻናት ቁጥር  እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ በኩል ያለው የግንዛቤ እጥረት በሚፈለገው ልክ ለደም ለመሰብሰብ አለማስቻሉንም አነስተዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ደም ባንኩ ለሆስፒታሎች በሚያቀርበው የደም አቅርቦት ላይ ዕጥረት እንዲከሰት ማድረጉንም ገልጸዋል።

ደም መለገስ የደም ዝውውር እንዲኖር በማድረግ፣ በኩላሊትና ጉበት የሚከሰት የጤና ጫና መቅረፍና  የልብ ምትን በማስተካከል ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ቅርንጫፍ ደም ባንኩ በተያዘው 2017 በጀት ዓመት 16ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዱንም  ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ደም በመለገስ በደም ዕጥረት የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:-ሳሙኤል መንታሞ ከሆሳዕና ጣቢያችን