የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በመድሀኒት ረገድ የሚታየውን ህገ-ወጥነትና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መከላከል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

በቢሮው የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የ2016 በጀት አመት አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ዙርያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሶንቆ እንደገለጹት፥ ባለፈው በጀት አመት የመድሀኒት ችርቻሮ ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት መከናወኑንና የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ስራው በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እንዲያስችል በመድሀኒት ረገድ የሚታየውን ህገ ወጥነትና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በይበልጥ መከላከል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቅዝቃዜ ሰንሰለታቸው መጠበቅ የነበረባቸው መድኃኒቶች ያለ ፍሪጅ መቀመጣቸው መገምገሙን ጠቅሰው በቀጣይ ከማስተማር ባለፈ ጥብቅ ክትትልና ህጋዊ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውይይት መድረኩ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 ዕቅድ የቀረበ ሲሆን በዚህም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን፤ በተለይ የምግብ ቅየጣ ስራና የድንገተኛ ቁጥጥር ስራ በአግባቡ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ልማት እቅድ መሪ አቶ ፍሳሌ ፍርዳ ናቸው።

የሙያ ፈቃድ አለማደስ፣ በመንግስትም ሆነ በግል ጤና ተቋም ሳይሰሩና የስራ ልምድ ሳይኖራቸው የሙያ ፈቃድ ምዝገባ መጠየቅ፣ ለቁጥጥር ስራው ትኩረት አለመስጠትና በቁጥጥር ግኝቶች መሠረት ከህግ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ተከታትሎ ለህግ አለማቅረብ በበጀት አመቱ ተግዳሮት እንደነበሩ  በመድረኩ ተነስቷል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የግል ጤና ተቋማትና የመድሀኒት ማከፋፈያዎች ህገ-ወጥነትን በሚከላከል መልኩ እንደሚሰሩና  በጤና ተቋማት ደረጃ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በመጀመርያ ደረጃ ክሊኒኮች ላይ ያለውን ህገ ወጥነት ለማስቀረትና ችግሮችን ለመቅረፍ በቀጣይ በአግባቡ እንደሚሰራ ጠቅሰው የፕላምፕነትና መሠል መድሀኒቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን