በኢያሱ ታዴዎስ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፣ ዓለም ከምን ጊዜውም በላይ ውጥረት ውስጥ የገባችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይም የኃያላን መንግስታት እርስ በርስ አለመተማመን ውጥረቱን አባብሶ በተለያዩ ሀገራት የጦርነት ደመና እንዲያንዣብብ ምክንያት ሆኗል፡፡
መንግስታትም ባላቸው ጦር እየተመኩ ጦርነት ውስጥ ለመግባት እየተንደረደሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ እስራኤል እና ፍልስጤም ያሉ ሀገራት ደግሞ ጦር ተማዝዘው ራሳቸውን ለድርድር እንኳን ለማዘጋጀት ፍቃደኞች አልሆኑም፡፡ ለገዛ ዜጎቻቸው ሳይጨነቁ በእልከኝነት የከፈቱትን ጦርነት አፋፍመውታል፡፡
የእነዚህ ሀገራት የጦርነት ድባብ በአጭር የሚቋጭ አይመስልም፡፡ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንዳይስፋፋ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ታዲያ እንደ አዲስ ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት ስጋት እየደቀነ ያለው የሀገራት ግጭት፣ መንስኤው የሀገራት ወሰንና ድንበር አጠቃቀም አለመጣጣም ስለመሆኑ የፖለቲካ ምሁራን አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ለዚሁ አብነት ሆኖ የሚጠቀሰው ደግሞ የእስራኤል እና የፍልስጤም ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀ የድንበር ግጭት ነው፡፡ የሁለቱ ሀገራት የአይጥና ድመት ፍጥጫ ጅማሮውን ያደረገው የጽዮናዊነት እንቅስቃሴ ከተቀሰቀሰበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ አንስቶ ነበር፡፡
እስራኤል በድንበር ይገባኛል ሰበብ ከፍልስጤም ጋር የገባችው እሰጥ አገባ እየተካረረ ዛሬ ላይ በጦርነት አፋጧቸዋል። ዌስት ባንክ፣ የጋዛ ሰርጥ እና ኢየሩሳሌም አሁን ድረስ ሁለቱን ሀገራት ያላግባባ የድንበር ውዝግብ መነሾ ናቸው፡፡
ደግሞ በሌላ አቅጣጫ ሩሲያ እና ዩክሬንም እንዲሁ እርስ በርስ ተፈላልገው ጦር እንዲማዘዙ ያደረጋቸው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ነው፡፡ ክሪሚያ፣ የተወሰነው የዶኔስክ ክፍል እና ሉሃንስክ ለጦርነቱ መነሾ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው፡፡
የድንበር ውዝግቡ ከእነዚህ ሀገራት የተሻገረ ነው፡፡ ቻይና ከታይዋን፣ ቻይና ከጃፓን፣ ሶማሊያ ከሶማሊላንድና ከፑንትላንድ፣ ሰርቢያ ከክሮሺያ ሌላ ለጠብ የተፋጠጡበት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ትንሽ የሚመስለው ልዩነት እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ሀገራትን በጎራ ከፍሎ ዓለም ለሶስተኛው ጦርነት እንድትገፋፋ መንስኤ እየሆነ ነው፡፡
በመርህ ደረጃ ግን የሀገራትን መሰል ልዩነት መፍታት የሚችሉ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች ፍንትው ብለው ተቀምጠው እናገኛቸዋለን፡፡ የግዛት/ የድንበር አንድነት (Territorial Integrity) ዓለም አቀፉ ሕግ (International Law) በመርህ ደረጃ በመሰረታዊነት ካስቀመጣቸው ሕጎች ዋነኛው ነው፡፡
ሕጉ ሀገራት የገዛ ድንበራቸውን ማስጠበቅ፣ ብሎም በጎረቤትነት ከሚዋሰኑ ሌሎች ሀገራት ጋር ሉኣላዊነታቸውን ባስጠበቀ መልኩ መጠቀም እንዲችሉ መብት አጎናጽፏቸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በበኩሉ፣ በአንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 4 ላይ የግዛት አንድነት ወይም የድንበርን ጉዳይ “መሰረታዊ” ሲለው ይገልጻል። ቻርተሩ ይህን ሲል ጉዳዩ ከሀገራት ሉኣላዊነት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ሕጉ በመሰረታዊነት እንዲከበር ከመሻት መሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ይኸው አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 4፣ ማንኛውም በኃይል የአንድን ሀገር ድንበር ገፍቶ ለራስ ጥቅም የማዋልን ድርጊት ከጠብ አጫሪነት ጋር ያያይዘዋል፡፡
የግዛት አንድነት ወይም የድንበር ባለቤትነት መብት በምድራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንዳለው ነው የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩት፡፡ ይህ ጉዳይ በጥቂቱ ትኩረት ማግኘት የጀመረው በ15ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነም ይነገራል፡፡
ያኔም ቢሆን ግልጽ የሆነ መብትና ግዴታን ያስቀመጠ አልነበረም፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የ30 እና የ80 ዓመታት ተብለው የሚጠሩትን ጦርነቶች ባስተናገደችው አውሮፓ፣ ከግጭት ነጻ ሆና እንድትንቀሳቀስ ጦርነት ባካሄዱት አካላት ዘንድ የተደረገው የዌስትፋሊያ ስምምነት ለግዛት አንድነት ሕግ መነሻ ሆኖ እንደቀረበ ይታመናል፡፡
ጦርነቶቹ የኃይማኖትና የግዛት መልክ ነበራቸውና ኃይማኖቶቹ እንደ ኃይማኖታቸው፣ ግዛቶቹ እንደየግዛታቸው ሉኣላዊነታቸው እንዲከበርላቸው ያደረገ ነበር ስምምነቱ፡፡ ግን ደግሞ ይኸውም ስምምነት የግዛት አንድነትን ከማስጠበቅ አኳያ ፍጹም መብት አላጎናጸፈም፡፡
በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተንሰራፋው ብሄርተኝነት (Nationalism) እና በራስ የመወሰን (Determination) እሳቤ፣ ሰዎች በሚኖሩባቸው ግዛቶች ዙሪያ የነበራቸውን አስተሰሰብ መቀየር መቻሉ ይነገራል፡፡
ብሄርተኝነት ሰዎች የሚኖሩባቸው ግዛት ባለቤት እንደሆኑና የግዛት ድንበራቸው እንዲከበር የሚያስችል እሳቤን ያሰረጸ ነበር፡፡ የጂኦግራፊ ተመራማሪው ጉንትራም ኸርብ ብሄራዊ ማንነት የሚገለጸው በግዛት ነው ሲል አመክንዮውን ያቀርባል፡፡
ሰዎች ስለመኖራቸውና ስለታሪካዊ ዳራቸው ማስረጃው ግዛት ነው ብሎም ያምናል፡፡ እናም አንድ ሕዝብ የራሱ ግዛት እንዲኖረው በግልጽ የተካለለ ብሄራዊ ግዛት ሊኖረው እንደሚገባም ያስረዳል፡፡
ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወዲህ የተመሰረተው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ፣ የግዛት አንድነት በዓለም አቀፍ መርህ ደረጃ እንዲቀመጥ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ አስፍሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያም ወዲህ ጦርነት በዓለማችን ላይ ባለመቅረቱ ሕጉ በአግባቡ እንዳይፈጸም አድርጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተመሰረተበት ከ1945 ወዲህ ግን የግዛት አንድነት ጥሩ መሰረት ኖሮት እንዲተገበር አስችሏል፡፡ በተለይም የመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር፣ ሀገራት በኃይል የሌሎች ሀገራትን ድንበር እንዳይነኩ በማስጠንቀቅ ጭምር አስፍሯል፡፡
ሕጉ ጥብቅ ቢሆንም በሂደት በተለያዩ ሀገራት የተነሱ ቁርሾዎች ግን ለይምሰል ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ብዙዎች ይተቹታል፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም ቢሆን በቻርተሩ የጸደቁትን ተያያዥ ጉዳዮች በስራ ላይ ለማዋል ብዙ ርቀት ሄዷል፤ ምንም እንኳን ተግባራዊነቱ ላይ ፍርደ ገምድልነት እንደሚታይ ቢነገርም፡፡
በዋነኛነት ግን ሀገራት ግዛትና ድንበራቸው ተጠብቆ ከጅምላ ጭፍጨፋ፣ ከጦር ወንጀሎች፣ ከዘር ማጥፋት እና ሰብዓዊነትን ከሚጋፉ ወንጀሎች ነጻ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል ሕጉ፡፡
ሕጉ በራሱ ሀገራት በግዛትም ሆነ በድንበር መብታቸው ሳይገፈፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢያትትም ሕጉን የሚያስፈጽሙ እንደ መንግስታቱ ድርጅት ባሉ አካላት ዘንድ ግን አድሎአዊነት መስተዋሉ አልቀረም፡፡
ለዚያ ነው የድንበር ውዝግቦች እየተስፋፉ ጦር እስከመማዘዝ ደረጃ የደረሱት፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ጦርነት እንዳያመሩ የሚያስችል አሰራር አለመዘርጋቱ ስጋት አጥልቷል፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስታቱ ድርጅት ከአንጀቱ ለተግባራዊነቱ ካለመስራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ድርጅቱ ሁሉንም ሀገራት በእኩል ዓይኑ አለመመልከቱ ከትችት አላስመለጠውም። በተለይም ለምዕራባዊያኑ ያደላ መሆኑም አልተወደደለትም፡፡ ለዚያ ነው የሩሲያ እና ዩክሬን፣ እንዲሁም እስራኤል እና ፍልስጤም ጦርነት ማብቂያ ያላገኘው፡፡
More Stories
“ትልቅ ዓላማ ይዞ መነሳት ከሁሉም ይበልጣል” – ወጣት ነፃነት ምትኩ
“የሳሙና ተብሎ 30 ብር ይሰጠኝ ነበር” – አቶ ደረጀ ሞገስ
“ስራዬን የጀመርኩት በብዙ ገንዘብ ሳይሆን ባካበትኩት ልምድ ነው” – ጋዜጠኛ ህይወት መለሰ