“የማባክነው ገንዘብና ጊዜ የለም” – ወይዘሮ ጽዮን አበራ

“የማባክነው ገንዘብና ጊዜ የለም” – ወይዘሮ ጽዮን አበራ

በደረሰ አስፋው

ዛሬ ላይ በሀገራችን ሴትነት ከምንረዳው ዓይነት ተራ ትርጉም የተለየ ሆኗል፡፡ የትናንቱ ታሪክ ተቀይሮ በሁሉም ዘርፍ ሴቶች እያሳዩ ያለው ትጋትና ውጤት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጥበብ ተጠቅመው በሚሰሯቸው ስራዎች በርካታ ልባም ሴቶች ጫናዎችን ፈልቅቀው መውጣት ችለዋል፡፡

በቅዱሱ መጽሃፍም ጠቢቡ ሰሎሞን “ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል፤ ዋጋዋ ከቀይ ዕንቊ እጅግ ይበልጣል” ሲል ነው የተናገረው፡፡ በዓለም ላይ ከሞሉ ውድ ነገሮች ስለምን ልባምን ሴት ከቀይ ዕንቁ ጋር አነጻጸራት ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

በፖለቲካው ቢሆን በኢኮኖሚው ዘርፍ የዚህች ልባም ሴት መገለጫ የሆኑ ሴቶች እየተፈጠሩ ስለመሆኑ ማንሳት እንወዳለን፡፡ የዚህ እትም እቱ መለኛችንም የዚሁ መገለጫ ነች፡፡ በሀዋሳ ከተማ የ“አንፆኪያ ባህላዊ ምግብ ቤት” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናት፡፡

ወደ ንግዱ ዘርፍ ከተሰማራች አጭር ጊዜ ቢሆንም በስራዋ ግን በአርአያነት የምትጠቀስ መሆን ችላለች፡፡ የምታዘጋጃቸው የአገልግል ምግቦቿና ባህላዊ ምግቦቿ ደግሞ ልዩ መገለጫዋ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ጽዮን አበራ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ውቅሮ ቀበሌ ነው፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ ስላሴ፣ ኢትዮጵያ ትቅደም፣ ዩቢኤስ፣ በለጡ እና ሌሎች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተምራለች።

ትጉህ ለነበረችው ተማሪም የ12ኛ ክፍል ውጤቷም ያማረ ሆነ፡፡ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመግባት ዕድል አገኘችና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በሶሾሎጂ የትምህርት ክፍል ለ3 ዓመታት ተከታትላ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃለች፡፡

ከዩኒቨርስቲ ምርቃ በኋላ ግን ጽዮን በሁለት መንታ መንገድ ላይ ቆመች፡፡ ቤተሰቦቿ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥራ እንድትሰራ ሲመኙ እሷ ግን ልቧ ወደፈቀደው ንግዱ አዘነበለች፡፡ በልጅነቷ ገና ተማሪ እያለች ጀምሮ ስትመኘው የነበረው ንግድ ሚዛኑን ደፋና ወደዛው ስራ ተሰማራች፡፡

ይህን ስታስብ ግን በእጇ ምንም አይነት ለመንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ አልነበራትም፤ ሀሳብ፣ የራስ ጉልበትና የዓላማ ጽናት እንጂ። መንቀሳቀሻ ገንዘብ የለኝም ብላም እጇን አጣጥፋ በቤት ውስጥ አልተቀመጠችም፡፡ እንደመነሻ የተጠቀመችው የወላጆቿን የቤት ውስጥ ግብአት በመጠቀም አንባሻ እና ዳቦ ጋግራ በቤት ውስጥ በመሸጥ ነበር፡፡

ይህ ጅምር ስራዋ ብዙም ሳይቆይ ሌላ ዕድል ይዞላት ብቅ አለ፡፡ መንግስት ያዘጋጀው የብድር አገልግሎት የነገዋን ተስፋ ይበልጥ ያለመለመ ሆነ፡፡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በ2010 ዓ.ም በወጣቶች ተዘዋዋሪ ብድር ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ስራ ሲያስገባ ተጠቃሚ ከነበሩት ወጣቶች መካከል አንዷ እሷ ነበረች፡፡

በተሰጣት የመስሪያ ቦታም ምግብ ቤት ከፍታ መስራት ጀመረች፡፡ ይሁን እንጂ የተሰጣት ቦታ ለስራዋ ምቹ ሆኖ ባለመገኘቱ ተለዋጭ ቦታም ቢሰጣትም እሷ ግን ለስራዋ ምቹ በሆነ ቦታ በግሏ ተከራይታ መስራትን ተመራጭ አደረገች፡፡

ተከራይታ መስራት ከጀመረች 3 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ቁርሳ ቁርስ፣ የጾምና የፍስክ ምግቦችን በመጠኑ በማዘጋጀት ስራ የጀመረች ሲሆን አሁን ግን ስራዋን አሻሽላ በተጨማሪ አገልግል ምግብ መስራት ጀምራለች፡፡ ይህን አዲስ ስራ ከጀመረችም 8 ወር ሞልቷታል፡፡

ቢሆንም ስራዋ በአጭር ጊዜ በተጠቃሚዎች ዘንድ በመወደዱ በከተማዋ አቶቴ አካባቢ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህን ስታደርግም እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን የገበያውን ዕድል ቀድማ በማጥናት መሆኑን ነው የተናገረችው።

የተለያየ ዋጋ ያላቸው ለጾምና ፍስክ የሚሆኑ አገልግል፣ ቁርሳ ቁርስ፣ ምሳና እራት ምግቦችን ታዘጋጃለች፡፡ በዚህ አገልግሎትም በትላልቅ ሆቴል ቤቶች በውድ ዋጋ የሚገኙ ምግቦች በጽዮን ምግብ ቤት በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ስራዋም በርካታ ደንበኞችን እንድታፈራ አስችሏታል፡፡

የአገልግል ምግቦች በሰዎች ትዕዛዝ የሚዘጋጅ እንደሆነ ገልጻ በስፋት የሚዘጋጀው ግን የፍስክ እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡ አንድ የፍስክ አገልግል አልጫ ስጋ፣ ጥብስ፣ አይብ፣ እንቁላል፣ ክትፎ፣ ድፎ ዳቦና ብርዝን ያካተተ ነው፡፡

ዝቅተኛው የአገልግል ምግብ 650 ብር የሚያስከፍል ሲሆን እስከ 3 ሰው በበቂ ሁኔታ የሚያስተናግድ ነው፡፡ የ10 ሰው 4 ሺህ 500 ብር፣ የ5 ሰው 8 ሺህ፣ የ30 ሰው 12 ሺህ እያለ ዋጋው ተቆርጦለታል፡፡ በዚህ ስራዋ የተለያዩ በጎ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች እሷን ተመራጭ እንዳደረጓት ነው የገለጸችው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከባህላዊ ምግቦች ዝግጅት እንዲሁ የጽዮን ምግብ ቤት ሙሉ ነው፡፡ የራሷ ፈጠራ የሆኑ ባህላዊ ምግቦችንም በማዘጋጀት የባህል አምባሳደር ነች ማለት ይቻላል፡፡ ከነዚህ ባህላዊ ምግቦች መካከል በወላይታ ብሄረሰብ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ቢላንዶ (ቆጮ በቦሎቄ ሆኖ አብሮት ከሚቀርብ እርጎ ጋር)፣ ከበቆሎ ዱቄት የሚዘጋጅና ብዙ አይነት ስያሜ ያለው ፎሰሴ ወይም ቡሌንታ፣ ሙቾ የሚባለውን እንዲሁ ከአይብ ጋር በመቀላቀል 6 አይነት አድርጎ በማቅረብ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

ጽዮን ንግዱን ከቤተሰብ የወረሰችው አይደለም፡፡ እንዲያውም ወደ ንግድ የተሰማራ የለም፡፡ እሷ ግን ገና የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነግዳ ፍሬያማ የመሆን ዓላማ ነበራት፡፡ እንዲያውም ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የቻለችውም በወላጅ አባቷ ግፊት እና ጫና እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡ እሷ ወላጅ አባቷን መወትወት ባታቋርጥም እሳቸው ግን ብልህ በተሞላበት የአባትነት ባህሪ እያግባቡ ከ8ኛ ክፍል በኋላ እንዲሁም ትምህርትሽን ጨርሺና ትነግጃለሽ እያሉ በማባበል ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንድትገባ የነበራቸው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደነበር ነው የተናገረችው፡፡

ይሁን እንጂ የልቧ ምኞት እና ተሰጥኦ በጊዜው ሆነና ዛሬ ላይ ጠንቃቃ ነጋዴ ለመሆን በቅታለች፡፡ ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቀች ተቀጣሪ ለመሆን አንድም ቀን የማስታወቂያ ቦርዶችን አልተመለከተችም፡፡ ስራ ፍለጋ ብላም የቢሮ ደጆችን አልረገጠችም፡፡

በምግብ ቤቱ በየጊዜው አዳዲስ የግሏን የፈጠራ ስራ እየጨመረችበት ዛሬ ላይ አንቱ የተባለች ሰው መሆን ችላለች፡፡ በስፍራው ተገኝቼ እንደታዘብኩትም ደንበኞቿ በልተው እና ጠጥተው ብቻ አይወጡም፡፡ ከፍለዋት ለተመገቡት ጣፋጭ ምግቦቿ ምስጋናን ችረዋት፣ አበረታታዋት አንዳንዶች ደግሞ እጅሽ ይባረክ ብለዋት ሲወጡ መመልከት ችያለሁ፡፡

ወ/ሮ ጽዮን ዛሬ ላይ በራሷ ጥረት ባቋቋመችው የአገልግሎት ዘርፍ በአስተናጋጅነት፣ በምግብ ዝግጅት፣ በቡና ማፍላት፣ በጽዳት እና በሌሎችም የስራ ዘርፎች ለ12 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥራለች። ለነዚህም ለእያንዳንዳቸው እንደ ስራቸው ባህሪና አይነት ከትንሹ አንድ ሺህ አምስት መቶ እስከ ትልቁ 4 ሺህ 500 ብር በወር ደመወዝ ትከፍላለች፡፡

በዚህ ስራ መሰማራቷ ያገኘችውን ውጤት ስትገልጽም፡-
“የበርካታ ንብረት ባለቤት አድርጎኛል። በሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ቤቶችን ገዝቻለሁ፡፡ በቤት ውስጥ ዳቦና አንባሻ በመጋገር የጀመረው ስራዬም ዛሬ ላይ ተጨማሪ ምግብ ቤት ለመክፈት አስችሎኛል፡፡ ከባዶ እጅ በተነሳው ስራዬ በብድር ጀምሬ ዛሬ ላይ የራሴ የምለው ጥሪት ማፍራት ችያለሁ፡፡” ብላለች፡፡

ወ/ሮ ጽዮን ምግብ ቤቱን ከመክፈት ባሻገር ስራዋን በግሏ በማስተዋወቅ የገበያውን ዕድል በመጠቀም ታዋቂነትን አትርፎላታል፡፡ ለዚህም ማህበራዊ ሚዲያውን በአግባቡ ነው የምትጠቀመው። የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም የአገልግል ምግብን በማስተዋወቁ አጋዦች ሆነዋታል፡፡ “ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ” ያለች ሲሆን የራሷ ፈጠራ የሆኑ አዳዲስ ባህላዊ የምግብ ዝግጅቶችንም በዩቲዩብና በሌሎችም አማራጮች ለህዝቡ እንዲደርሱ ታደርጋለች፡፡

በተለይ በምገባ ወይም ማዕድን በማጋራት ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ስራዋን በማጉላት ድጋፍ ያደርጉላታል፡፡ እሷም ደሀዎችን በመመገብ ተግባር በመሰማራት እነዚህን በሚዲያው በማሰራጨት ራሷን ታስተዋውቃለች፡፡

ዛሬ ላይ የአገልግል ምግብ ከመተዋወቅ ባለፈ የተጠቃሚዎች ቁጥርም አድጓል። “ሄሎ” እያሉ ባሉበት ሆነው ትዕዛዝ ይሰጧታል፤ እሷም ትዕዛዙን በሰዓቱ ጥንቅቅ አድርጋ ተጠቃሚዎች ዘንድ በማድረስ ከሰአቷ ዝንፍ አትልም፡፡ ይህም አንዱ መታወቂያዋ ሆኗል፡፡

የሀገራችን ሴቶች ንግድ ለመጀመር ቀዳሚው ገንዘብ ብቻ አለመሆኑን ልብ ሊሉ እንደሚገባ ትመክራለች፡፡ እሷ ስትጀምር ገንዘብን ይዛ አለመጀመሯን አስታውሳ እንዴት መስራት አለብኝ? ምንድነው የምሰራው? የሚለው አስተሳሰብ ካለን አቅም ጋር አዋህዶ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው የተናገረችው፡፡

“ከቤት ወጥቶ መስራት ባይቻል እንኳ በቤት ውስጥ ቁጭ ተብሎ የሚሰሩ ስራዎች በርካታ ናቸው፡፡ ካፒታልን በመጠበቅ የምናጠፋው ጊዜ እና ገንዘብ በርካታ ነው፡፡ እኔ ስጀምር ገንዘብ አልነበረኝም፤ ቤት ውስጥ ያሉ የዳቦ መጋገሪያዎችን ነው የተጠቀምኩት፡፡ ካለን ነገር መነሳት ይቻላል፡፡ መንቀሳቀሻ ገንዘብ ከሌለንም ተቀጥረን የምናገኘውን ገንዘብ በመቆጠብ ጥሪት ማግኘት ይቻላል” ብላለች፡፡

የወደፊት እቅዷ ደግሞ ሰፊ እንደሆነ ነው የምትገልጸው፡፡ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እና ብንኖር ብዙ ትልሞች አሉኝ” ነው ያለችው። ለዚህም ስትል አሁን ላይ በይዞታ ያሏትን ቦታዎች በመሸጥ ትልቅ ሆቴል የመክፈት ሀሳብ አላት፡፡ ለዚህም በዘርፉ ለመሰማራት የሚያስችል ጥናት እያደረገች ነው፡፡

በሀዋሳ ከተማ በሆቴሉ ዘርፍ እየተሰራው ያለ ምንድነው? ገና ያልተነካስ ምን ጸጋ አለ? የሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች የጥናቷ የትኩረት አቅጣጫ ናቸው፡፡ በተለይ በባህሉ የውጭ ቱሪስቶችን መሳብ የምትችልበት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጋለች፡፡ እንዲሁም የእንግዶች ማረፊያንም ያካተተ ስራ ለመስራት አቅዳለች።

ጽዮን የገንዘብ አጠቃቀሟም በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፤ ይህ ደግሞ በስራዋ ውጤታማ እንዳደረጋት ትገልጻለች፡፡ ዕቁብ ትጥላለች፣ ትቆጥባለች እንዲሁም ብድርም ትወስዳለች።

“የማባክነው ገንዝብና ጊዜ የለም። ለአንድ ነገር መግዣ ብበደር እንኳ ያን ገንዘብ ለመተካት ተግቼ እሰራለሁ፡፡ ገንዘብን አለአግባብ ማባከን በኔ ዘንድ ጸያፍ ነው። በኔ ዘንድ በትንሹ ገንዘብ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲፈጥር የማድረግ ስልትን እጠቀማለሁ። የቅንጦት ኑሮ አሁን ላይ ለኔ ተመራጭ አይደለም፡፡

“በእግሬ መሄድ እየቻልኩ ለቅንጦት ለትራንስፖርት መክፈል አልፈልግም፡፡ ገንዘብ ስለተጠነቀኩለት ነው ብዙ ነገር ያፈራሁት የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ፡፡ ስራዬ ያን ያህል ትልቅ ከሚባሉ ስራዎች የሚመደብ ባይሆንም ከፈጣሪ በታች ለገንዘብ የምሰጠው ትኩረት ለውጤት አብቅቶኛል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

“ውጤታማ ለመሆን የራስ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ በሰው ላይ መደገፍ ዘላቂ ባለመሆኑ ይህን ብዙም ተመራጭ አላደርግም፡፡ ከዚህ ይልቅ በራሴ ለመቆም ነው የምጥረው፡፡ የቤተሰብ ድጋፍ ጎጂ ነው ባልልም እኔ ውስጥ ያለው ራዕይ፣ ዓላማና ዕቅድ ነው ሊገፋኝ የሚገባው እንጂ በሌሎች ሊሆን አይገባም፡፡

“መደገፍ አለብኝ ብዬ ድጋፍን የምጠብቅ ሴት አይደለሁም፡፡ ጫናዎች ቢከሰቱም እንኳ ዓላማዬ ላይ ብቻ ትኩረት የማደርግ ሴት ነኝ፡፡ ይህን ሌሎች ሴቶችም ሊያዳብሩት ይገባል” የሚል ምክር አዘል አስተያየቷን ነው የገለጸችው፡፡

ጽዮን ዩኒቨርስቲ ገብታ በመማሯ በራሷ ያዳበረችው ተሰጥኦ ቢኖርም ከትምህርቱም ያገኘችው ጥቅም አለ፡፡ በእውቀትም ይሁን በልምድ እንድትጎለብት እንደረዳት ነው የተናገረችው፡፡ ከተለምዶ አሰራር ወጥታ ስራዋንም ሚዛናዊና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችላትን እውቀትም ገብይታበታለች፡፡

ካስተማሪ፣ ከአቻ ጓደኛ፣ መጽሃፍት በማንበብም ያጎለበተችው እውቀት እንዳለ ነው የጠቆመችን፡፡ ይህም ለዛሬው ስራዋ አጋዥ እንደሆናት ጠቁማ ተፈጥሮ ከለገሰቻት መሰጠት ጋር ቀምራ ለዛሬው ውጤታማነቷ አግዟታል፡፡