“ሥራን ማክበርና የሰውን ችግር መረዳት ልዩ ባህሪዬ ነው” – አቶ አወቀ ሲራክ አበጋዝ

“ሥራን ማክበርና የሰውን ችግር መረዳት ልዩ ባህሪዬ ነው” – አቶ አወቀ ሲራክ አበጋዝ

በአብርሃም ማጋ

የዛሬው ባለታሪካችን አቶ አወቀ ሲራክ በርዕሱ የተናገሩትን ሃሳባቸውን ያጠናከሩት ሥራቸውን እንደህይወታቸው ቆጥረውና እጅግ አክብረው እንደሚሠሩ በመግለፅ ነው፡፡

ሥራ የህይወት ማዳኛ እንደሆነም ያክላሉ፡፡ ከሥራ ውጭ የሆነች ህይወት ውጤቱ ከጉስቁልና ባሻገር መጨረሻው ሞት እንደሆነም ከማብራራት ወደ ኋላ አላሉም፡፡

አቶ አወቀ ለ41 ዓመታት ያህል በመንግስት ሥራ ላይ ሲያሳልፉ በአብዛኛው በሃላፊነት ነበር፡፡

ሆኖም በዚህን ጊዜ ከሥራቸው ያሉ ሠራተኞችን የሥራ ዲስኘሊን እንዲኖራቸው አባታዊ አመራር ይከተሉ ነበር፡፡ በዚሁም ተግባራቸው በርካቶች ወደ ሥራ መሥመር ገብተው በሥራ እንዲታነፁ አድርገዋል፡፡

ከተዘረዘረው ውጭም አቶ አወቀ ሲራክ የተቸገረውን መርዳት ታላቅ እፎይታ እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ፡፡

በዚሁም በመሥሪያ ቤታቸውም ሆነ በመኖሪያ አካባቢያቸው በሰዎች ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታሉ፡፡

ለመግቢያነት ይህንን ካልን ዘንድ የአቶ አወቀ ሲራክን ምርጥ ተመክሯቸውን ልናስነብባችሁ ወደድን መልካም ንባብ፡፡

አቶ አወቀ ሲራክ በቀድሞው መንግስታዊ አወቃቀር በወሎ ጠቀላይ ግዛት፣ በቦረና ሳይንት አውራጃ፣ በመካነ ሰላም ወረዳ፣ በመካነሰላም ከተማ በ1950 ዓ.ም ህዳር 12 ተወልደው የ68 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡

የልጅነት ህይወታቸው ሲዳሰስ እስከ 12 ዓመት ድረስ ትምህርት የመማር እድል ተነፍገው በከብት እረኝነት አሳልፈዋል፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ የተጠቀሱትን ተግባር እየፈፀሙ ከቆዩ በኋላ በ1962 ዓ.ም ላይ ወደ ቀድሞው ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነው ሃዋሣ የመምጣት እድል ያገኛሉ፡፡ እድሉን ሊያገኙ የቻሉት ወላጅ አባታቸው በሐዋሣ ከተማ በመንግሰት ሥራ ላይ ተቀጥረው በመሥራት ላይ ስለነበሩ ነው እናታቸው ከመካነ ሰላም ከተማ በ1962 ዓ.ም ወደ ሃዋሣ ከተማ ያመጧቸው፡፡

ወደ ሃዋሣ ከተማ መምጣታቸውን ተከትሎ በ1963 ዓ.ም በመስከረም ወር ላይ ሃዋሣ ታቦር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡

በመሆኑም የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው ያለፉት በ1969 ዓ.ም ሲሆነ በ1970 ዓ.ም ላይ 9ኛ ክፍል መከታተል የጀመሩት በመደበኛውና በቀኑ ትምህርት ኘሮግራም ሳይሆን በማታው ነበር፡፡

ምክንያቱም በ1969 ዓ.ም መጨረሻ ወር ላይ የመንግስት ሥራ ተወዳድረው በማግኘታቸው ነበር፡፡ ሥራውን ያገኙትም በቀድሞው አጠራር በሲዳሞ ክ/ሃገር እርሻና ህዝብ ማስፈር ጽ/ቤት በአስተዳደር ሥራ በቋሚነት ተቀጥረው ነው፡፡

በመሆኑም ቀን እየሠራ ማታ ማታ እየተማሩ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በማታው ትምህርት ኘሮግራም ተምረው አጠናቅቀዋል፡፡

በመቀጠልም የመንግሰት ሥራን እየሠሩ በርቀት ትምህርት ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በአስተዳደር ትምህርት በዲኘሎማ ተመርቀዋል፡፡

መ/ቤታቸው ከእርሻና ህዝብ ማስፈር ጽ/ቤት ወደ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ግብርና ሚኒስተር ተጠሪ ጽ/ቤት ሲቀየር እሳቸውም ጽ/ቤቱ ተዛውረው አስተደደር ሥራ ተመድበው እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል፡፡

አሁንም መ/ቤቱ ተለውጦ ደቡብ ቀጠና ግበርና ልማት ጽ/ቤት ሲሆን በተመሳሳይ ሥራ መደብ በአስተዳደር ሥራ ተመድበው ከ1978-1984 ዓ.ም ድረስ ለ6 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ አሁንም የመ/ቤቱ ሥም ተቀይሮ ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጽ/ቤት ሲሆን በተመሳሳይ ሥራ ተመድበው ከ1985 – 1996 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል፡፡

በ1996 ሰኔ ወር ጀምረው እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ዲላ ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአስተደደርና ፋይናንስ አገልግሎት ሐላፊ ሆነው ተመድበው ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

ከሰኔ 18/1998 – 2010 ዓ.ም ታህሳስ ድረስ በደቡብ ብሔሮችብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ተዛውረው በተለያዩ ፋይናንስና ንብረት አስተደደር ውስጥ በባለሙያነት አገልግለው በ2010 ዓ.ም ከጥር ወር ጀምረው የጡረታ መብታቸውን አስከብረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ አንዳለ አቶ አወቀ በመንግሰት ሥራ ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በተጓዳኝም በእግር ኳስ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ከ1969 – 1978 ዓ.ም ድረስ በሐዋሣ ቀይ ኮከብ እግር ኳስ ክለብ በተጫዋችነት ያገለገሉ ሲሆን በክለቡ መሥራችነትም ይታወቃል፡፡

ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ በ1979 በ1ኛ ደረጃ እግር ኳስ ዳኝነትና በፌደራል እግር ኳስ ዳኝነት ከፍተኛ ስልጠና ወስደው በእግር ኳስ ዳኝነት እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ በዳኝነት ከ1979 – 1990 ዓ.ም ድረስ ለ11 ዓመታት ያህል አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

ከ1991 – 2015 ዓ.ም ድረስ በእግር ኳስ ውድድር በታዛቢነት፣ በኢንስትራክተርነት ሠርተዋል፡፡ ከ3 ዓመት ወዲህ የእግር ኳስ ሥራን አቁመው እረፍት ላይ ይገኛሉ፡፡

በአስተዳደር ሥራ ላይ እያሉ በተለይም ዲላ ግብርና፣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሲመሠረት ተመድበው ከሄዱ በኋላ ተቋሙን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ /በማቴሪያል/ የማደራጀት ሥራን በዋናነት ፈጽመዋል፡፡ በርዕስ መስተዳደር ጽ/ቤት ተዛውረው ሲመጡም ያልተደራጀውን የንብረት አስተዳደርና የሰው ሃይል አደረጃጀቱን በማመቻቸት ትልቅ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

በተግባሩም የእቃ ግዢና የንብረት አስተዳደር ሥራዎችን ከመንግስት ደንብና መመሪያ አንፃር ብቻ እንዲፈፀም አድርገዋል፡፡

ሥራው ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚሠራ ስለሆነ ከአባልና ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጋር ተያይዞ የግል ፍላጐታቸውን ለማሟላት የሚሯሯጡ ግለሰቦች መሰናከል ይፈጥሩ ነበር፡፡

ነገር ግን እሳቸው ከረጅም ሥራ ልምድ በቀሰሙት ብቁ አስተዳደራዊ እውቀት በጥበብ እየመሩ የጽ/ቤቱን ሥራ መልክ ለማስያዝ ችለዋል፡፡

በስፖርት ሥራ ወቅት ያከናወኑት ተግባር ቢኖር ከሁለተኛ አለም አቀፍ ደረጃ የእግር ኳስ ዳኝነት በርካታ ወጣቶቶችን ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ከሌሎች የሥራና የሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ከእነዚያ ወጣቶች መካከል በአሁኑ ወቅት የአለም አቀፍ የእግር ኳስ ዳኝነት ላይ ያሉ ከወንዶች  ክንዴ ሙሴ፣ ትግል ግዛው፣ በላይ ታደሰ ከሴቶች ወይንሸት አበራ፣ ማህሌት አሥራት፣ምስጋና ጥላሁን ሥንታየሁ ደፈርሻ… የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በሥራ ወቅት በርካታ የእውቅና የመስክር ወረቀቶችንና ሸልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ እውቅናና የምስክር ወረቀቶችን ያገኙት በስፖርት ሥራ በኩል ነበር፡፡

ለአብነት ያህል የደቡብ ክልል ስፖርት ምክር ቤት በ1999 ዓ.ም የመላው ደቡብ ጨዋታዎች ከየካቲት 3 – 17 1999 ዓ.ም በተዘጋጀው ክልል አቀፍ ዓመታዊ ሻምፒዮና ውድድር አርቢትር ኮሚቴ ሆነው በማገልገላቸው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል መንግስት የወጣቶችና የሰፖርት ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት የሐዋሣ ኦሎምፒክ ሳምንት ዝግጅት ላይ ባደረጉት አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኘሬዝዳንት ከአቶ አሰፋ ማሞ እጅ የምስክር ወረቀት ከምስጋና ጭምር ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሸን የመምሪያው 1ኛ ደረጃ ኦርቢትር ሆነው ባሳዩት ችሎታና ቀን አገልግሎት ብቁ ስለሆኑ ለፌደራል አርቢትርነት ደረጃ የተሰጠውን ፈተና በሚገባ ስላለፉ ታህሳስ 1 1990 ዓ.ም የፌደራሉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የምስክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለው ስልጣን መሠረት ከሚያዝያ 27 እስከ ግንቦት 1/2002 ስልጠና ወስደው የእግር ኳስ ዳኞች ኮሚት በሰጠው ግምገማ መለኪያ መሠረት ረዳት ጁኔየር ኢንስትራክተር ስለሆኑ የኢትዮጰያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የመስክር ወረቀት ሰጥቷቸዋል፡፡

ባጠቃላይ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ስፖርታዊ የእግር ኳስ እንቅስቃሴች በማገልገል ከ2ዐ በላይ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል፡፡

ከዚህ ውጭም በመጨረሻ ከነበሩበት /ከክልል ም/ቤት/ በጡረታ ሲገለሉ ምክር ቤቱ በጥሬ ገንዘብ፣ በዓይነትና ከምስጋና ወረቀት ጭምር ሸልሟቸዋል፡፡ በወቅቱ የጥሬ ገንዘብ መጠን 10 ሺህ ብር፣ አንድ ሙሉ ልብስ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 32 ኢንች ቴሌቪዥን ቶሽባ ላፕቶኘ ሸልሟቸዋል፡፡ በሥራ ያላቸው ፍቅር ምን እንደሚመስል ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጡን ምላሽ ቢኖር፡- ለሰው ልጅ ሥራ መሥራት በጣም አስፈላጊ እና ወሳኝ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እሳቸውም ቢሆን ህይወታቸውን ይዞ አንደፈለጉ እንዲኖሩ ያስቻላቸው ሥራ በአግባቡ መሥራታቸው እንደሆነ ሙሉ እምነት አላቸው፡፡

በሥራ ላይ ሰለቸኝ ደከመኝ፣ አስጠላኝ፣ ደበረኝ… ወዘተ የሚባሉትን የስንፍና ምልክት የሆኑ ቃላቶችን በሳቸው ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ ሥራ ካለ ሁሌም እረፍት የላቸውም፡፡ ችግር ካልሆነ በስተቀር በሥራ ዓለም ማርፈድና መቅረት የሚባሉ ነገሮችን አያውቁመ፡፡ ጠዋት ቀደም ብለው በመግባት ከሰዓት በኋላ የሥራ ሰዓት ሲገባደድ ደቂቃዎችን አሳልፈው ይወጣሉ፡፡

በመሆኑም በሥራ ዓለም ውስጥ ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው አንድ ሰው በርትቶ ከሠራ ውጤታማ ከመሆን የሚያግደው ነገር አለመኖሩን ያብራራሉ፡፡

ሥራን ማክበርና የሰዎችን ተግባር መረዳት ልዩ ባህሪያቸው እንደሆነም ከመግለፅ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ ሥራን ማክበር ራስን ማክበር ነው ይላሉ፡፡ በሐላፊነት በሠሩባቸው ጊዜያት ከበታች ሠራተኞቻቸው የሥራ ሰዓትን አክብረው እንዲሠሩ የሚያደርጉበት ምከንያት ለሥራ ካላቸው ከብር ነው፡፡ ከሠራተኞች ጋር ሠላማዊ ግንኙነት ፈጥረው በመተባበር፣ በመነጋገር፣ በመወያየት፣ በመስማማት፣ በመናበብ ስለሚሠሩ ሁሌ ውጤታማ ከመሆን ቀርተው አያውቁም፡፡

የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዳይባክን ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ማህበራዊ ህይወታቸው ሲዳስስ በማንኛውም ማህበራዊ ህይወት ይሳተፋሉ፡፡ በለቅሶ፣ በሠርግ፣ በተለያዩ ስብሰባዎች… በመሳተፍ ረገድ ወደር የሌላቸው ሰው ናቸው፡፡ በዚህ መነሻ አሁንም በተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎች ከሐላፊነት ጭምር ወስደው እየሠሩ ናቸው፡፡

አቶ አወቀ ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በ1976 ሐምሌ 26 ሲሆን የ3 ሴት ልጆች አባት ናቸው፡፡

ሶስቱም አግብተው ልጆች የወለዱ ሲሆንሁለቱ አሜሪካን ሃገር ሲኖሩ አንዱዋ በሁለተኛ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስት ሥራ ተቀጥራ ትሠራለች፡፡

በተጨማሪም አቶ አወቀ 4 ወንድና 2 ሴት በድምር 6 የልጅ ልጆችን በዓይናቸው ለማየት ታድለዋል፡፡

ይህ ምርጥ ተሞክሮ በሌሎቹም ዘንድ መለመድ እንዳለበት እየጠቆምኩኝ የዛሬውን ዝግጅቴን በዚሁ ቋጨሁ ሰላም፡፡