ሲምቡ ÷ ሌላኛው የአፍሪካ ኩራት

ሲምቡ ÷ ሌላኛው የአፍሪካ ኩራት

በአንዱዓለም ሰለሞን

እ.ኤ.አ በ2016 በተካሔደው ኦሎምፒክ  የመዝጊያ ስነ ስርዓት የታንዛኒያን ባንዲራ በመያዝ ታየ፡፡ ይህ አትሌት በወቅቱ በተደረገው የወንዶች የማራቶን ውድድር የ5ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው አልፎንሴ ሲምቡ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ፣ በወርሀ ጥር 2017 በሙምባይ ማራቶን አሸነፈ፡፡ በዚያው ዓመት በተካሔደው የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ 2:09:51 በመግባት የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቃ፡፡

በ2019 በኳታር፣ ዶሀ በተካሔደው የዓለም ሻምፒዮና ያደረገው ውድድር ግን ውጤቱ ጥሩ የሚባል አልነበረም። በውድድሩ 16ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀ፡፡

በ2021 በተካሔደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሀገሩን በመወከል ቢሳተፍም፣ ውድድሩን የፈጸመው ግን የ7ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በተሳተፈበት የጋራ ብልጽግና ጨዋታዎች ላይ በማራቶን ተወዳድሮ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ቻለ፡፡

በወርሀ ህዳር 2024 በተካፈለበት የቫሌንሽያ ማራቶን የ4ኛ ደረጃን በመያዝ ቢያጠናቅቅም ውድድሩ ግን የራሱን የተሻለ ሰዓት ያስመዘገበበት ነበር፤ 2:04:38 በመግባት፡፡ በ2025 በተካሔደው የቦስተን ውድድር ደግሞ 2ኛ በመሆን አጠናቀቀ፤ 2:05:04 በመግባት፡፡

ሲምቡ በውድድር ዘመኑ ያሳካው ጣፋጭ ድል የተገኘው ደግሞ ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ በ2025 በጃፓን በተካሔደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማሸነፍ በውድድሩ ታሪክ ለታንዛኒያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘ አትሌት ለመሆን በቃ፡፡

የ33 ዓመቱ አትሌት የተቀዳጀው ይህ ድል በእርግጥም የአመታት ጥረቱ ውጤት ነው፡፡ ድሉ ለሀገሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ከማስገኘት ባሻገር፣ የኬንያና የኢትዮጵያን አትሌቶች የበላይነት የገታም ጭምር ተብሎለታል፡፡

በእርግጥ እርሱም ቢሆን ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ይህንኑ ሀሳብ ማንሳቱ አልቀረም፡፡ ይህ ዓመት ታላቅ ስኬት የተቀዳጀበት መሆኑን ከገለጸና ለዚህም የታንዛኒያን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጨምሮ ሌሎች የሚገባቸውን አካላት ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፡-

“በጣም ነው የተደነቅሁት፡፡ ምክንያቱም የተወዳደርኩት የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች በተሳተፉበት ውድድር ላይ ነው፡፡ እነርሱም ቢሆን የእኔን ማሸነፍ አልጠበቁም ነበር፡፡”

የሲምቡ ማሸነፍ፣ ታንዛኒያ ከተፎካካሪነት ባሻገር አሸናፊ የሚሆን አትሌት እንዳላት ከማሳየቱም በላይ፣ በዚህ የውድድር ዘርፍ እንደሌሎቹ የረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች ሁሉ፣ የምስራቅ አፍሪካ የበላይነት በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚረጋገጥበትም ሆኗል፡፡ ከምንም በላይ ግን ሲምቡ ለሀገሩ አትሌቶች በዓርዓያነት የሚጠቀስ ስኬት የተጎናጸፈበት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየትም እንዲህ ብሏል፡-

“ተስፋ ሳይቆርጡ ያሰቡትን ለማሳካት ለሚጥሩ አትሌቶች በርቱ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ያሰባችሁትን እንዳታሳኩ ያደርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ከጥረት ጋር ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡”

ሲምቡ ይህን ሲናገር ዝም ብሎ አይደለም፤ ከህይወት ተሞክሮው በመነሳት እንጂ፡፡

“ይህን ድል ለማሳካት 10 ዓመታትን ጠብቄያለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ውድድር የተሳተፍኩት በ2015 በቤጂንግ ቻይና ነበር፡፡ በወቅቱ ውጤቱ ጥሩ ባይሆንም ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ በ2017 ደግሞ በለንደን ተወዳድሬ የነሀስ ሜዳሊያ አገኘሁ፡፡ ከ2017 ጀምሬ በበርካታ ውድድሮች ላይ ተሳትፌ ሳይሳካልኝ ቆይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ተስፋ አልቆረጥኩም” በማለት በውድድር ዘመኑ ስላጋጠመው ውጣ ውረድና ስለነበረው ሁኔታ ተናግሯል፡፡

ሲምቡ በዓለም ሻምፒዮናው ውድድሩን የፈጸመው ከተፎካካሪው አትሌት የአጭር ርቀት ሩጫ ውድድር በሚመስል መልኩ በመቅደም ነው፡፡ አትሌቱ ሁኔታውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየትም እንዲህ ብሏል፡-

“ወደ ስታዲየም ስንገባ እንደማሸንፍ እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ በቪዲዮ ስክሪኑ ላይ ይህን መመልከቴ ለእኔ የማይታመን ነገር ነበር፡፡”

በእርግጥ የሁለቱ አትሌቶች የፍጻሜ ትንቅንቅና የአሸናፊነት ልዩነት ከዚህ ቀደም በማራቶን ውድደር በዚህ መልክ ከታዩት ሁሉ አሸናፊውን ለመለየት የሚከብድ ነበር፡፡ በ2001 በኤድመንተን በተካሔደው የዓለም ሻምፒዮና ገዛኸኝ አበራ ኬንያዊውን አትሌት ሲሞን ቢዮት ከቀደመበት የላቀ፣ በኦሎምፒክ ደቡብ አፍሪካዊው ጆሲዋ ቱግዋኔ ደቡብ ኮሪያውን ሊ ቦንግ ጁ ካሸነፈበትም በበለጠ በጠባብ ልዩነት የተገኘ ድል ነበር፡፡

አሁን ሲምቡ በታንዛኒያዊያን እየተወደሰ ነው፡፡ በእርግጥ ወደ ስፖርቱ ለመግባት እያሟሟቁ ላሉም ሆነ በስፖርቱ በመሳተፍ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች በዓርዓያነት ሊጠቀስ የሚገባውን ድል ተቀዳጅቷልና ይህ የሚገባው ነው፡፡ የእርሱ አሸናፊነትም ቢሆን ለበርካታ ታንዛኒያዊያን መነቃቃትን እንደሚፈጥርም እሙን ነው፡፡

ከውዳሴውና አድናቆቱ ባሻገርም፣ ሲምቡ ስሙ ከቀደምት የታንዛኒያ ስመ ጥር አትሌቶች ጋር እየተነሳ ይገኛል፡፡ በ1974 በጋራ ብልጽግና ሀገራት ውድድሮች ላይ የዓለም ክብረ ወሰን የሰበረው ፊልበርት ባዬ እና በ1978 በኤድመንተን በተካሔደው መሰል ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ነበረው ጊዳሚስ ሻሀንጋ እዚህ ላይ ይጠቀሳሉ፡፡

የአሹራ ከተማ ካውንስል ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን አክህዋሪ ደግሞ በ1968 በሜክሲኮ በተካሔደው ኦሎምፒክ፣ ሀገራቸውን በመወከል በማራቶን የተሳተፉትን የአባታቸውን ታሪክ መለስ ብለው እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል፡፡

የጽህፈት ቤት ሃላፊው አባት በወቅቱ በቁርጭምጭሚታቸውና በትከሻቸው ላይ የገጠማቸውን ጉዳትና ህመም ተቋቁመው ውድድሩን መጨረሳቸው የጽናት ተምሳሌት አድርጓቸው ነበር፡፡ አክህዋሪም ይህን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ክስተት አስታውሰው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፡-

“አባቴ ምን ጊዜም አንድ ሰው የጀመረውን ነገር መፈጸም እንዳለበት ያምናል፡፡ የአልፎንሴ ሲምቡ ታሪክም ይህን ሌጋሲ ያስቀጠለ ሲሆን እኛ ለዚህ የአይን እማኝ በመሆናችን ደስተኞች ነን።”