የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
2ኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የጤና ፎረም በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ተካሂዷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ6ኛ ጊዜ በክልሉ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ በጂንካ ከተማ ጂንካ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ የተከበረው ፎረሙ “አንድነት ለተግባራዊ እርምጃ፤ የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም እንተባበር” በሚል መሪ ቃል ነው።
የፌደራል ጤና ጥበቃ ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ፎረም ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነብዩ ቤዛ፤ አፍላ ወጣትነት ፈታኙ የወጣትነት ዘመን በአግባቡ ከተገራ እድል፣ ካልተገራ ደግሞ አደጋ እንደሚሆን አንስተዋል።
የወጣቶች ጤና ፎረሙ መደራጀት ወጣቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ጤንነት ለማስጠበቅ የሚረዳ በመሆኑ በየመዋቅሮቹ ይኸው ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙ አውስተው፤ በቂ ባይሆንም በጅምር ስራዎች ግን መሻሻሎች መታየታቸውን በማመላከት ለተሻለ ውጤታማነት የአደረጃጀቶቹን ሚና ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
እንደ ሀገር 1/3ኛ የሚሆን ህዝብ አፍላ ወጣቶች መሆናቸውን በማውሳት ለስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው ተገቢው እንክብካቤ እንደሚሹ የጠቀሱት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤና እና ስርዓተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሪሁን ገብሬ ናቸው።
ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለወጣቶች የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች መንስኤ መሆኑን በማንሳት ችግሩን ለመቅረፍ አካታች የጤና ስርአትን ጨምሮ አፍላ ወጣቶች እርግዝና የመከላከልና የቤተሰብ ምጣኔ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የጤና ካውንስሎች በየደረጃው እየተቋቋሙ ፎረሞች መመስረታቸውን ጠቅሰዋል።
የክልሉ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ካውንስል ምክትል ፕሬዚደንት ወጣት በረከት ተፈሪ በበኩሉ፤ ፎረሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል በመሆኑ በየመዋቅሩ የወጣቶች ጤና ካውንስል አደረጃጀቶችን የማጠናከር ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝቧል።
የወጣቶችን የጤና ችግሮች ለመፍታት በፌደራል ጤና ጥበቃ በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መቆየታቸውን በመጥቀስ ለቀጣይም አዲስ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን በፎረሙ የተሳተፉት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶ/ር ዋሴ ልንገርህ ገልጸዋል።
የፎረሙ ተሳታፊዎች የጂንካ ሆስፒታል ወቅታዊ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ: ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የህፃናት የወደፊት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልና የተሻለ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ገለፀ
5ኛው አገራዊ የሠላም ኮንፈረንስን በተመለከተ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተላለፈ መልዕክት
ፈጣን ፣ ወቅታዊ እና ተአማኒ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑን የሚመጥን አሰራርን መዘርጋት እንደሚገባ ተገለጸ