በመሐሪ አድነዉ
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠሩት ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ትብብራቸውን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይም ሦስቱ ሀገራት የጋራ ፓስፖርት ለማስጀመር መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። ሦስቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ በኢኮዋስና በሌሎች ድርጊቶች መወገዛቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተለይም ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በኢኮዋስ ጫና ደርሶብናል በሚል ከአባልነት የመውጣት ውሳኔን አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም ሦስቱም የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት እርስ በርስ እንደሚመሩና እንዲተባበሩ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች ተፈራርመው እንደነበር ይታወቃል፡፡
ባለፈው ነሐሴ ወር ላይም ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኩናፋሶ የጋራ የመከላከያ ስምምነት መፈራረማቸውንም የአልጀዚራ ዘገባ አመላክቷል። አሁን ላይም ከኢኮዋስ የተገለሉት ሦስቱ የአፍሪካ ሀገራት የጋራ የባዮ ሜትሪክስ ፓስፖርት ለመጀመር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የኢ አር ቲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
የሣህል ግዛቶች ትብብርን መሠረት በማድግ የአባል ሀገራቱ የጋራ የባዮሜትሪክስ ፓስፖርትን ለመጠቀም ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው የህብረቱ መሪ ኮሎኔል አስማይትይታ ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር በታጠቁ ኃይሎች የፀጥታ ችግር የሚገጥማቸው ሀገራት ናቸው። በዚህም አንዳንድ የምዕራብ ዓለም ወታደሮች ፀጥታና ደህንነትን መጠበቅ በሚል ሰበብ ሀገሮች ውስጥ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም የምዕራቡን ዓለም ጦር ከየግዛታቸው አስወጥተው አሁን ላይ ሀገር በቀል የጋራ የፀጥታ ትብብርን መስርተዋል፡፡ ይህ ወታደራዊ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ተከትሎ አሁን ላይ የጋራ ፓስፖርት ለመጠቀም መወሰናቸውንም የአግዱሉ ዘገባ አትቷል፡፡
እነዚህ ሦስት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መንግሥታት ሥልጣንን በኃይል የተቆጣጠሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ህብረትና ከኢኮዋስ መታገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህም ተደጋግፈው ለመቆም ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የሣህል ቀጠና ኮንፌደሬሽን የተባለ ጥምረትን የመሠረቱት ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ የማሊውን ወታደራዊ መሪን ለጥምረቱ ሊቀመንበር አድርገው መርጠውም ነበር፡፡
እኚህ የማሊው መሪና የህብረቱ ሊቀመንበርም ሦስቱ ሀገራት የጋራ ፓስፖርት ለመጠቀም መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ የሣህል ቀጠና ኮንፌደሬሽን ማቋቋማቸው በርካታ ጉዳዮችን በጋራ ለመጠቀም እንደሚያስችላቸው ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ በተለይም ባንኮችንና የጋራ ተቋማትን ዜጐቻቸው በጋራ እንዲጠቀሙ እንደሚያስችልም መመላከቱን የቢቢሲ ዘገባ ጠቁሟል፡፡ አሁን ላይ ሦስቱም የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ተቋሞቻቸውን በጋራ ለመጠቀም የጀመሩትን ሥራ የሚያጠናክር ሌላ አገልግሎቶችን ለማስጀመር መስማማታቸውም ተሰምቷል፡፡
ይህም ዜጐቻቸው በባዮሜትሪክ ፖስፓርት በጋራ መጠቀማቸው አንዱ ወደ አንዱ ሀገር የመንቀሳቀስ እድልን ይፈጥርላቸዋል ተብሏል። የባዮ ሜትሪክስ ፓስፖርት በአሰሪና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ መረጃዎች የተደገፈ ሲሆን የሦስቱ ሀገራት ዜጐች ባንክን ጨምሮ ሌሎች የጋራ ተቋሞችን በጋራ ለመገልገል የጋራ ፓስፖርትን ማስጀመርም ትልቁና ወሳኙ ሥራ ነው ሊባል ይችላል፡፡
እነዚህ ሦስቱ ሀገራት ከምዕራባውያን ተፅእኖ ራሳቸውን ለማላቀቅ እየሠሩ ስለመሆናቸውም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እንደሚያስፋፉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለዚህም በትራንስፖርት፣ በኮሙኒኬሽን እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚፈለገውን መሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማከናወን ሦስቱ ሀገራት የተሻለ ግንኙነት ለመመሥረት አቅደዋል፡፡
ለዚህም ያግዛቸው ዘንድ ሦስቱ ሀገራት የጋራ የባዮሜትሪክስ ፓስፖርትን ለመጀመር ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው የሣህል ቀጠና ኮንፌደሬሽን ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡
የአሁኑ ትራንስፖርት ዜጐችን የማገናኘቱ ዜና የተሠማውም ሀገራቱ የሣህል ቀጠና ጥምረትን ከመሠረቱ አንደኛ አመታቸውን ሊደፍኑ በተቃረቡበት ጊዜ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
More Stories
“ጤናችን በአመጋገባችን ይወሰናል”-ዶክተር ዘላለም ታፈሰ
አዲስ ህይወትን በአሜሪካ
ጥቂት ስለ በርሊን ማራቶን