“ለተኪ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ተሰጥቷል”  – አቶ ሻሻሞ ቂሊሳ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ሻሻሞ ቂሊሳ ይባላሉ፡፡ በሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ ቢሮው በ2016 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ በፌደራል ደረጃ ስላገኘው እውቅናና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አንስተን ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በመለሠች ዘለቀ

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን፡፡

አቶ ሻሻሞ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- የኢንዱስትሪ ልማት ለሀገራችን ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሻሻሞ፡- ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። የሀገሪቱ ግዙፍ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዲሁም አመቺ ሕጋዊ ማዕቀፎች ለዘርፉ እድገት አዎንታዊ አስተዋፅዖ ከሚያበረክቱ መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቷል፡፡

ሀገራችን ለረጅም አመታት በግብርና ስትተዳደር ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ምርቱ ምንም አይነት እሴት ሳይጨመርበት ወደ ውጪ ሲላክ ቆይቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ ሀገራችን ማግኘት ያለባትን ጥቅም በተገቢው እያገኘች አይደለችም፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማለት በተለይ የግብርና ግብአቶችንና ማዕድን ግብአቶችን በመጠቀም ግብአት ጨምሮ የሚያመርት ነው፡፡ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በግብርና ብቻ ማሳደግ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ትርጉም ባለው መልኩ ማስኬድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በተለይ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ታምርት የሚል ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ ስለዚህ ከዚያ ወዲህ ያለው የኢንዱስትሪ መነቃቃት በሀገሪቷ ላይ ትልቅ ድርሻ ይዟል፡፡ እየመጣ ያለው ለውጥም፣ በዚያ ልክ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በኢንዱስትሪ የሚገኘው ገቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመራ መጥቷል፡፡

ወደ ክልላችን ስንመጣም በኢንዱስትሪ ዘርፍ በቁጥርም በጥራትም እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ተኪ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡ በፊት ወደ ውጪ በምትልከው ምርት ላይ ብቻ ነበር ትኩረት ይሰጥ የነበረው፡፡ ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወዲህ ከዚህ በፊት ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በክልሉ በተለይ የቆዳ ምርቶች፣ አነስተኛ ማሽኖች፣ በጨርቃጨርቅ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ዘመናዊ የእንጨትና ብረታብረት ጨምሮ በርካታ ተኪ ምርቶች እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡

ለአብነትም የዳቦ ማሽኖች፣ የወታደር ልብሶች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ እና የመሳሰሉ ምርቶች በክልላችን ተክተው እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በቅርብ የተደረገው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

ንጋት፡- በክልሉ በ2016 ዓ.ም በጀት አመት ዘርፉን ውጤታማ ከማድረግ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ሻሻሞ፡- 2016 ዓ.ም እንደ ክልል ሁለት ትላልቅ ግቦችን ለማሳካት አቅደን ወደ ተግባር የገባንበት አመት ነበር፡፡ አንደኛው እንደ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ዘርፉ ከነበረበት ወደ ቢሮ የተሸጋገረበት አመት ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እስከ ታች መዋቅሮችን የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ ከላይ እስከ ታች ድረስ የተቋም ግንባታ የተካሄደበት አመት ነበር፡፡ አጠቃላይ አደረጃጀቱ የቱ ጋር ምን ተቋም መሆን አለበት የሚለውን ቀደም ብለን አጠቃላይ መዋቅር እንዲሁም አስፈላጊ ግብአቶችና የሰው ሀይል የማሟላት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም መዋቅሩ ጠንካራ እንዲሆን አድርገናል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እቅዶችን በተሻለ መልኩ ማሳካት አለብን ብለን ተንቀሳቅሰናል፡፡ የትኛው ግብ በየትኛው ሰዓትና እንዴትና እነ ማን ናቸው የሚያሳኩት ብለን ለይተናል። ከተቋም ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ወደ ተግባር ተገብቷል። ለአብነትም ከመብራት ሀይል፣ ከልማት ባንክ፣ ከቤቶችና ከተማ ልማት እንዲሁም ከግብርና ሴክተር ጋር መግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ለውጤታማነት ተንቀሳቅሰናል፡፡ አጠቃላይ እቅዳችን በተቀመጠው ጊዜና በተቀመጣው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ የ2016 በጀት አመት አጠቃላይ በፌደራል ደረጃ የተሻለ አፈጻጸም ፈጽመናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከድሬዳዋ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ አግኝተናል፡፡

እንደ ተሞክሮ የተነሱ ተግባራት ነበሩ። ለአብነትም የዘርፉ ማህበራት ጠንካራ እንዲሆን የማድረግ ስራ ሰርተናል፡፡ ስለተመዘገበው ውጤትም የማበረታቻና የማትጊያ ሽልማት አግኝተናል፡፡ ኮምፒዩተር ከነ ፕሪንተሩ፣ አንደኛ ደረጃ ዋንጫ፣ የብር የሰርተፊኬት ሽልማት አግኝተናል፡፡

ዘንድሮ ደግሞ እንዴት ነው ይህንን ውጤት ማስቀጠል የምንችለው ብለን የታዩ ክፍተቶችን በመገምገም ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ አጠቃላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ብለን የለየናቸውን እስከ ታች ድረስ በመገምገም ችግሮችን ደረጃ በደረጃ የመፍታት ስራ ተሰርቷል፡፡ ትልቁ ማሳኪያ የሆነልን የክልሉ አምራች ኢንዱስትሪ ስትሪንግ አደረጃጀት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተደራጅቷል፡፡ ይህም አጠቃላይ አምራች ኢንዱስትሪ ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን የሚፈታና ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚያስኬድ ነው፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የኢንዱስትሪ ልማት ባለቤት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ንጋት፡- ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ያለው ምቹ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ሻሻሞ፡- ክልላችን ለአምራች ኢዱስትሪ ዘርፍ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ምቹ ሁኔታ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ነው፡፡ የመብራት አቅርቦት ሲሆን በተለይም ፓርኮችና ኢንዱስትሪ ዞኖች አካባቢ የተሻለ የመብራት አቅርቦት አለ፡፡

ሁለተኛ የመስሪያና የማሳያ ቦታዎች ናቸው፡፡ ከመስሪያና ማሳያ ቦታዎች አንጻር በአሁኑ ጊዜ ሶስት ህንጻች ግንባታቸው አልቆ ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ አንዱ ባለ ሁለት ወለል ሲሆን ሁለቱ ባለ አንድ ወለል ናቸው። በሀዋሳ ከተማ ሁለት እንዲሁም በይርጋለም ከተማ አንድ ህንጻ ተገንብቶ ዝግጁ ሆነዋል። ሌላም ባለ አራት ወለል ህንጻ በዚህ አመት መጨረሻ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ በዚህ አመት ደግሞ ሁለት ኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት እቅድ ተይዟል፡፡

ሁለተኛ ከመስሪያ ቦታ ጋር ተያይዞ የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ተሟልቶ 24 ሰዓት የማምረት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ የማያቋርጥ የመብራትና የውሃ አቅርቦት ተመቻችቷል፡፡ ሌላኛው ቆሻሻን መልሶ ለማልማት የሚያስችል ትሪትመንት ፕላንት ተተክሏል፡፡

የሀገር ውስጥም ይሁን ውጭ ሀገር አምራቾች በዶላር ሳይሆን የኢትዮጵያ ብር ከፍለው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ክልሉ ለአግሮ ኢዱስትሪ የሚሆኑ የግብርና ግብአቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች፣ የአካባቢ የጸጥታና አምራች የሰው ሀይል ያለበት በመሆኑ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡

ንጋት፡- በክልሉ ምን ያህል አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ?

አቶ ሻሻሞ፡- በክልሉ አጠቃላይ መካከለኛ፣ አነስተኛና ከፍተኛ 1ሺህ 302 አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 130 ከፍተኛ፣ 82 መካከላኛና 1090 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡

ንጋት፡- በሀገራችን የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንዱስትሪ ልማት መነቃቃት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሻሻሞ፡- የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ አለው። ለውጡ ከተጀመረ ወዲህ በዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ታይቷል፡፡ ከዚህ በፊት ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ ግብአቶች እጥረት ነበረ። እነዚህ ችግሮች በሂደት እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡ ሀገር ውስጥ አምራች ኢዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከለውጡ በኃላ አምራቾች ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡

እንደ ሀገርም የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩ የወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላና ችርቻሮ የንግድ ዘርፎች የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው። ይህም የውጭ ባለሃብቶች በጥሬ ቡና፣ ቅባት እህል፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ እና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች እና የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ላይ እንዲሳተፉ እድል ይፈጥራል፡፡

የግሉ አምራች ዘርፉ ወደ ላቀ የዕድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያግዝና አሁን የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ባለሀብቶች በወሳኝ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል። በተጨማሪም ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ጠንካራ የውጭ ንግድ ስርአት እንዲኖር መደላድል ይፈጥራል።

በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት በማስቀጠል ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ራዕይን ዕውን ለማድረግ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓታችንንም ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከታላላቅ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎችና በማደግ ላይ ከሚገኙ በርካታ ሀገራት መካከል የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ሥርዓትና የውጭ ምንዛሪ አጥረት ያለባት ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ ከሕዝብ ብዛት፣ ከሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ከተመጣጣኝና ከተወዳዳሪ ግብአቶች፣ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ሁኔታና ከተፈጥሮ ሀብትና ከማዕድናት አኳያ በብዙ መልኩ ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ሀገር ናት።

የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎቹ የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለማቃለል ማስታገሻ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። የባንክ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆንና የካፒታል ገበያ እንዲጀመር መወሰኑ ለአምራች ዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አማራጭ መፍትሄ ይሆናሉ። እኛም እንደ ክልል ይህንን ለውጥ ተከትለን አምራች ኢንዱስትሪ በብዛትም በጥራትም እየተመራ እንዲሄድ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡

ንጋት፡- ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ሽግግር ለማድረግ በሚደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሻሻሞ፡- ዋናው የአምራች ኢንዱስትሪ ግብአት ግብርና ሲሆን ቀጥሎ ማዕድን ነው፡፡ ስለዚህ ግብርናን ይዘን ነው ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር የምንችለው፡፡ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት የሚመጣጠኑ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ማሻሻያው የአምራች ዘርፉን ችግሮች መፍታት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ንጋት፡- በ2017 ዓ.ም በጀት አመት በዘርፉ የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠል ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ሻሻሞ፡- በበጀት አመቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ነገሮችን በመፍታት የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል በማቀድ ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ ኢኮኖሚያችን ግብርና መር ኢንዱስትሪ እንደመሆኑ መጠን ሞዴል አርሶ አደሮችም ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የግብርና ምርት በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች መቋቋም አለባቸው ብለን ግብ ይዘናል፡፡ ውጤታማ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠርና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በስፋት በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እቅድ ይዘን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ ወደ ውጪ የምንልካቸውን ምርቶች በመጠንም፣ በጥራትም፣ በአይነትም ማሳደግ አለብን፡፡

በአርሶ አደሩ እጅ ያሉና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ለአብነትም እንደ ቃጫ፣ እንቁላል፣ ቀርከሃና የመሳሰሉ ምርቶችን ለማሳደግና እነዚህን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሻሻሞ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡