የአርሶ አደሩን ገቢና የኑሮ ደረጃ በመሠረታዊነት ለማሻሻል በመንግሥት የተጀመሩ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮችን ማጠናከርና በግብርና ልማት ዘርፍ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
የወተት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ግቦችን ማሳካት በሚል መሪ ቃል የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ እንስሳትና ዓሣ ዘርፍ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ የህዝብን ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ድህነትን በመቀነስ የዞኑን አርሶ አደሮችን ገቢና የኑሮ ደረጃ በመሠረታዊነት ለማሻሻል በመንግሥት ከተያዙ ዋና መስኮች አንዱ የሆነውን ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ተግባርን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በዛሬው ዕለት በተካሄደው መድረክ አስታውቋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቡና ምርት ቀጥሎ ለወጭ ንግድ ኤክስፖርት ከሚደረጉ ምርቶች አንዱ የእንስሳት ምርት መሆኑን ጠቁመው የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ የተሻለ ገቢ ከማስገኘቱም በላይ ዘርፉ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አይነተኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የአርሶ አደሩንና የማህበረሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት የተሟላ ለማድረግ የእንስሳት ተዋጽኦ ለመጠቀም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ ዘርፉን በጥራት በመምራት ለገበያ መቅረብ ስንችል ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በመሆኑ የዞኑ አስተዳደር ከፈተኛ ትኩረት ሰጥቶ በንቅናቄ እየመራ ነው ብለዋል።
በኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ የእንስሳት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አበባ፤ የወተት ምርትና ምርታማነት በተሻለ ሁኔታ ስናመርት የምግብ ሥርዓታችንን የምናዘመንበትና የምናስተካክልበት በመሆኑ በእንሰሳት ዝሪያ ማሻሻል ላይ ውጤታማ የሚያደርጉ እስትራቴጂካዊ ስልቶችን ለመከተል ዓላማ ያደረገ መድረክ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ስጥተዋል።
አቶ አስራት አክለውም በሲንክሮናይዜሽን ከተዳቀሉ ላሞችና ጊደሮች 1 ሺህ 616 ጥጃ ይወለዳሉ ተብሎ ከታቀዱት ዉስጥ 645 ጥጃዎች መገኘታቸውን ጠቁማው፤ ተጠቃሚ አርሶ አደር እስከ 6 መቶ 60 ማድረሳቸውን አመልክተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የዘርፉ ባለሙያዎችና በእንሰሳት ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች በምርታማነቱ ሂደት የሚያጋጥሙ ውስንነቶችን በማንሳት በቀጣይ መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ልማትና አመጋገብ፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ የተሻሻለ አያያዝና የግብዓትና የምርታማነት አሰራሮችን አቀናጅቶ በአንድ መንደር ለማከናወን የሚረዱ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እንዲሁም ልምድ ልውውጥና የመረጃ ፍሰትን በማጠናከር ወጪ ቆጣቢ የእርባታ ዘዴዎችን ለመከተል ያለመ መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ መጠናቀቅ የተሻለ አፈጻጸም ላለቸው ወረዳዎች ማህበራትና በዘርፉ ለተሰማሩ ግለሰቦች እንዲሁም ሞዴል አርሶአደሮች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በክረምት የተከናወኑ የወጣቶች በጎ ተግባራት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት ሊወጣ የነበረ ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ለይርጋጨፌ ከተማ የፈርጅ 1 እውቅና ተሰጠ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ዘርፎች በ70 ሚሊየን ብር ወጪ የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ