የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው
በኢትዮጵያ በደማቅ ስነ-ስርዓት የሚከበረው የመስቀል በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔሲኮ/ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ሕዳር 2006 ዓ.ም ነበር፡፡
መስቀል የቱሪስት መስህብ መሆኑ፤ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ የሚደረግለትና ለትውልድ እንዲተላለፍ እገዛ መደረጉ፤ ዓለም አቀፍ አጥኚዎችና ተመራማሪዎችን መሳቡ በቅርስነት እንዲመዘገብ ለሀገራችን ትሩፋት መሆን ችሏል፡፡
የበዓሉ በዩኔስኮ መመዝገብ ያመጣው ፋይዳም በዓሉን ለማክበር በርካታ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በየአመቱ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡
የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ከሚያመጣው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሙ ጎን ለጎንም የሃገሪቱ ገጽታ በመገንባትም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
እንደ መስቀል ያሉ ያልተበረዙና ህዝቡ ያቆያቸው “ፌስቲቫሎች” ከማህበራዊ ትስስራቸው ባሻገር የልማት ቁልፍ መሳሪያ ናቸው፡፡
በመሆኑም በቀጣይ እንደ መስቀል ያሉ ፌስቲቫሎችን በዩኔስኮ ከማስመዝገብ ባሻገር ለምተውና ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ መስራት የባለድርሻ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡
ከበዓሉ ማግስትም ቱሪስቶች ሌሎች ታሪካዊና የቱሪስት ቦታዎችን እንዲጎበኙ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራ ሀገራችንን ያልታዩ ቦታዎችን በማስተዋወቅ እንግዶች እንዲቆዩ የማድረግ ስራው ቢስፋፋ የቱሪዝም ስራው ይበልጥ የማስተዋወቅ እድልን እንደሚፈጥር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የሰሜን ተራሮች፤ አክሱም ሐውልቶች፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፤ ጢያ ትክል ደንጋዮች፤ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ ሐረር ጀጎል፤ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር፣ የፋሲል ግምብ፣ መስቀል፣ ፍቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ሄር-ኢሴ፣ ሸዋል ኢድና ጥምቀት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ደግሞ መስቀል፣ ፍቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ሄር-ኢሴ፣ ሸዋል ኢድና ጥምቀት ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ይመደባሉ፡፡
በአሉንም በድምቀት ለማክበርና ለቱሪስቶችም የተመቸ እንዲሆን የሆቴል አገልግሎት፣ በአሉ የሚከበርበት ቦታ ፅዳቱን የጠበቀ እና የፀጥታ ጉዳይም የተጠናከረ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በበአሉም የሚታደሙ ቱሪስቶችን በአግባቡ በመቀበል ሌሎችም ወደ በአሉ እንዲሳቡ ማድረግ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ሀና በቀለ
የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው

More Stories
በክረምት ወራት የታየውን ትጋት በበጋውም ለመድገም ቁርጠኞች መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ
ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረዉን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው መሪ ዕቅድ ዙሪያ የዉይይት መድረክ ተካሄደ
የየም ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል የቋንቋና የባህል ሲንፖዚየም እየተካሄደ ነው