ሞሮኮ ወደ ፍፃሜ ለማለፍ ዛሬ ምሽት ከፈረንሳይ ጋር ትጫወታለች

ሞሮኮ ወደ ፍፃሜ ለማለፍ ዛሬ ምሽት ከፈረንሳይ ጋር ትጫወታለች

በቺሊ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍፃሜው የአፍሪካ ተወካይዋ ሞሮኮ ከፈረንሳይ ጋር ምሽት 5 ሰዓት ላይ ትፋለማለች።

በውድድር መድረኩ ከ20 ዓመታት በኋላ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት የአትላስ አንበሳዎቹ በምድብ ማጣሪያው ስፔንን እና ብራዚልን በማሸነፍ ቀዳሚ ሆነው ከምድባቸው ወደ ጥሎ ማለፉ መሻገራቸው ይታወሳል።

በጥሎ ማለፉ ደቡብ ኮሪያን 2ለ1 ሲያሸንፉ በሩብ ፍፃሜው ደግሞ አሜሪካን 3ለ1  አሸንፈው በጠንካራ ብቃት ነው ወደ ግማሽ ፍፃሜው የተሻገሩት።

ፈረንሳይ በበኩሏ በምድብ 3 ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ቢሆንም ምርጥ 3ኛ ሆና ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ ይታወቃል።

በጥሎ ማለፉ ጃፓንን 1ለ0 ስታሸንፍ በሩብ ፍፃሜው ኖርዌይን 2ለ1 ረታ ነው ለግማሽ ፍፃሜው የደረሰችው።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በ2022ቱ በዋናው የዓለም ዋንጫም የግማሽ ፍፃሜ ተፈላሚ መሆናቸው አይዘነጋም።

ጨዋታው በፈረንሳይ 2ለ0 አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው።

ሞሮኮ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ለፍፃሜ ለመድረስ ትጫወታለች።

ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ አህጉር ጋና እና ናይጄሪያ ብቻ ናቸው ለፍፃሜ የደረሱት።

ፈረንሳይ እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍፃሜ ደርሳ ዩሯጓይን በመለያ ምት አሸንፋ ሻምፒዮን መሆኗ ይታወሳል።

በሌላ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሁለቱ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አርጄንቲና እና ኮሎምቢያ ወደ ፍፃሜው ለመሻገር ሌሊት ላይ ይጫወታሉ።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ