ህብረተሰቡ በሽታን ለመከላከል የሚሰጡ ክትባቶችን በአግባቡ በመውሰድ እንዳለበት ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መስከረም 28/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረተሰቡ በሽታን ለመከላከል በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጡ ክትባቶችን በአግባቡ በመውሰድ ጤናውን መጠበቅ እንዳለበት በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ገለጸ።
በወረዳው ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት አሰጣጥና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቃሲም ጸጋዬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት የጉበትና የወባ በሽታ የማህበረሰቡ ትልቁ የጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ይቻል ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጡ የክትባት አይነቶችን በአግባቡ በመውሰድ ጤናውን መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የጉበት በሽታን ለመከላከል በክትባት አሰጣጡ ላይ ተግዳሮት የነበረውን የግብአት ችግር በመንግስት በኩል እየተቃለለ መሆኑን ገልጸው፥ ማህበረሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የጤና ባለሙያዎችን አቅም በዕውቀትና በክህሎት በማብቃት ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በሆስፒታልና በጤና ተቋማት ደረጃ ህጻናት በተወለዱ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሚሰጠውን የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት በወረዳው ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ቃሲም ተናግረዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የተጠናከረና በየዕለቱ የሚገመግም ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እንደሚሰራ ያብራሩት ኃላፊው፥ ለውጤታማነቱ ህብረተሰቡ አጎበርን በተገቢው በመጠቀምና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጉበት መከላከያ ክትባት አሰጣጥ ዙሪያ የተሰጠው ስልጠናም ለተግባራዊነቱ በየደረጃው ያሉትን የጤና አደረጃጀቶችን በመጠቀም ተገቢው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የወረዳው ጤና ጽ/ቤት የእናቶችና ህጻናት ስርአተ ምግብ ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሮ ሙሉወርቅ ህያር በበኩላቸው፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሔደው የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት ህጻናት በተወለዱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ክትባቱ በመስጠት በሽታውን ዘጠና ከመቶ መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው 10 ዶዝ ወደ 5 መውረዱ የበሽታው መከላከያ ተደርገው በሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ውጤት የሚያመጣ ነው መሆኑን ጠቁመው፥ ሰልጣኞች የተሰጣቸው ስልጠና በአግባቡ በስራ ላይ በማዋል የእናቶችና ህጻናት ጤና መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል መሰረት ድንቁ፣ መችበዙ ወርቁ እና ቅድስት አብርድ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበራቸውን ግንዛቤ ይበልጥ እንዳሳደገላቸው ተናግረው ለውጤታማነቱም በየቀበሌያቸው ለሚገኙና ለሚመለከታቸው የጤና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ተግባር እንደሚገቡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው
የአርባምንጭ የድል ፋና የመጀሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አንዳንድ በሆስፒታሉ ያገኘናቸዉ ተገልጋዮች ተናገሩ
በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ