በክረምት የተከናወኑ የወጣቶች በጎ ተግባራት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት ሊወጣ የነበረ ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

በክረምት የተከናወኑ የወጣቶች በጎ ተግባራት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት ሊወጣ የነበረ ወጪ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በክረምት ወራት በተከናወኑ የወጣቶች በጎ ተግባራት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከመንግስት የሚወጣ ወጪ ማዳን መቻሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የበጋ ወራት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ወጣቶች በግንባር ቀደምነት በማሳተፍ የተሰራው ስራ እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፥ ሰው ተኮር ተግባራት በተግባር የተረጋገጠበት ስራ በክረምት ወራት መሰራታቸውን ገልጸው የተሰሩ ስራዎች ከፍ ያለ ዋጋ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መልካም ተግባር ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በበጋ ወራትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት አስተዳዳሪው ለዚህም ሁሉም መሳተፍ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

ቀጣይ ጥንካሬዎችን በማጎልበት እና ጉደለቶችን ማረም እንደሚገባም አመላክተዋል።

የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ገመዳ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት ለአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ግንባታ፣ በጤና፣ በትምህርት በአከባቢ ጥበቃና በሌሎች ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ከ436 ሺህ በላይ ህብረተሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፥ በዚህም ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በወጣቶች ጉልበት ለማዳን ታቅዶ ከዕቅድ በላይ መፈጸም መቻሉንም ገልፀዋል።

የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሪፖርትና የበጋ ወራት ዕቅድ ለውይይት ያቀረቡት የመምሪያው ምክትል ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላምነሽ እንግዳ ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች 400 መኖሪያ ቤት ለመገንባትና ለመጠገን ታቅዶ ከ700 በላይ ቤቶች ግንባታና ጥገና መከናወኑን ተናግረዋል።

በክረምቱ የታየውን ሰው ተኮር ተግባራትን በበጋውም አጠናክሮ ለመቀጠል መታቀዱን ገልጸው፥ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች በክረምቱ የብዙዎችን እምባ ያበሰ ትልቅ ስራ መሰራቱን በመጥቀስ፥ በበጋ ወራት የታቀደውን ለማሳካት ልዩ ርብርብና ትኩረት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ መዋቅሮችና ማህበራት ዕውቅና ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን