በኢያሱ ታዴዎስ
“የዶሮ እንቁላል አለ”፡- በሆሳዕና ከተማ ጎዳናዎች ላይ ወደ አመሻሽ ገደማ በተደጋጋሚ የሚሰማ ድምጽ ነው፡፡ በአካባቢው ያለን ሰው ሁሉ ጆሮውን ወደ ድምጹ እንዲያዘነብል ያስገድዳል፡፡ እሱ ግን ሥራው ነውና ለመግዛት የሚያስቆመው ሰው እስኪያገኝ ድረስ መልሶ መላልሶ ይህንኑ ድምጽ ያሰማል፡፡ በእኔም በጆሮዬ የተንቆረቆረው ይኸው ድምጽ ነበር፡፡
ድምጹን ወድጄዋለሁ፡፡ እንድወደው ያደረገኝ ደግሞ በራሱ ዜማ አውጥቶለት የሰዎችን ትኩረት በሚስብ መልኩ ለገዢው ጥሪ እያደረገ ያለመታከት ማሰማቱ ነው፡፡ በአንክሮ የተመለከተው ሥራ ወዳድነቱን አፍታም ሳይቆይ ይገነዘባል፡፡
በሰላሳዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነው። አለባበሱ የክት እንደሚባለው ነው፡፡ ሽሮዋማ ቀለም ያለው ሸራ ሱሪ ታጥቋል፡፡ ከላይ ደግሞ በሸሚዝ ላይ ኮት ደርቦ ቆልፎታል፡፡ ለአረማመድ የሚያመቸውንም ጫማ ተጫምቷል፡፡
አንገቱ ላይ ዞራ እስከ ደረቱ የወረደችው ቀጭን ሪቫን፣ የወረቀት ታፔላ አንጠልጥላለች። ታፔላውም “የሞባይል ካርድ አለ” የሚል መልዕክት አዝሏል፡፡ በእጁ ደግሞ ትከሻውን ደገፍ አድርጎ በዛ ያለ እንቁላል የተቀመጠበት ክፍት የካርቶን ማስቀመጫ ጣል አድርጓል፡፡
ገራገርነቱን በሚያሳብቀው የፊት ገጽታው ፈገግታን አክሎበት ለአላፊ አግዳሚው ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል አጸፋዊ ምላሽ ይሰጡታል፡፡ በከተማዋ ታዋቂ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ የተወሰኑ ጉዞዎችን አብሬው በመጓዝ የሥራውን ሁኔታ ካጤንኩ በኋላ የተወሰነ እረፍት አደረግን፡፡ ከዚህ በኋላ ወጋችን ቀጠለ፡፡
ብርሃኑ ተሻለ ይባላል፡፡ በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ጽ/ቤት የገቢ ምጣኔ ጥናትና መመሪያ ዝግጅት የስራ ዘርፍ ላይ በባለሙያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡
ትውልድና ዕድገቱ በሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ አሼ ቡቁና ቀበሌ ነው፡፡ አምስት ልጆችን ባፈራው ቤተሰቡ ውስጥ 3ኛ ልጅ ከመሆኑም በላይ ብቸኛ ወንድ ነው፡፡ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የአባቱ ክትትል አልተለየውም ነበር፡፡
“አባቴ በትክክል ገርቶ ነው ያሳደገኝ” ሲልም ከልጅነት ወደ ዕውቀት እንዲሻገር የአባቱ ሚና ምን ያህል እንዳገዘው ይናገራል፡፡ ትምህርቱንም ቢሆን በአግባቡ እንዲከታተል ከፍተኛ እገዛ እንዳደረጉለት ይመሰክራል፡፡
በዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ከሆሳዕና ከተማ በእግር አንድ ሰዓት ያህል በሚርቀው አሼ ቡቁና ቀበሌ ተምሯል፡፡ 9ኛና 10ኛ ክፍልን ደግሞ በየካቲት 2567 ት/ቤት፣ እንዲሁም 11ኛና 12ኛን ደግሞ በዋቸሞ መሰናዶ ት/ቤት ተምሯል፡፡
ታዲያ በትምህርት ቆይታው ጥሩ የቀለም አቀባበል እንደነበረው ይገልጻል፡፡ በተለይም ከ3ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ እንዳጠናቀቀ ይናገራል፡፡ 9ኛና 10ኛ ክፍልንም እንዲሁ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቁን ይናራል። ታዲያ ትምህርቱን ሲማር ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆኑለትም፡፡
በተለይም የትምህርት ደረጃው ከፍ እያለ ሲመጣ ለተሻለ ትምህርት ከሚኖርበት የገጠር ቀዬ ወደ ከተማ መጥቶ መማር ነበረበት፡፡ በከተማም በግሉ ቤት ተከራይቶ ይማር ስለነበር ከቤት ኪራይ አልፎ በቀላሉ ቀለቡን ለማሟላት ይቸገር ነበር፡፡
ረሃብና ጥማቱ አይጣል ነበር፡፡ የቀለቡ ነገር ቢከብደውም አንገቱን አልደፋም፡፡ ይልቅስ በትምህርቱ ጎበዝ በመሆኑ ዓላማው ላይ ትኩረት አደረገ፡፡ የዛሬውን ችግር ነገ በሚሰማራበት ሥራ ድል እንደሚነሳ አልተጠራጠረም ነበር፡፡
ይሄ ቆራጥነትና የዓላማ ጽናቱ በተገቢው ተምሮ ወደ ከፍተኛ ተቋም መግቢያ ፈተናን በጥሩ ውጤት አምጥቶ እንዲያልፍ ረዳው፡፡ በወጣለት ዕጣ መሰረትም ቴፒ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል እንደ ልማዱ ትምህርቱ ላይ ትኩረት አድርጎ የ3 ዓመታት ቆይታ ካደረገ ወዲህ ሊመረቅ ችሏል፡፡
ከዚያም በ2006 ዓ.ም አሁን እየሰራ የሚገኝበትን የሆሳዕና ከተማ ገቢዎች አስተዳደር በሰራተኝነት ተቀላቀለ፡፡ ወደ ሥራው ዓለም እንደተቀላቀለም በባህርይው ከሰዎች ጋር ቶሎ የመላመድ ልማድ ነበረውና ሥራው አዲስ አልሆነበትም፡፡ የሚቸግረውን ከታላላቆቹ በመጠየቅ ወዲያው ሥራውን ለመደው፡፡
ይሁን እንጂ በወር የሚያገኘው ደመወዝ ኑሮውን ከእጅ ወደ አፍ ከመሆን አላዳነውም። ገና ወሩ ሳይጋመስ ገንዘቡ አልቆ ሌላኛው ወር እስኪመጣ ድረስ ጭንቅ ሆነበት፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግስት ሥራው እንዳሰበው ወጪውን ሁሉ አሟልቶ ተርፎት እንዲቆጥብ አላስቻለውም፡፡
ወር እየጠበቀ የሚያገኘው ገንዘብ ከችግር ስላላዳነው ቆም ብሎ እንዲያስብ አስገደደው። ወትሮም አቅሙ እስከምን ድረስ እንደሆነ ልቡ ያውቃል፡፡ ታዲያ የወር ደመወዙን ብቻ እየጠበቀ በየጊዜው እየተወደደ የመጣውን ኑሮ መሻገር እንደማይችል ስለገባው ምን ማድረግ እንዳለበት ቀን ከሌት ያወጣ ያወርድ ጀመር፡፡ ደግሞ ደጋግሞ ከራሱ ጋር መከረ፡፡
ይሄኔ የመጣለት ሃሳብ የመንግስት ሥራውን እየሰራ በትርፍ ሰዓቱ በንግድ ሥራ መሰማራት ነበር፡፡ በቅድሚያ ግን የቅዳሜ ገበያን ንግድን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሳሙና፣ ክብሪት፣ ግሊስሪን የመሳሰሉ ጥቃቅን ሸቀጦችን መነገድ ጀመረ፡፡ ንግዱን አስቀጥሎ እያለም በ2007 ዓ.ም ትዳር መሰረተ፡፡
ከሁለት ጉልቻ በኋላ መደበኛ የመንግስት ስራውን እየሰራ ንግዱን ለመቀየር ወጠነ። ይኸውም የእንቁላል ንግድ ነበር፡፡ 2010 ዓ.ም ውጥኑ ተሳክቶ አዲሱን ንግዱን አሃዱ ብሎ የጀመረበት ነበር፡፡ በወቅቱ በምንድህስና ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቆ ያለሥራ ተቀምጦ ከነበረው ከቅርብ ጓደኛው ጋር አብሮ ለመነገድ ተማከረ፡፡
ምክሩም መሬት ወረደና ሁለቱ ጓደኛሞች እንቁላል መነገድ ጀመሩ፡፡ ብርሃኑ ይነግድ የነበረው የመንግስት የሥራ ሰዓቱን በማይሻማ መልኩ ነበር። ንግዱንም ሲጀምሩ ከቀድሞው የጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ በ3 ሺህ፣ በ4 ሺህ ከዚያም አለፍ ሲል በ5 ሺህ ብር እንቁላል በመረከብ ወደ ሆሳዕና ከተማ በማምጣት ነበር፡፡
ቀስ በቀስ ንግዱን እየለመዱት መጡ፡፡ ትርፍ ግን ሊያገኙበት አልቻሉም፡፡ የትርፉ ነገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሲደርስ ጓደኛው ንግዱን ለማቆም ወሰነና በውሳኔው ጸና፡፡ ትርፍ በጊዜ ሂደት እንደሚመጣ የተረዳው ብርሃኑ ግን የጓደኛውን ፈለግ ሊከተል አልፈለገም፡፡ ይልቅስ የማታ ማታ ዓላማው ግቡን እንደሚመታ ራሱን አሳምኖ ነበርና ለብቻው በእንቁላል ንግዱ ቀጠለ፡፡
ኪሳራ በማስተናገዳቸው ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጥ ያደረገው በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ የቀሰመው የኢኮኖሚክስ ዕውቀቱ እንደነበርም እግረ መንገዱን ይናገራል፡፡ ኪሳራ በንግድ ዓለም በተለይም በጅማሬው ምዕራፍ ሊገጥም የሚችል እንደሆነና ቀስ በቀስ መውጣት እንደሚቻል ተገንዝቧል፡፡
ንግዱን ሲጀምሩ የራሳቸውን ሱቅ ተከራይተው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ሱቁ ፈረሰ። የእንቁላል ዋጋም እየተወደደ መጣ፡፡ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለብቻው ለመጋፈጥ ቢገደድም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ እንቁላል እንደ ቀድሞው ከሌላ አካባቢ ማምጣቱን ትቶ ከዚያው ከሆሳዕና ከተማ ከአከፋፋዮች እየተረከበ ለሚጠይቁት ሰዎች መነገድ ጀመረ፡፡
ይህን ማድረጉ ደግሞ ካላስፈላጊ እንግልት እና ከትራንስፖርት ወጪ እንዳዳነው ጠቆም አድርጓል፡፡ ንግዱ ውጤታማ እንዲሆን በውስጡ የተፈጠረው ፍላጎት እያየለ ሲመጣም ከተማዋን በእግሩ እያካለለ በባለ ሶስት እግር ጋሪ መሸጡን ቀጠለ፡፡
በዚህም በከተማው በስፋት እየታወቀ መጣ። “የዶሮ እንቁላል አለ” እያለ ራሱ በፈጠረው ዜማ በከተማዋ ጎዳናዎች እየጮኸ የሚያስተጋባው ድምጹ መለያው ሆነ፡፡ ባለፈ ባገደመ ቁጥርም “የዶሮ እንቁላል አለ” እያሉ በእሱ ዜማ የሚጠሩት አያሌ ናቸው፡፡ የሚጠሩት ግን በንቀት አሊያም በሹፈት አልነበረም፤ ሥራውን ለማበረታታት እንጂ፡፡ ልጅ አዋቂው ሁሉ ይወደዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሰላምታ ይሰጡታል፡፡ “ጎበዝ! በርታልን” የሚሉም አሉ፡፡
የመንግስት ሰራተኛ በመሆኑ በቀን ውስጥ ለንግዱ የሚጠቀመው ሰዓት ውስን ነበር። ከ11 ሰዓት ተኩል በኋላ እስከ ምሽት ድረስ፡፡ በመንግስትና በግለሰብ መስሪያ ቤቶች የሚሠሩ ሰዎች የሚያርፉባቸውን የእረፍት ቀናት (ቅዳሜና እሁድ) እሱ ለንግዱ እንደ በረከት ነው የሚያያቸው። ከሰኞ እስከ አርብ ያልተጠቀማቸውን ቀናት ማካካሻ ናቸው፡፡ እንደ ልብ ይነግድባቸዋል፡፡
ታዲያ በጊዜ ሂደት ከራሱ ጋር በእጅጉ ያዋሃደውን የእንቁላል ንግድ፣ አሁንም ትርፉ ብዙ አያሳስበኝም ሲል አስገራሚ ምላሽ ይሰጥበታል። “እኔ በፍፁም ትርፍ ላይ ትኩረት አላደርግም። ዋናው ነገር ሥራውን መሥራቴና ሕብረተሰቡን መጥቀሜ ነው” ሲልም ተደምጧል፡፡
“ከአንድ መቶ ብር እንቁላል ላይ አንድ እንቁላል ትርፍ ካገኘሁ ለእኔ ከበቂም በላይ ነው። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ከሁለት መቶ ብር እንቁላል ላይ ነው የአንድ እንቁላል ትርፍ የማገኘው” ሲል ግርምትን የጫረብኝን፣ ግን ደግሞ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሲታሰብ ለሕብረተሰቡ በጎ ዓላማ ያደላን ሃሳብ አካፈለኝ፡፡
ሰበብ አስባብ እየፈለገ ትርፉን ብቻ እያሰበ ከመጠን ያለፈ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፍ ነጋዴ በበዛበት በዚህ ጊዜ፣ እንደ ብርሃኑ ያለ ከራሱ ይልቅ ለሕብረተሰቡ የሚያስብ ነጋዴ ማግኘቴ ግርምቴን ይበልጥ ጨምሮታል፡፡
ወጣት ብርሃኑ ከመንግስት ሥራው በተጓዳኝ እንቁላል ንግድ ላይ መሰማራቱ ከሕብረተሰቡ ዘንድ ጉራማይሌ አስተያየቶችን እንዲያስተናግድ አድርታል፡፡ አብረውት በመንግስት ሥራ የተሰማሩትና በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች ለሥራ ያለውን ታታሪነት ስለሚያውቁ በጎ ምላሽ ነበራቸው፡፡
ዳሩ ግን ዓላማውን ያልተረዱት በጥርጣሬ ይመለከቱታል፣ ይገፉትማል፡፡ የከተማው ገቢዎች ጽ/ቤት ሰራተኛ በመሆኑ ንግዱን ለስለላ እንደሚጠቀም የሚያስቡም ነበሩ፡፡ “በጤናው አይደለም” የሚሉም አልጠፉም፡፡ ብዙሃኑ የተከበረ የመንግስት ሥራ እየሰራ በሆሳዕና ከተማ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ እንቁላል መሸጡ አይዋጥላቸውም ነበር፡፡ ከስስት ጋርም ያገናኙታል፡፡
በተለይም የንግድ ሥራውን የጀመረ ሰሞን አሉታዊ አስተያየቶች ይበዙ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በጊዜ ሂደት ግን ሰዎች እየለመዱ እንደመጡ ይናገራል፡፡ ይበልጥኑ እንዲበረታታ ያገዘው በመንግስት መስሪያ ቤቶች በኃላፊነትና በባለሙያነት የሚያገለግሉ ሰዎች በየጊዜው የሚሰጡት ያልጠበቀው በጎ አስተያየት ነበር፡፡
“አሁን ግን ሁሉም ነገር ተለውጦ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው አስተያየት ፍጹም ጤናማ ነው። ይህም ሥራዬን እንድወደውና እንድገፋበት ምክንያት ሆኖኛል” ሲልም በሂደት በሥራው ሕብረተሰቡን ማሳመን መቻሉን ይናገራል፡፡
የንግድ ሥራውም ቢሆን በእንቁላል ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ያለችውን ጥቂት ጊዜ አሟጥጦ ለመጠቀም በማሰብ የሞባይል ካርድም እግረ መንገዱን ይሸጣል፡፡ እሱ እንደሚናገረውም ገና ጠዋት ወደ ቢሮ ከማቅናቱ በፊት “የሞባይል ካርድ አለ” የሚለውን የወረቀት ታፔላ ደረቱ ላይ ለጥፎ የሞባይል ካርዱን ይዞ ለሚፈልግ ሰው ይሸጣል፡፡
ከቢሮው ቅጥር ግቢ ሲደርስ ደግሞ ታፔላውን ከኮቱ ስር በመወሸቅ የዘውትር የቢሮ ሥራውን ደቂቃ እንኳን ሳይሸራርፍ በትጋት ይሰራል፡፡ መደበኛ ሥራውን እንዳከናወነም ወደ ውጪ በሚወጣበት ቅጽበት የሞባይል ንግዱን ያጧጡፋል፡፡ በመደበኛውም ሆነ በንግዱ ሥራ ቀልድ አያውቅም፡፡
ታዲያ ታታሪው ብርሃኑ ገና ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀል የነበረውንና አሁን ደግሞ በንግዱ ዘርፍ ተሰማርቶ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን ጊዜ ማነጻጸሩ አልቀረም፡፡ ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው ሲልም ይመሰክራል፡፡
“ያኔ እኮ ደመወዝ በተቀበልኩ ጊዜ ገንዘቡ ከአስራ አምስት ቀን አይዘልም ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ ቤተሰቤን የማስተዳድረው ከመደበኛው የመንግስት ሥራ እና ከንግዱ በማገኘው ገቢ ነው። ከባለቤቴ ጋር በጋራ ሁለት ልጆችን አፍርተናል። ቤተሰቤ የሚተዳደረው በእኔ ገቢ ብቻ ነው። ስለዚህ ቢያንስ ለእኔና ለቤተሰቤ መትረፍ ችያለሁ። ይህ ደግሞ ሥራን ሳልንቅ ዝቅ ብዬ በመስራቴ የመጣ ውጤት ነው” ሲልም ልዩነቱን ያስቀምጣል።
ወጣት ብርሃኑ በማሕበረሰብ ደረጃ መለወጥ ያለበት ትክክለኛ ያልሆነ አመለካከት አለ ሲልም ከልምዱ የተረዳውን ሕብረተሰቡ ቢሰማልኝ በማለት ያስተላለፈው መልዕክት አለ፡-
“ማሕበረሰባችን በአንድ ጊዜ ለውጥ ካልመጣ አይቀበልም፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ በአንድ ጀንበር የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ ለውጥ የምናመጣው ደጋግሞ በመሥራት በሂደት ነው፡፡ ደግሞም የተሰማራንበትን ሥራ ምንም ይሁን ምን ማክበር አለብን፡፡
“ያ ያከበርነው ሥራ ነው መልሶ የሚያከብረን። በዚህ ኑሮ ውድ በሆነበት ጊዜ ሥራን ከፍ ዝቅ ሳናደርግ ካልሠራን ለመቋቋም እንቸገራለን፡፡ አንድን ሥራ ሳናቋርጥ ውጤታማ እስከምንሆን ድረስ በትጋት መሥራት አለብን፡፡”
ወጣት ብርሃኑ ከራሱ አልፎ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተጽዕኖ ስለማሳደሩ አንዱ ማሳያ የእሱን ፈለግ ተከትለው ሥራን ሳይንቁ መሥራት የጀመሩ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ “አንተን አይቼ እኔም ተለውጫለሁ፤ አርዓያዬ ነህ” የሚሉ አስተያየቶችን ማድመጥ ለእሱ እንግዳ አይደለም፡፡ ለምዶታል፡፡ ይህ ደግሞ የመንፈስ እርካታ ያጎናጽፈዋል፡፡
አጋጣሚውን አግኝቼ ያወራኋቸው የተወሰኑ ሰዎች ስለእሱ ምስክርነታቸውን ሰጥተውኛል። ሁሉም ማለት ይቻላል ስለሥራ ወዳድነቱና ትጋቱ በአድናቆት መስክረውልኛል፡፡ ደግሞም ይወዱታል፡፡ የሚወደድ ባህርይ እንዳለውም አጫውተውኛል፡፡
ጉዞው እዚህ ላይ አልተገታም፡፡ በዚሁም ረክቶ አላበቃም፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ የስኬት ምዕራፍ እንደሚጠብቀው እምነት ጥሎ አሁንም በትጋት መሥራቱን ቀጥሎበታል፡፡ ክብር የሰጠው ጥቂት የሚመስለው ሥራ በቀጣይ የሕይወት ምዕራፉ የትዕግስቱንና የትጋቱን ፍሬ እንደሚያበላው እርግጠኛ ሆኖ እርምጃውን ቀጥሏል፡፡
በውብ ዜማ የተከሸነው “የዶሮ እንቁላል አለ” የሚለው ሸማቹ እንዲገዛው የሚያነሳሳው ጥሪው፣ በሚጓዝባቸው ቦታዎች ሁሉ በጉልህ ይሰማሉ፡፡ እኔም በትጋቱ እየተገረምኩ ከልብ የመነጨ መልካም ምኞቴን እየገለጽኩለት በዓይኔ ሸኘሁት፡፡ “የዶሮ እንቁላል አለ”… “የዶሮ እንቁላል አለ”…“የዶሮ እንቁላል አለ” ከዓይኔ ርቆም ድምጹ ይሰማኛል…
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው