ስኬታማ የነበረው የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት

በመሐሪ አድነው

የሀገራዊ ምክክሩ አንዱ አካል የሆነው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ከሰሞኑ በሲዳማ ክልል ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በምክክር ሂደቱ ለችግሮቻችን መፍትሔ በማመላከት የተረጋጋ ሀገርን በመፍጠር ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል በሲዳማ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካለት ገልፀዋል፡፡

ከጋዜጣችን ሪፖርተሮች ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሠራተኛ ማህበራት እና የሴቶች ኮንፈደሬሽን ተወካዮች እንደገለፁት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ግልፅና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መንሸራሸራቸውን አንስተዋል፡፡

የሲዳማ አድንድነት ፓርቲን /ሲአፓ/ ወክለው የተገኙት አቶ መንክር ሃ/ሚካኤል ከ1964 ዓ.ም የመሬት ለአራሹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ረጅሙን ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡

የንጉሱ ሥርዐት ከተገረሠሠም በኋላ የሲዳማ አርነት ንቅናቄን መሥርተው እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ የትጥቅ ትግል አድርገዋል፡ ፡ ከኢህአዴግ እስከ ብልጽግና ዘመንም በተፎካካሪነት ዘልቀዋል፡፡ ከ5ዐ አመታታ በላይ በቆዩበት የፓለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት ወቅት በጠመንጃ ከመሸናነፍ በስተቀር በሃሳብ የተሸናነፉት ጊዜ አልነበረም፡፡

ይሄ ሂደት ደግሞ ደም ከማፋሰስና ሀገራችንን ከማደህየት ባለፈ የሠለጠነ ፖለቲካ እንዲኖረን አላደረገም፡፡ አሁን የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሄ እንደሚኖረው እምነታቸው እንደሆነ አቶ መንክር ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ ፓርቲ እርሰ በርስ ያላግባቡና ሲንከባለሉ የመጡ ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን በማንሳት አጀንዳ የመለየት ሥራውን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን እንዳከናወኑ ጠቁመዋል፡ ፡ ከ25ቱ ተወካዮች ውስጥ መካተታቸውንም በመጠቆም፡፡

የሃይማኖት ተቋማት የሠላም መሠረት በመሆናቸው ለሠላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር እንደሚሠሩ የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሸበዲኖ ወረዳ ቤተክህነትን ወክለው የተገኙት መጋቢ ስብሃት ቀሲስ ሠለሞን ስዩም ናቸው፡፡ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ምክክር መደረጉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ ነው የሚኖረው። ህዝቡ ተመካክሮ የወሰነው ውሳኔ ሃገራዊ መግባባትን ለማምጣት በሚደረገው ሂደት ለአፈፃፀምም ምቹ ነው የሚሆነው፡፡ ህብረተሠቡም የትግበራው አጋዥ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አጀንዳው የራሱ የህዝቡ ስለሆነ ሲሉ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ፓርቲዎች ባልነበሩበት ከጥንት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን በእያንዳንዱ ብሄር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ችግሮቹን በመመካከርና በመወያየት ነው ሲፈታ የኖረው፤ ስለሆነም አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ ችግሮቻችንን በሠለጠነ መልኩ ለመፍታታ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የእነ ቀሲስ ሠለሞን ቡድን የለየው አጀንዳ እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም አንዱ የሌላውን አክብሮ፣ እንዲሁም ህግንና ሥርዓትን ጠብቆ የራሱን ሃይማኖት አስተምህሮ ብቻ እንዲያራምድና ለሀገርና ለወገን ምቹ ጠቃሚ አሻራ ማኖር እንዳለበት ነው፡፡

ሌላኛው አጀንዳ ደግሞ “በህገመንግስቱ አንቀፅ 39 የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚለው ነገር ኢትዮጵያን የሚወክል አይደለም፤ ቢወጣ ጥሩ ነው” የሚል ሃሳብ ተንፀባርቆበታል፡፡

የሐዋሣ ከተማ ሴቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ህይወት ቤላሞ በበኩላቸው መመካከር የችግሮቻችን መፍቻ አንዱ መንገድ በመሆኑ፤ ምክክሩ ለውጥ እንደሚያመጣ እምነት አላቸው።

በአጀንዳ ልየታውም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ሂደት እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ በሚያመጡ ሃሳቦች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

በአጀንዳ ልየታው ወቅት የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ በመሆናቸው የጋራ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ነቅሰን ለኮሚሽኑ አቅርበናል፤ ተግባራዊ ውጤትም እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ችግር የሚቀረፈው በመወያየት፣ በመነጋገርና በመተማመን በመሆኑ ምክክር አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ ተጽእኖ ፈጣሪ ማህበረሠብን ወክለው በምክክሩ የተሳተፉት ዶ/ር ሲሳይ ሠለሞን ናቸው፡፡

ዶ/ር ሲሳይ እንዳሉት አሁን ላይ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች አለመረጋጋቶች ይታያሉ። እነዚህን ችግሮች መፍታት የሚቻለውና አማራጭ የሌለው መንገድ ዘመናዊ በሆነ መልኩና በሰለጠነ አኳኋን ችግሮቻችንን በውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ብቻ ነው፡፡

ችግርን በችግር፣ ጦርነትን በጦርነት መፍታት እንደማይቻልና እስከ አሁን የመጣንበት የመሸናነፍ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ እንዳላስገኘም ያምናሉ፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ተቀራርቦ መመካከር የሚኖረው ሚና የጎላ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር ያለንን በቂ ሃብት ለመጠቀም ሠላምን ማስጠበቅ፣ አንድነትን ማጠናከርና በድህነት ላይ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ አሳታፊና አካታች እንደነበር የገለፁት ዶ/ር ሲሳይ ጐልተው የተነሱት በታሪክ መዛባቶች ላይ፣ ባልተገቡ ትርክቶች ዙሪያና ፍትሃዊና በእኩልነት ተጠቃሚነት ዙሪያ ሃሳቦች ተነስተው አጀንዳዎች ተሰብስበዋል፡፡

መንግስት ማድረግ ያለበት ህዝብ አጀንዳዬ ነው ብሎ የሠጠውን ጉዳይ በታማኝነት ወደ ተግባር መለወጥና ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ከህዝቡ የሚጠበቀው ደግሞ የጋራ እሴት የሆኑ ነገሮችን መጠበቅ፣ ባህሎችን ማክበርና ለተግባራዊነቱ ከምክክር ኮሚሽኑ ጐን መቆም አለበት ተብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ኮንፌደሬሽን የመጡት አቶ ጫንያለው አወቀ ሲቪክ ማህበራትን ወክለው ነበር የተገኙት፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው ውይይት አጀንዳዎችን ከማሰባሰብ ያለፈ ጠቀሜታ አለው የሚሉት አቶ ጫንያለው በሂደቱ ህብረተሠቡ ይበልጥ እየተቀራረበ ሃሳቡን እንዲለዋወጥ አድርጐታል ባይ ናቸው፡፡

“በውይይቱ ላይ መሳተፍ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ቀደም ሲል በውስጤ የነበረው ስጋት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በማህበረሠቡ ውስጥ ምንም አይነት ልዩነት የለም ማለት በሚቻልበት ደረጃ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በጉልህ የተነሱ ሃሳቦች እንዳመላከቱ ጠቁመው የሚሻለውም አንድነት ብቻ መሆኑንን ገልፀዋል፡፡

“የቸገረው የዚህን አይነት የውይይት መድረክ የሚያዘጋጅ ነው እንጂ በሀገራዊ አንድነቱ ላይ የሚደራደር ህዝብ አለመኖሩን መገንዘብ በመቻሌ ከፍተኛ ተስፋ አጭሮብኛል።” ሲሉ ነው አቶ ጫንያለው የገለፁት፡፡

ከነሐሴ 22 ጀምሮ በሲዳማ ክልል ሲካሄድ የነበረው የአጀንዳ ልየታ ሥራ በስኬት መጠናቀቁን የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገልፀዋል። የተጀመረው ሥራ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት አስቻይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የአጀንዳ ልየታ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በኮሚሽኑ የተያዙ እቅዶች በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሲዳማ ክልል ደረጃ የተለዩ አጀንዳዎች በሀገር ደረጃ በኮሚሽኑ ለሚደራጀው ዋና አጀንዳ በግብአትነት የሚውል መሆኑም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡ በተወካዮች አማካኝነት የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተረክበዋል፡፡