“የክህሎት መር ሥራ ዕድል ፈጠራ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት እና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው፤ በከተማው በሥራ ዕድል ፈጠራ በተከናወኑ ሥራዎች በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላም፣ በንብ ማነብና በሌሎች ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡
በኢንዱስትሪ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ ሆኖ እየቀረበ እንደሆነ ከንቲባው አንስተዋል፡፡
በከተማው ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ማህበራት የመስሪያና መሽጫ ቦታዎችን በማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊትነቱን በመውሰድ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ በብድር አመላለስ የሚታየውን ክፍተት ሁሉም ተበዳሪዎች በወቅቱ በመመለስ የበኩላቸውን እንዲወጡና የምክር ቤቱ አባላት በአመላለስ ርብርብ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የዲላ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የተረጋጋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስነ ምህዳር ለመፍጠር፣ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ወሳኝነት አለው፡፡
ክህሎት መር ሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ የሁሉም ባለድርሻዎች ቅንጅት ወሳኝነት እንዳለው የገለጹት አቶ ታሪኩ፣ በከተማው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ማህበራት እያስመዘገቡ ያለውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ ክህሎት መር በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አብነት አክሊሉ ናቸው፡፡
አክለውም አቶ አብነት ሥራ ለተፈጠረላቸው ወጣቶችን በተገቢው በመደገፍ የዘርፉን ውጤታማነት ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በጉባኤው ማህበራትን በማበረታታት፣ በመደበኛ ዕቅድ በሚፈጸሙ ጉዳዮች የሚስተዋሉ ውስንነቶችና በቀጣይ በሚተገበሩ ሥራዎች መመሪያ ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው